ከተሞች በእቅድ ሊመሩ ይገባል

አዲስ አበባ፦ ከተሞቻችን በእቅድ ሊመሩ ይገባል ሲሉ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የከተማና መሠረተ ልማት ተመራማሪ አቶ ተፈራ በዬራ አስታወቁ።

ተመራማሪው አቶ ተፈራ በዬራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዋነኛው የሀገራችን ችግር ከተሞች እየቀደሙን እኛ ከኋላ እየተከተልን ስንሄድ ቆይተናል፡፡ከተሞች በህገወጥነት ወደጎንዮሽ እየተስፋፉ ሲሄዱ እየተከተልን ከተማ ስንል ቆይተናል። ከዚህ አካሄድ ተላቀን ዘመን ተሻጋሪና ውብ ከተሞችን ለመፍጠር ቀድሞ አስቦና አቅዶ መምራት ተገቢ ነው።

የከተማና የገጠር ትስስርን በመሰረተ ልማት አስቀድሞ በማቀድ፤ የመሬት አጠቃቀማችን ላይ የትኛው አካባቢ ለየትኛው መዋል እንደሚገባው በመለየትና ቀድሞ በማቀድ የሚመራ ከሆነ በሚፈለገው መልኩ ከተሞችን ማሳደግ ይቻላል ያሉት ተመራማሪው፤ በገጠርና በከተማ ያለው ትስስር በተቀናጀ መልኩ የሚመራ ከሆነ ከተሞቻችን የሚመሩን ሳይሆን እኛ ወደ ምንፈልገው ደረጃ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ከተሞቻችንን መምራትና ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ከተማ ዞሮ ዞሮ ወደ ገጠር እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ ቀድመን ገጠርን የምንሰራ ከሆነ፤ ሰዎች መንገድ ዳር መጥተው እንዳይሰፍሩ አስቀድሞ በእቅድ መምራት ያስፈልጋል። ከተሞቻችንን ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ወደ ምንፈልገው ደረጃ መምራትና ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

በሀገራችን እንደ ችግር የሚታየው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖሩ ነው ሲሉም የትኛው አካባቢ ለየትኛው መዋል እንዳለበት የሚያሳይ ለቤት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድ፣ ለአምራች ኢንዱስትሪና ለአረንጓዴ ስፍራዎች የሚለውን ቀድሞ ማቀድ እና ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አሁን በኮሪደር ልማቱ የሚታዩ ማስተካከያዎች እና ከተማን እንደገና የማደስ ስራዎች ቀድሞ የማቀድ ችግሮች መሆናቸውን አውስተው፤ ከተሞቻችን በእቅድ እና በእቅድ ብቻ እንዲመሩ ማድረግ ከተቻለ በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችንም አስቀድሞ መፍታት እንደሚቻል አቶ ተፈሪ አስገንዝበዋል።

አረንጓዴ ስፍራዎች የከተማ ሳንባ በመሆናቸው በእቅድ መካተት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ሁሉንም አካባቢ በፎቅ የሚሞላ ከሆነ፤ ከተማ ሳንባ የሚያጣ ይሆናል። በመሆኑም ለአረንጓዴ ስፍራዎችም ጭምር አስቀድሞ በማቀድ ከተሞችን በእቅድ መምራት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተፈሪ በሰጡት ምክረ ሀሳብ እንዳመላከቱት፤ የሀገራችን የከተሞች እድገት አስፈላጊውን መሰረተ ልማት አሟልተው በእቅድ እንዲመሩ ከወዲሁ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ላይ መሰራት አለበት።

በሀገራችን የምንፈልገውን የከተማ ደረጃ ለማምጣት የኮሪደር ልማት ተጀምሯል። ይህ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። አሁን ባለንበት የከተማ ደረጃ መቀጠል አይቻልም። የህዝብ ቁጥሩ እየሰፋና እያደገ ነው። ከፍተኛ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰት አለ። ይህንንም ችግር ለመቀነስ በእያንዳንዱ ከተማ ላይ መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ለምሳሌ በመዲናዋ የሚታየው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር በእያንዳንዱ ከተማ አስፈላጊ መሰረተ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ሚዛናዊ እየሆነ የሚሄድ መሆኑን ገልጸው፤ የተመጣጠነ የከተማ እድገት ለማምጣት የገጠር እና የከተማ ተስስሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ቀድመው ባደጉ ከተሞች ኮሪደር ልማት ላይ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም ቀጣይነት ያለው ውይይት አስፈላጊ ነው። የህብረተሰቡን ደጋፊነት ለማስቀጠል ቀደም ሲል የተሰሩት ስራዎች ያስገኙትን ውጤቶች ለህብረተሰቡ የማስገንዘብ ስራ መስራትም ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም

Recommended For You