የምናገኘው ሰው ሁሉ የሚነግረን እየተቸገረ እንደሚኖር ነው። ጎዳና ተዳዳሪው የዳቦ መግዣ ማጣቱን ይነግረ ናል። በቪላ ቤት የሚኖረው መኪናውን ለመቀየር የተወሰነ ገንዘብ እንዳጠረው ሹክ ይለናል። ሥራ የሌለው የሥራ እድል ችግር እንደገጠመው ሲያማርር፣ ሰምተን ሳናበቃ ስራ ያለው ጋር ስንሄድ ደግሞ ደመወዙ ለኑሮ ውጥንቅጥ አልበቃ ብሎት መላ እንደጠፋው ያወራል።
ድሃው መተዳደሪያ ገንዘብ ቸግሮት ሀብታሙ ደግሞ እንደጠበቀው ባለማ ትረፉ የኪሳራ ችግር ውስጥ ነኝ ይላል። እነዚህን ችግሮች ሰምተን ግራ ስንጋባ በህይወት መስመር ከአንደኛው ጫፍ እነዚህን ሁሉ ሁነቶች ፉርሽ ያደረገ ሰው እናገኛለን። ለዘመናት የንግድ ማዕከል ሆና ቆይታለች። ከመሃል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ አገራት ጋር በንግድ መንገዶች ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባህር ወደቦች አማካኝነት ትገናኝ ነበር፤ሐረር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢንስቲትዩት የሚገኘው “ዋግነር ዘ ዲክሽነሪ ኦፍ ኢትዮጵያን ባዮግራፊ” በመጀመሪያው ገጽ ላይ እንደሚለው የተለያዩ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች የሚኖሩባትን ሐረር “እኛ እርስ በእርስ ስንናከስ ይህች የብዙ ዘር እና ሃይማኖት ውህድ የሆነች ከተማ ግን እርስ በእርሱ ከሚበላላው ጅብ ጋር ሳይቀር ተግባብቶ የሚኖርባት ህዝብ ያለባት ከተማ ናት። ” ሲል አሞካሽቷታል። እኛም ለሥራ በሄድነበት ከዚህ ታሪካዊ ከተማ ያገኘነውን ወጣት ሥራ ፈጣሪው እናስተዋውቃችሁ።
አቶ ካሊድ ሳቢት ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው ሐረር ልዩ ስሙ አስመዲን በሪ በሚባለው አካባቢ ነው። 35 ዓመት ሞልቶታል። እጅግ በከፋ ድህነት ባለበት ቤተሰብ ወስጥ ያደገው የዛሬው ወጣት ስራ ፈጣሪ እንግዳችን አቶ ካሊድ ሳቢት። አሁን የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ ያልወጣው ዳገት፣ ያልወረደው ቁልቁለት፣ ያልተሻገረው ወንዝ የለም። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተወለደው ስራ ፈጣሪው ካሊድ የሀብት ማማ ላይ ለመውጣት ከድህነት ጋር ግብግብ በመግጠም፤ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ነው።
ትምህርትና ፈታኝ ጊዜ
አቶ ካሊድ አንደኛም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል ጥሩ ተማሪ በሚባል ደረጃ የሚገኝ እንደነበር አስታውሶ ከቀለም ትምህርቱ ባሻገር በትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ሳይቀር እውቅና የተሰጠው ሥነ ምግባር ያለው ተማሪም እንደነበር ይናገራል።
በችግር ሳቢያ በቀለም ትምህርት ከ10ኛ ክፍል በላይ መሄድ አልቻለም። ስለዚህም የትምህርት ዓለሙን በዚህ ተሰናብቶ ስራ ፍለጋ ጉዞ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ፤ ህይወት ሌላ መስመር ያዘች፤ አዱኛ እንዲህ ናት!
ሌላ መልክ የያዘው የህይወት ገጽ ለወጣቱ ካሊድ ከባድ ነበር። ከድህነት ጋር ፊት ለፊት ገጠመ። የሰው ፊት ማየትና መለመን እጅግ ፈታኝ እና አስከፊ መሆኑንም የሚናገረው ካሊድ፤ ከትውልድ ከተማው ያስወጣውን ድህነት አምልጦ የራስ ሀብት አፍርቶ ለቤተሰብም አለኝታ መሆን አለብኝ የሚለውን ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት ብርቱ ፍላጎት ታክሎበት ዘመቻ ሥራ ፍለጋ ተያያዘው።
ህይወት በገጠመኝ የተሞላች ናት፤ የሚለው ወጣቱ አዲስ አበባ በአንዲት አነስተኛ የህንፃ መሳሪያ መሸጫ ሱቅ በሦስት መቶ ብር ተቀጥሮ ለአንድ ዓመት ሠራ። ያኔ ታዲያ የስራ ምንነትን በማወቅም ሆነ ልምድ በመቅሰም በተጨማሪም የወደፊት ራዕዩን በመያዝ ከሸገር ወደ ትውልድ ከተማው ሐረር ተመለሰ።
ጥንስስ
ካሊድ አዲስ አበባ ተቀጥሮ በሚሰራበት ሰዓት እንዴት ከትንሽ ስራ ተነስቶ ህይወትን መለወጥ እንደሚቻል እንዲሁም ከፍተኛ ቦታ እንደሚደረስ በቀሰመው እውቀት መሰረት የተለያዩ የስራ አማራጮችን ማየት ተያያዘው።
በተለይም በጥቂት የመንቀሳቀሻ ገንዘብ ሊጀመር የሚችል ሥራ ማጤን የተያያዘው ወጣቱ በሐረር ከተማ ስልክ እንዲህ እንደ አሁኑ ባልነበረበት ሰዓት የከተማዋ ህብረተሰብ ይቸገር ነበር። ይህንን ችግር የተረዳው ሳቢት አዲስ አበባ ተቀጥሮ በሚሰራበት ወቅት ባስቀመጣት ጥቂት ገንዘብ ስልክ ማስደወያ ወይም ቴሌ ሴንተር ከፈተ። በ5000 ብር የተጀመረው የስልክ ማስደወያ “ቴሌ ሴንተር” እየሰራ እቁብ በመግባት ወደ ሌላ ስራ ተሸጋገረ።
የእርሱ መነሻ ስራዎች በሙሉ በከተማዋ የሚናቁ ስራዎች እንደሆኑ የሚናገረው ወጣት ካሊድ ሳቢት ሁለተኛው የስራ ዘርፍ ያደረገው “ጌም” ማጫወት ነበር። ተማሪዎች ወደሚገኙበት አካባቢ “ጌም” ማጫወቻ ሱቅ የከፈተው ሳቢት ከስራ ባሻገር ተማሪዎች ለሱስ ተጠቂ እንዳይሆኑ በተለይ በከተማ እንደ ቀላል የሚቃመውን ጫት እንዳይቅሙ ረድቷቸዋል።
ምንም ዓይነት ሱስ እንደሌለበት የሚናገረው ወጣት ሳቢት ጌም እያጫወተ የሚያገኘውን ገንዘብ በመሰብሰብ እና በመቆጠብ ለተሻለ ስራ ዝግጅቱን ተያያዘው እናም የተወሰነ ገንዘብ ካጠራቀመ በኋላ ከወዳጅ ዘመድ ጥቂት ገንዘብ በመበደር አዲስ ስራ ጀመረ። የመኪና ማሰልጠኛ ተቋምም ከፈተ። በ500ሺ ብር የተከፈተው ይህ ማሰልጠኛ ለብዙዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ወጣቱም የልፋቱን ፍሬ ያየበት የሥራ ዘርፍም ነበር።
ቤተሰብ
“አሁን ላላሁበት ህይወት ከራሴ ጥረት እና ትጋት ባሻገር የቤተሰቤ ድጋፍ ከፍ ያለ ነበር። በተለይ ባለቤቴ ወይዘሮ ሀጀር አደም ምክርና ድጋፍ ከፍ ያለ ነበር” የሚለው ወጣት ካሊድ ልጆቹም ተጨማሪ የብርታቱ ምንጮች እንደሆኑ ይናገራል።
የሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ስራ መስራት የሚጀመረው ከቤተሰብ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው በጥሩ ሥነምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ቀዳሚውን ኃላፊነት ይወስዳሉ። ፈላስፋው “ሕጻን ልጅ ከሰጣችሁኝ በፈለግሁት መንገድ ቀርጬ አሳያችኋለሁ” እንዳለው የሰውን ልጅ ባህሪ በሚፈልጉት መንገድ ለመቅረጽ የሚቀለው በሕጻንነት ስለሆነ በቤተሰብ ደረጃ ልጆችን ገርቶ ለሀገርና ለወገን ራሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ አድርጎ ማሳደግ ይቻላል ይላል።
“እኔ እንደተቸገርኩት ልጆቼ እንዲ ቸገሩ አልፈልግም፤ በልጆቼ በእያንዳን ዳቸው ስም በባንክ እቆጥብላቸዋለው። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም። ከሚቀመጠው ገንዘብ ባሻገር የስራ ባህልንም ማውረስ አገርን እና ህዝብን መውደድ ማስተማርም ዋነኛው ስራዬ ነው። ” ይላል ካሊድ። ለልጆች ከሚወርሱት ሀብት በፊት መልካም ስነ ምግባር የስራ ባህልና አገርን መውደድ ማስተማር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ከዚያ ሲያድጉ ስራ ፈጣሪዎች ለወገን የሚያስቡ ግብርን በአግባቡ የሚከፍሉ ብቁ ዜጋ እንደሚሆኑ ይገልጻል።
ንዋይ
ከጥቂት ዓመታት በፊት የሦስት መቶ ብር ወርሃዊ ደሞዝተኛ የነበረ ሲሆን፤ አምስት ሚሊዮን ካፒታል አስመዝግቧል። በጥቂት መንቀሳቀሻ የተጀመረው ስራ አሁን ካሊድ የመኪና ማሰልጠኛ ተቋም በመሆን ከ15 በላይ ቀላል እና ከባድ መኪኖች ባለቤት ሆኗል።
ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ስራ የጀመረው አቶ ካሊድ በአሁኑ ሰዓት ለ15 ሰዎች ቋሚ የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ከ15 ለሚጠጉ ደግሞ ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል። በቀጣይም የሚያቅዳቸው የስራ ዘርፎች እንዳሉት ይናገራል።
እቅድ
ወጣቱ ስራ ፈጣሪ ካሊድ ሐረር የንግድ ከተማ እንደሆነች አስታውሶ ይህች ታላቅ ታሪካዊ እና የንግድ ከተማ ይህ ነው የሚባል ለሁሉም የእድሜ ክልል የሚመች መዝናኛ ስፍራ እንደሌላት መታዘቡን ይናገራል። ታዲያ ማህበረሰቡን በመጥቀም ነው ነጋዴውም መጠቀም ያለበት የሚለው፤ ለህብረተሰቡ የሚሆን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚዝናኑበት ሁሉን አቀፍ መዝናኛ የመክፈት ምኞቱ አለው። የክልሉ መንግስት ይህንን ራዕዬን ተመልክቶ ለዚህ አገልግሎት የሚውል ቦታ ቢሰጠው ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስራ እድል መፍጠር ውጥን አለው።
ምክር
ሀሜት፣ አሉባልታ፣ ምቀኝነት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ ድብቅነት፣ ውሸት፣ ማታለል፣ ሙሰኝነት፣ አድሏዊነት፣ ማግለል፣ ማስመሰል፣ የሀገር ፍቅር ማጣት፣ ለሰላምም ሆነ ለዕድገት ፀር ስለሆኑ ከእኛ አልፈው ወደ ልጆቻችን እንዳይሻገሩ መስራት እንደሚያስፈልግ ካሊድ ይመክራል። በተጨማሪም ለዕውነት መወገን፣ ችግሮቻችንን በግልጽ ውይይት መፍታት፣ የምናውቀውን ከመደበቅ ወጥተን ላላወቀው ማሳወቅ፣ ይገባናል ባይ ነው፡፡ እንደ አቶ ካሊድ እምነት ጥፋታችንን ሳንሸፋፍን አምነን ለማረም መስራት፣ መጥላትም መጥፎ ባህሪን ተግባርን እንጅ ዘርን ወይም ቋንቋን አለማድረግ፣ መጥፎውን የማውገዝ ወይም የመቃወም ጥሩውን የማወደስ ወይም የመደገፍ ባህል ማዳበር፣ ለሰላማችንም ሆነ ለዕድገታችን አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው።
የሞራል እሴቶች፣ ወጎች እና ባህሎች ለዕድገት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለአንድነት መሰረት እንዲሆኑ መጥፎውን በማረም መልካሙን ማጎልበት እንደሚያስፈልግም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ ካሊድ ይናገራል። “እነዚህን እያደረግን በመልካም ባህርይ ላይ ትጋት ጨምረን ማንኛውም ሰው ከአሰበው የሀብት ማማ ላይ መውጣት ይችላል። ለዚህም እኔ አንዱ ማሳያ ነኝ” ይላል። የዝግጅት ክፍላችንም የወጣቱ ካሊድ ምኞት እንዲሳካ የሚመለከታቸው አካላት ሊያግዙት እንደሚገባ ለመጠቆም እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
አብርሃም ተወልደ