የዚምባቡዌ መንግሥት ፖሊሶች ለሥራ ሲሠማሩ ሞባይል ስልክ እንዳይዙና እንዳይጠቀሙ አገደ።
ሁሉም ፖሊሶች ለሥራ ሲሠማሩ ስልካቸውን ለበላይ ኃላፊዎቻቸው አስረክበው መውጣት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
ለፖሊሶች ተልኳል የተባለው የማሳሰቢያ መልዕክት መንስኤ እና ዓላማው ግን አልተጠቀሰም።
ከእረፍት ሰዓት ውጪ ፖሊሶች ሞባይል ስልካቸውን መጠቀም እንዳይችሉ የተላለፈው ውሳኔ ሙስናን ለመቀነስ ያለመ ሊሆን እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሁለት የትራፊክ ፖሊሶች ከሰሞኑ አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻዎችን እና ሞተሮችን እያስቆሙ ከአሽከርካሪዎች ጉቦ ሲቀበሉ የሚያሳይ ምስል ተለቋል።
ቪዲዮው ወትሮውንም በሙስና የተዘፈቁ ናቸው የሚባልላቸውን የሀገሪቱን የትራፊክ ፖሊሶች ገመና የገለጠ ነው በሚል መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የዚምባቡዌ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፖል ንያቲ ሁለቱ ጉቦ ሲቀበሉ የታዩ የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
“ለፖሊስ አገልግሎት የማይመጥኑ” ሲሉ የገለጿቸውን ባልደረቦቻቸው አስተዳደራዊ ቅጣትና የወንጀል ክስ እንደሚጠብቃቸውም ነው የገለጹት።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዚምባቡዌ ተቋማት በሙስና ቢፈተኑም የትራፊክ ፖሊሶች ያፈጠጠ ጉቦ የመጠየቅ ልምድ ግን አሳሳቢ ስለመሆኑ ዜጎች ያነሳሉ።
ሐራሬ ባለፈው ወርም ይህንኑ ችግር ይቀንሳል ያለችውን ውሳኔ አሳልፋ ነበር፤ ፖሊሶች ለሥራ ከጣቢያ ሲወጡ ስልካቸውን እንዳይዙ የሚከለክል መመሪያ አውጥታ ተፈጻሚ ግን አልሆነም።
“ምንም እንኳን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ብናሰማም ትዕዛዙን የበላይ አዛዦች ሊያስፈጽሙት አልቻሉም” የሚለው አዲሱ የእገዳ ደብዳቤ፥ ፖሊሶች ከምሳ ሰዓት እና ከእረፍት ውጪ ስልካቸውን በሥራ ሰዓት መጠቀም እንደማይችሉ አመላክቷል።
የተላለፈውን ውሳኔ የማያስፈጽሙ የፖሊስ አመራሮች ስልካቸውን ይዘው ለሥራ ወጥተው በተገኙት ፖሊሶች ምትክ ለግዳጅ እንዲሠማሩ ይደረጋሉም ነው የተባለው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅት 27/207 ዓ.ም