ኢትዮጵያ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች የሥራ አስፈጻሚ አባል መሆኗ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ያግዛታል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች በሥራ አስፈጻማ ኮሚቴ በአባልነት መመረጧ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በዚምባዌ ቪክቶሪያ በተካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ጉባዔ ላይ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆና ተመርጣለች፡፡

አቶ ደሳለኝ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች የሥራ አስፈጻሚ አባል መሆኗ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ ያግዛታል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሌሎች አባል ሀገራት የዜጎቻቸውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ በሕገ መንግሥት ትርጉም የደረሱበትን ደረጃ ለማወቅና ለመተግበር ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻችላታልም ነው ያሉት፡፡

በነበረው መድረክ ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ዓለም አቀፍ ተሞክሯን የምታካፍልበት መድረክ በአዲስ አበባ ይዘጋጃል ያሉት አቶ ደሳለኝ፤ በመድረኩም የ48 አባል ሀገራት የአጣሪ ጉባዔው ፕሬዚዳንቶችና ከአህጉሪቱ ውጪ የታዛቢነት ሚና ያላቸው ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚመጡ እንግዶች ይሳተፋሉ፡፡

አቶ ደሳለኝ አክለውም፤ ኢትዮጵያ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧ በአፍሪካና በዓለም ያለው ተደማጭነቷን ለማሳደግ፤ የጥናትና ምርምር ተቋማትም ተሳትፏቸው እንዲጨምር እንዲሁም የዜጎችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የሚረዳ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ጉባኤው በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያም ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት የሚያበቋት መስፈርቶችን በማሟላት እና የድርሻዋን በመወጣት ተገቢውን አስተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

መድረኩ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ለማስተዋወቅ እድል የተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አጣሪ ጉባዔውም በተለያዩ ሀገራት በሚካሄደው ኮንፈረንስ በመሳተፍ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ሥርዓትን ለማጠናከር የሚረዱ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በሕገ መንግሥታዊ ፍትህ መስክ የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታይ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እ.ኤ.አ ማርች 15/2017 ጀምሮ በሥራ ላይ ያለና 48 የአፍሪካ ሀገራትን ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You