‹‹ህብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሀገራዊ መግባባቱ አስኳል ነው›› – አቶ አገኘሁ ተሻገር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ

አዲስ አበባ፡- ብዝኃ ማንነት ላላት ኢትዮጵያ ህብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሀገራዊ መግባባቱ አስኳል ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህዳር 29 “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል፡፡ በመሪ ሃሳቡና ህብረ ብሔሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚዲያ አመራሮችና ለጋዜጠኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡

በሥልጠና ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር እንደገለጹት፤ እንደ ኢትዮጵያ ብዝኃ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና አመላካከት ላላት ሀገር ህብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሀገራዊ መግባባቱ አስኳል ነው። በዓሉ የኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት ዕውቅና ከመስጠት በላይ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትንና ሰላም ለማጽናት ይረዳል፡፡

የፌዴራል ሥርዓትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባትና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመነጋገርና በመመካከር በመፍታት ህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አገኘሁ ገለጻ፤ በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ዕርስ በርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ ነው፡፡ እንዲሁም የክልሎች መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ የሚያደርግ ነው፡፡

የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍፃሜ ለማድረስ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ በአስተናጋጅ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችና ታሪካዊ ቦታዎች እንዲተዋወቁ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

ህብረብሔራዊ አንድነት ያለ ሀገራዊ መግባባት አይጸናም ያሉት አፈ ጉባዔው፤ ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት መሠረቱ ነው፡፡ ሀገራዊ መግባባት በውይይት፣ በምክክር፣ በሰጥቶ መቀበል የሚመጣና ለጋራ እሴቶች ክብርና ዋጋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወል ትርክቶች ተሰናስነውና ተዋሕደው ሲፈሱ ህብረብሔራዊ አንድነትን እንደሚገነቡ አመልክተው፤ በአንፃሩ የእኔ ባህል፣ ታሪክ፣ ሃይማኖት በአጠቃላይ የእኔ ማንነት ብቻ የበላይ ይሁን የሚለው ነጠላ ትርክት ህብረ ብሔራዊ አንድነት እውን እንዳይሆን ያደርጋል ብለዋል፡፡

አንድነቷ ያልተጠበቀና ሰላሟ ያልሰፈነ ሀገር ልማቷን ማሳካት አትችልም ያሉት አቶ አገኘሁ፤ በዓሉ የጋራ ታሪኮችንና እሴቶችን የምናሳይበት፣ የሕዝቦች የኑሮ መስተጋብር የሚበለጽግበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

19ኛው የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በየደረጃው ሲከበር የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር እንዲረጋገጥ በማድረግ እንዲሁም የሀገራችን ሰላምና አንድነት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ በትኩረት የምንሠራበት ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍትሐዊነት፣ ህብረብሔራዊና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ሲከበር በሕዝቦች መካከል በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You