– ከዓባይ ግድብ ከአንድ ሺህ 443 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል መንጭቷል
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በሰዓት ስድስት ሺህ 456 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ሰዓት ኢነርጂ መመረቱን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።በሩብ ዓመቱ ከዓባይ ግድብ አንድ ሺህ 443 ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት ኃይል መመንጨቱ ተመላክቷል፡፡
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ትንተናና ፖሊሲ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ አስፋው እንደገለጹት፤ በ2017 በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰዓት ስድስት ሺህ 456 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ኢነርጂ ተመርቷል፡፡
በ2017 በጀት የመጀመሪያ ሶስት ወራት በሰዓት የተመረተው ኢነርጂ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአንድ ሺህ 706 ነጥብ 25 ጊጋ ዋት ኢነርጂ እንደሚበልጥ አስረድተዋል።
ጠቅላላ በሰዓት ከተመረተው ስድስት ሺህ 456 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ኢነርጂ አራት ሺህ 300 ነጥብ 58 ጊጋ ዋት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መተላለፉን አስታውቀዋል። በሰዓት 305 ነጥብ 34 ጊጋ ዋት ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መተላለፉን እና ለዳታ ማዕከል 886 ነጥብ 74 ጊጋ ዋት ሰዓት መተላለፉን ጨምረው ገልጸዋል። የመስመር ዝርጋታን በመሚለከትም በሩብ ዓመቱ 437 ነጥብ 43 ኪሎ ሜትር መስመር መዘርጋቱን አስረድተዋል።
በሩብ ዓመቱ ከዓባይ ግድብ ብቻ አንድ ሺህ 443 ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት ኃይል የመነጨ ሲሆን፤ የዓባይ ግድብ የፕሮጀክት አፈጻጸምም 97 ነጥብ ስድስት በመቶ መድረሱን አመላክተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የውጭ ኢንቨስትሮች እምብዛም ተሳትፎ በማያደርጉበት በኢነርጂ ዘርፍ ለመሳተፍ 60 ሚሊዮን ዶላር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ኅዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም