“የኢትዮጵያ የመልማት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዓባይ ተፋሰስና ወደ ትልቁ ናይል በሚገቡ ወንዞቻችን ነው” – ፕሮፌሰር መኮንን አያና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ የማደግና ያለማደግ፤ የመልማትና ያለመልማት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዓባይ ተፋሰስና ወደ ትልቁ ናይል በሚገቡ ወንዞቻችን እንደሆነ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር መኮንን አያና አስታወቁ።

ፕሮፌሰር መኮንን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስ ታወቁት፤ ግብጻውያን «የናይል ውሃ የመኖርና ያለመኖር እጣ ፈንታችንን የሚወስን ነው» እንደሚሉት፤ የሀገራችን የማደግና ያለማደግ፤ የመልማትና ያለመልማት እጣ ፈንታም የሚወሰነው የሀገሪቱ 70 በመቶ የውሃ እና ሌሎች እምቅ ሀብቶች ባሉበት በዓባይ ተፋሰስ እና ወደ ትልቁ ናይል በሚገቡ ወንዞች እና በወንዞቹ አካባቢዎች ነው።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ የውሃ ሀብት በባህሪው ከተፈጥሮ ፤ ከአየር ንብረት ለውጥና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች እየቀነሰ የሚመጣ ነው። በመሆኑም ይህንን ከፍተኛ ጥቅም ያለውና ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባ ሀብት በአግባቡ እያበለጸጉ መጠቀም ይጠበቃል።

አሁን እንደሀገር የያዝናቸው የልማት አቅዶች እውን ሊሆኑ የሚችሉት ውሃን ብቻ ሳይሆን ከውሃ የሚገኘውንም የኤሌክትሪክ ሃይል በአግባቡ በማልማት መጠቀም ሲቻል ነው ያሉት ተመራማሪው፤ ዛሬ በስፋት እየተሠሩ ያሉ ከተሞችን የማዘመን ሥራዎችም ቢሆኑ በቂ የኤሌክትሪክ ሃይል አና በቂ ውሃ የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል።

የውሃ ሀብትን መጠቀም፤ በተለይም ትልልቅ ወንዞችን እየገደቡ ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ማመንጨት መቻል ለኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሉዓላዊነትም መጠበቅ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ፕሮፌሰር መኮንን ገልጸዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ ግብጻውያን የህዳሴው ግድብ እውን መሆን እነሱ ላይ ምንም ተጽእኖ እንደማያመጣ ይልቁንም ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ ከጎርፍ አደጋ እንደሚታደጋቸው ቢያውቁም፤ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም።

ምክንያታቸው ደግሞ ለዘመናት የዘለቁበትን የበላይነታቸውን የሚያሳጣና ኢትዮጵያን ተከትለው ሌሎች ሀገራት ይጠቅመናል የሚሉትን መሥራት ጀምረው የግብጻውያን የበላይነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከቱታል በሚል ፍራቻ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዛሬ በመጠናቀቅ ላይ ያለው የህዳሴው ግድብ ምንም አይነት ነገር ርዳታ ሳይጠየቅ ሙሉ ለሙሉ የራስ አቅምን በመጠቀም እውን ለማድረግ ወደ ሥራ መገባቱ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር ብለዋል። የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በብዙ መንገድ እንደተፈተኑበት ሁሉ ውጤቱም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሕዳሴ ግድቡ ከምንም በላይ በሌሎች ወንዞች ላይ ለሚከናወኑ ግድቦችም ይሁን ለሌሎች ትልቅ አቅም የሚጠይቁ ፕሮጀክቶች ይቻላልን ያቀዳጀ ነው ያሉት ተመራማሪው፣ ከዚህ በኋላ ለሚከናወነ ሥራዎችም አቅም የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተደረጉ የስምምነት ሂደቶች እንደ አጠቃላይም በቀጣይ በሌሎች ጉዳዮች በሚካሄዱ ሀገራዊ ስምምነቶች ላይ ምን አይነት ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ትምህርት የተወሰደባቸው እንደሆኑም አስታውቀዋል ።

ከፕሮፌሰር መኮንን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ሙሉቃል በገጽ 6/7 ወቅታዊ አምዳችን ላይ ያገኙታል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ህዳር 5/2017 ዓ.ም

Recommended For You