አዲስ አበባ፡– የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ላይ ገዥ እና ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን በማካተት አዋጁ እንዲጸድቅ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሪል ስቴት ልማትና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ወቅት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ፤ የሀገር ግንባታ ሊሳካ የሚችለው ሁሉም አካል በነቂስ ሲሳተፍ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአዋጁ ላይ ለወደፊትም ማሻሻያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያመላከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ አዋጁ መርቀቅ የጀመረው ረጅም ጊዜ ቢሆንም አሁን ላይ ያሉ መሠረታዊ ለውጦችንና ማሻሻያዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የቤቶች ዘርፍ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ችግሮች ያሉበት እንደሆነና ችግሩ ጥልቅ በመሆኑ ከሀገር ውስጥ አልሚዎች በተጨማሪ የውጭ ባለሀብቶች ወደሀገር ውስጥ በመምጣት በቤት ልማት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ እሸቱ ተመስገን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ ላይ የሚታየውን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት ከተናጠል እንቅስቃሴ ይልቅ በጋራ በመሆን ለቤቶች ልማት ብድር የሚሰጡ ባንኮችን (mortgage bank) ለመመሥረት የሚያስችሉ አሠራሮች ሊኖሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢው እንዳሉት፤ ከመድረኩ ለአዋጁ ውጤታማነት ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች እንደተነሱና ረቂቅ አዋጁ ረጅም ጊዜ የሚያገለግል እንዲሆን ተጨማሪ አስተያየቶችን በጽሁፍ ማድረስ እንደሚቻል ገልጸው፤ ዘርፉን ለማሳደግ በዘርፉ ላይ የሚገኙ ተዋናዮች በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትም የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታ ሥርዓትን ዘመናዊና በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ፣ አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት፣ የሪል ስቴት ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት፣ ለዜጎች የቤት አቅርቦት እንዲሻሻል ለማድረግ እንዲሁም ልማቱና ግብይቱ እንዲቀላጠፍ ለማድረግ መሆኑን ተነግሯል፡፡
በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የቅድሚያ ሽያጭ የሚፈቀድ ሲሆን ይህም ለውጭ አልሚዎች የተከለከለ እንደሆነና በዝግ የባንክ ደብተር ተከፍቶ የሚቀመጥ ሲሆን፤ እንደአስፈላጊነቱ የሚለቀቅ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ተመላክቷል፡፡
በረቂቅ አዋጁ መሠረትም ለሪል ስቴት አልሚዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ፣ የቦታና የተናጠል ይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥ፣ የሪል ስቴት አልሚዎችና የቤት ገዥዎች ግዴታ፣ እንዲሁም ዋስትናንና ድጋፍ መስጠትን ያጠቃልላል፡፡
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ያስፈለገው የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ አስፈላጊነት የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማመቻቸት፣ የገበያ ግልጸኝነትን ለመፍጠር፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ሀብት ለመፍጠር፣ የከተሞችን ገቢና ልማት ለማሳደግ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት ግመታው በመደበኛነት በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ለንብረት ግብር፣ ለሽያጭና ግዥ፣ ለባንክ ብድር ማስያዣ፣ ለፍርድ ቤት ክርክር፣ ለውርስ፣ ለኢንሹራንስ፣ ለኪራይና ለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንደሚያገለግል በረቂቅ አዋጁ ተጠቅሷል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ረቂቅ አዋጁን በሚመለከት አስተያየትና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ በዘርፉ ላይ የፋይናንስ፣ የመሬት፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ አንስተው፤ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሄለን ደበበ አማካኝነት ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
በውይይቱ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር የሥራ ኃላፊዎች ፣ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ ቲንክታንክ ቡድን እና ሌሎችም በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም