እስራኤል ከአሜሪካ 25 “ኤፍ-15” የውጊያ ጄቶችን ልትገዛ ነው

እስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ የቀጣዩ ትውልድ “ኤፍ-15” ተዋጊ ጄት ባለቤት ለመሆን ተቃርባለች። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር 25 “ኤፍ -15” ጄቶችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል።የቦይንግ ዘመኑን የዋጁትና የቀጣዩ ትውልድ “ኤፍ-15ጄቶች” “ኤፍ-15ኢኤክስ” የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡት ጄቶች ግዥ የአሜሪካ ኮንግረንስ በዚህ አመት ለእስራኤል ያጸደቀው ድጋፍ አካል መሆኑንም ሚኒስቴሩ በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ አመላክቷል።የጦር ጄቶቹ የእስራኤል የአየር ሃይል በመካከለኛው ምስራቅ ቀዳሚነቱን ያስቀጥላሉ የተባለ ሲሆን፤ አሁንም ሆነ ወደፊት በቀጣናው ለሚገጥሙ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዙም ተገልጿል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ ቦይንግ “ኤፍ -15” ጄቶቹን ለእስራኤል ከ2031 ጀምሮ ማቅረብ ይጀምራል፤ በየአመቱም ከአራት እስከ ስድስት ጄቶችን አጠናቆ ያስረክባል። “ኤፍ-15 ጄቶቹ በዚህ አመት ከገዛናቸውና (በሊባኖስና ጋዛ) ጦርነት ውጤታማነታቸውን ካሳዩን ኤፍ-35 ጄቶች ጋር ሲጣመሩ የእስራኤልን የአየር ሃይል አቅምና ተደራሽነት ይበልጥ ያጠናክሩታል” ብለዋል የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ኢያል ዛሚር።

የቦይንግ “ኤፍ-15” ጄቶች (“ኤፍ-15ኢኤክስ”) በሚሸከሙት ክብደት፣ በሚያካልሉት ርቀትና በፍጥነ ታቸው የዘመኑ የመጨረሻ ቴክኖሎጂ ውጤት ናቸው ተብሏል። ለየትኛውም የውጊያ አውሮፕላን ሽፋን የሚሰጡ የጀርባ አጥንት ይሆናሉም ነው ያለው ቦይንግ በድረገጹ ባሰፈረው መግለጫ።

ኤፍ-15 ኢኤክስ”እስከ 13 ሺህ 300 ኪሎግራም የሚመዝኑ የጦር መሳሪያዎችን የሚይዝ፤12 መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን እንደሚሸከም፤በሰአት 3 ሺህ 581 ኪሎ ሜትሮችን እንደሚጓዝ፤ ዘመናዊ ራዳር፣ ሴንሰሮች እና የኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች የተገጠሙለት መሆኑን ጠቅሶ አል ዐይን ዘግቧል፡፡

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You