የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር ለኢኮኖሚ መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው

አዲስ አበባ፡- የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የፈጠራ ዘርፉን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ከዓለም አቀፉ የአዕምሯዊ ንብረት ድርጅት ጋር በመተባባር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የአዕምሯዊ ንብረት ሳምንት የማጠቃለያ መርሃ ግብር ትናንት ተካሂዷል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ፈጠራ ዘርፍ መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ መጠናከር የውጭ ኢንቨስትመንት ከማሳደግ ጎን ለጎን በየዘርፉ ፈጠራ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግና ለፈጠራ እንዲነሳሱ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በሀገሪቱ በቅርቡ የተጀመረው ስታርት አፕ ከፍተኛ የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ የሚሻ ነው ያሉት አቶ ወልዱ፤ በዚህ የሚሰማሩ አካላትም የባለቤትነት መብቱ አግኝተው በፍጥነት የፋይናንስ ድጋፍ የሚያገኙበት እድል እየተመቻቸ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የአእምሯዊ ንብረት ሳምንት የተዘጋጀው ያለው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

እንደ አቶ ወልዱ ገለጻ፤ በሳምንቱ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት፣ ለምርምር ተቋማትና ለዩኒቨርሲቲዎች የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኢኮኖሚ የገነቡ ሀገራት በአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡

አቶ ወልዱ፤ በተፈጥሮ ሀብት ብቻ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ መወዳደር አይቻልም ያሉ ሲሆን፤ የአዕምሯዊ ንብረት በማይዳሰስ ሀብት ውስጥ ሆኖ ከፍተኛ ልዩነት እየፈጠረ ያለ ዘርፍ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሕግ ማሻሻያዎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መፈረም፣የዲጂታል አገልግሎት ማስፋት፣ የግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ይበልጥ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ድርጅት አባል ከሆነች በርካታ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም የብዙ ስምምነቶች ፈራሚ እንዳልነበረች ጠቅሰው፤ ስምምነቱን ባለመፈረሟ የሀገሪቱ የአዕምሮ ንብረት ውጤቶች በዓለም አቀፍ ዙሪያ ጥበቃ ሳይደረግለት መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በሳምንቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አጽድቋል ያሉ ሲሆን፤ በቀጣይም የሀገሪቱን አዕምሮ ንብረት ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ስምምነቶች ይፈረማል፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You