በተኪ ሕክምና ግብዓት አቅርቦት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪን ማስቀረት ተችሏል

የሀገር ውስጥ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ አቅርቦት ሽፋኑ 36 በመቶ ደርሷል

አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያው ሩብ ዓመት በሀገር ውስጥ ሕክምና ግብዓት የምርት አቅርቦት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ። የሀገር ውስጥ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ አቅርቦት ሽፋኑ 36 በመቶ መድረሱም ተጠቁሟል፡፡

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትንተና እና ፖሊሲ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ አስፋው እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት የሕክምና ግብዓት የምርት አቅርቦቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና ተደራሽነቱን ለማስፋፋት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት የሀገር ውስጥ ሕክምና ግብዓት የምርት አቅርቦት በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ማስቀረት መቻሉን አመልክተው፤ ከውጭ የገባው የመድሃኒት እና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ መቀነሱንም አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓት አምራቾች የሚመረተው የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ አቅርቦት ስምንት በመቶ ብቻ ሽፋን እንደነበረው ገልጸው፤ በ2017 በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ አቅርቦት ሽፋኑን ወደ 36 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት በፓስታና በመኮረኒ 115 ሚሊዮን ዶላር፣ ከምግብ ዘይት 80 ሚሊዮን ዶላር፣ ከብቅል 63 ሚሊዮን ዶላር ማዳን መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ከውጭ የገቡት የምግብና መጠጥ ምርቶች ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ44 በመቶ እንደሚቀንስ አመላክተዋል፡፡

የጫማ የውጭ ምንዛሬን በሚመለከት 51 ሚሊዮን ዶላር ማዳን የተቻለ ሲሆን፤ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25 ነጥብ 63 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል አብራርተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ መደረጉ ለተኪ ምርት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You