“የኮሪደር ልማት ዋነኛ ግብ ለትውልድ የተሻለ ከተማና ሀገር መገንባት ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፦ የኮሪደር ልማት ሥራ ዋነኛ ግብ ለትውልድ የተሻለ ከተማና ሀገር መገንባት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን ሁለተኛ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ አፈፃፀም ገምግመዋል።

በግምገማ መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን የሚያስተባብሩ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኮሪደር ልማት ዋነኛ ግብ የተሻለ ከተማና ሀገርን ለትውልድ መገንባት መሆኑን ተናግረው፤ ትውልዱን ለከተሜነት እድገት ማዘጋጀት ስለመሆኑም ጨምረው ገልጸዋል።

ከተሜነት በፍጥነት እያደገ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ ትውልዱ አሁን የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን ጠብቆ በአግባቡ እንዲጠቀም ከወዲሁ መሥራት እንደሚገባም ነው ያነሱት።

የኮሪደር ልማት ሥራዎች የከተማዋ አመራሮች የሕዝብን ችግር ቀረብ ብለው እንዲመለከቱና ሰው ተኮር በሆነ አግባብ ለመፍትሄው እንዲሠሩ እድል የፈጠረ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ከተማና ሀገርን የመገንባቱ ሥራ በአንድ ጊዜ ተከናውኖ የማይጠናቀቅና በትውልድ ቅብብሎሽ የሚከናወን መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የሚከናወኑ ሥራዎች ኢትዮጵያ በቀጣይ ለመድረስ ላቀደችው የእድገት ርዕይ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ገልጸውም፤ ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

አመራሩ የኮሪደር ልማት ሥራውን በሚመለከት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ያከናወናቸውን ሥራዎች አድንቀው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች በሁለተኛው ምዕራፍ ላይም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቀጣይ የልማት ሥራዎቹ በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት እንዲጠናቀቁ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በመዲናዋ እየተከናወኑ ያሉ የሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ሥራዎች፣ የአረንጓዴ ሥፍራ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ መኪና ማቆሚያ፣ ብስክሌት መንገድ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን ጨምሮ ሌሎች ከተማዋን የሚያዘመኑና ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የልማት ሥራዎች መሆናቸውም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ያለበትን ሁኔታ ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን መገምገማቸውን አስፍረዋል።

ከንቲባ አዳነች 2ኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጋር በጋራ መገምገማቸውን ጠቁመው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡን አቅጣጫ 2ኛውን ዙር የኮሪደር ልማት በፍጥነትና በጥራት እናከናውናለን ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራሩን በማበረታታት ለልማት እየተባበሩ ያሉ የከተማዋን ሕዝብ፣ ሥራ ተቋራጮች፣ ባለሀብቶችን እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ማመስገናቸውንም ከንቲባዋ ገልፀዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You