ታሪክ ቀያሪዎቹ የቱሪዝም ዘርፉ ፈርጦች

ዜና ትንታኔ

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበሰቃ ሀይቅ ላይ የተገነባውን “ቤኑና መንደር”ን መርቀው ከፍተዋል። በመዲናዋ በገበታ ለሸገር፣ በክልሎች ደግሞ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ታሪክ ቀያሪ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ተከናውነው ለአገልግሎት በቅተዋል።

እነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክቶች ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ? ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆንስ ምን መደረግ ይኖርበታል? በሚሉና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉ ባለሙያዎች ሙያዊ ሃሳባቸውን አጋርተውናል።

ከፍተኛ የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልከዓ ምድሮች እና ህያው ባህሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትቀጥል በአሁኑ ጊዜ በቱሪዝም መሠረተ ልማት እየታደሰች ትገኛለች። የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታን በመሠረታዊነት እየቀየሩ ናቸው። ከገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከልም ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ወንጪ እና ጎርጎራ ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከቢሮ ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ሀገር እየሰፉ፣ ከመሀል ሀገር ራቅ ያሉ የመስህብ ሥፍራዎች፣ መልከዓ ምድሮች እና ፓርኮችን በመሠረተ ልማቶች  በማስተሳሰር አዳዲስ የቱሪስት እድሎችን እንዲከፈቱ መደላድል እየፈጠሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።

እነዚህ አቅሞች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከቱሪዝም በእጅጉ ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋሉ። የውጭ ምንዛሪ ገቢን ያሳድጋሉ፣ የሀገር ውስጥ ሀብትን በማንቀሳቀስ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። እንደ ታዳሽ ኃይል፣ ችርቻሮ እና የምግብ ማቀነባበሪያ ያሉ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ ይላሉ።

የቱሪዝም የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶቹ ፈርጀ ብዙ ፋይዳ አላቸው ያሉት አያሌው (ዶ/ር)፤ ማህበረሰቦችን የሚያጠናክር እና የተፈጥሮ ሀብቶችን የሚጠብቅ ሁሉን አቀፍ፣ አካባቢያዊና አካታች እድገትን ያበረታታሉ ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በመሠረተ ልማት እጦት ከተጓዦች ተደብቀው የቆዩትን መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ሥፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮች፣ እጅግ የተለዩ አዕዋፋት እና ዕጽዋቶችን በትስስሩ በተፈጠሩ ዕድሎች ለጎብኚዎችና አሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀው እጅግ ውብ የሆነው “ቤኑና መንደርን”ም እነዚህን ውጥኖች ይበልጥ እንደሚያሳካ ገልጸው፤ በተለይ ለምስራቁ የቱሪዝም መስመር እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንደሩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ቤኑና መንደር ይቻላልን በዓይናችን ያየንበት ነው ብለዋል። አካባቢው በጣም አስቸጋሪ የአየር ጠባይና መልክዓ ምድር እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህን በመቋቋም ውብ ገጽታ ያለውን መንደር እውን ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ሥዩም በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎችና የሬስቶራንቶች ጥራት ያለውና የደንበኛን ፍላጎት የሚያረካ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ወጥነት የላቸውም። ይህም በሀገሪቱ የቱሪስት ፍሰትና የገቢ ምንጭ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል ሲሉ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላትን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በተለይም የሆቴልና መሰል አገልግሎቶችን ማሳደግ ይገባል ያሉት አቶ ይታሰብ፤ ኢንስቲትዩትም ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።

ከመስተንግዶ ሠራተኞች የደንብ ልብስ አለባበስ ጀምሮ የሚጠቀሙት ቋንቋና መስተንግዶ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው ያሉት አቶ ይታሰብ፤ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥና መሠረተ ልማት በማሟላት ጥሩ መስተንግዶ በመስጠት የሀገርን ገጽታ መገንባትና የቱሪስት ቆይታ ጊዜ እንዲያራዘም ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የተሠሩና እየተሠሩ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ የሚታዩትን የቱሪስት መዳረሻዎች ውስንነት ችግር የሚቀርፉ ናቸው። ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው የቱሪስት ፍሰቱን የሚጨምሩ መሆናቸው ነው የገለጹት፡፡ ይህም የቱሪዝም ዘርፉ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You