መነጣጠል እስከማንችል ድረስ ተዋሕደናል!

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በአንድነት የሚኖሩባት ሀገር ናት። ከነዚህ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ውስጥ በሰፊ መልክዓምድር ላይ የሚኖሩና ከሀገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአማራና ኦሮሞ ብሔረሰቦች ተወላጅ ናቸው። እነዚህ ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች ጋር ለዘመናት ተከባብረውና ተደጋግፈው እየኖሩ ያሉ ሕዝቦች ናቸው። ሀገሪቱን በዓለም መድረክ ደምቃ እንድትታይ የሚያደርጉ የየራሳቸው መገለጫ የሆኑ ባሕላዊ እሴቶች፣ ቅርሶች፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሥነ- ቃል፣ ወግ፣ ዕምነት፣ ዕሴትና ሥነ-ጥበብ ያላቸው ብሔረሰቦች ናቸው።

ከዚህ ባሻገር ሁለቱ ብሔረሰቦች ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ በተጫወቱት ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። የኦሮሞና የአማራ ብሔረሰቦች ከሌሎች እህት ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ፣ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ቀንዲልና ተምሳሌት ሆና፤ ታፍራና ተከብራ እስከ ዛሬ ድረስ እንድትኖር ያደረጉ የሀገሪቱ የሉዓላዊነት፣ የነፃነት፣ የአልደፈር ባይነት፣ … ዋልታና ማገር ናቸው። የሀገር መደፈር እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው፣ ጥቃት የማይወዱ የነበላይ ዘለቀ፣ ባልቻ አባሳፎ፣ አብቹ፣ አብዲሳ አጋ፣ አሊ በርኬ … የመሳሰሉ የአርበኞችና የጀግኖች መፍለቂያ ብሔረሰብ ናቸው።

እነዚህ የጀግኖች መፍለቂያ፣ ጀግኖችን ከማፍራት ቦዝነው የማያውቁ ማሕፀነ ለምለም ብሔረሰቦች ከሌሎች እህት ወንድም ብሔረሰቦች ጋር በጋራ በመቆም በየዘመናቱ ቅጥሯን ጥሶ፣ ድንበሯን አልፎ የመጣን ጠላት ሁሉ አንገቱን አስደፍተው፣ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው፣ “ዳግመኛ አይለመደኝም” አስብለው ወደ መጣበት መልሰዋል። ይህን ደግሞ አይደለም ወዳጆቻችን ጠላቶቻችን አፍ አውጥተው መስክረዋል። አፍ አውጥተው የማይናገሩ ግዑዛን ፍጥረታትም ይመሰክራሉ።

እስኪ ጀግኖቹ የተዋደቁበት የዓድዋ ተራሮች የነ ባልቻና የነ ፊታውራሪ ገበየሁን ጀብድ ይመስክሩ። የማይጨው ተራሮች፣ የዓባይ በረሃ የእነ አብቹን፣ የእነ በላይ ዘለቀን የአርበኞቹን ጀብድ ይናገሩ። የካራማራውን ጀግና አሊ በርኬን ዛሬም የሶማልያ በረሃዎች ያስታውሱታል። የሮም አደባባይ ዛሬም የአብዲሳ አጋን ገድል አትዘነጋውም።

ታሪክ እንደሚያስረዳን፣ መሬት ላይ ያለውም ተጨባጭ ሐቅ እንደሚያሳየን ሁለቱ ብሔረሰቦች በሀገራቸው ክብርና ነፃነት የማይደራደሩ፣ ለጠላት የማይንበረከኩ፣ በአንድነት ቁመው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ያጸኑ፣ ለሀገር ነፃነት በየዓውደ ውጊያው በአንድ ምሽግ የወደቁ ብሔረሰቦች ናቸው። የሁለቱም ሆነ የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ኅብረት የኢትዮጵያ የአልደፈር ባይነቷ ሚስጥር ነው።

ይህንን የኢትዮጵያ የአልደፈር ባይነት ምስጢር የተረዱት የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች፤ የበሬ ወለደ ትርክት በመፍጠር በብሔረሰቦች በተለይ በሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ለዘመናት የልዩነትና የጥላቻ ግንብ እየገነቡ ይገኛሉ። ለዘመናት ተዋዶና ተከባብሮ የኖሩ ሕዝቦች እንዲገፋፉ ማድረግ የሴራቸው መዳረሻ አድርገው ይዘዋል። ይህንን ለማስፈፀምም የሀገራችንን አንዳንድ ፖለቲከኞችን ሲጋልቡ ይስተዋላል፡፡

በእርግጥ ፖለቲከኞች የተሻለ ርዕዮተ ዓለም ቀርፀው ተፎካክረው ሥልጣን መያዝ በሕግ ተደንግጎ የተሰጣቸው መብት ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብን የሚጠቅም፣ ልማትን የሚያፋጥን፣ እድገትንና እኩልነትን የሚያረጋግጥ፣ ድህነትን ድል የሚነሳ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነድፈው መወዳደር ያቃታቸው አንዳንድ ፖለቲከኞች ሕዝብን ከሕዝብ የሚለያይ፣ አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ እንዲነሳ፤ የጥላቻ መርዝ ሲረጩ፣ ሥልጣን በቋራጭ ለመያዝ በህቡዕ የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ ሲያስፈፅሙ ይስተዋላል።

ታሪካዊ ጠላቶቻችን በተለይ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ሕዝብ ያላቸው ሁለቱ ብሔረሰቦች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸው ተሳትፎና ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ይረዳሉ። ሁለቱ ሕዝብ በዓይን ጥቅሻ ሲግባቡ፤ ከፊታቸው የሚቆም ጠላት እንደማይኖርና የትኛውም ችግር እንደማይበግራቸው ጠንቅቀው ያውቁታል። በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥ የኦሮ- አማራ ጥምረት ጉልህ ድርሻ መኖሩን ያስታውሱታል። ስለዚህ የሁለቱ ብሔረሰቦች አንድ መሆን፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና የታሪካዊ ጠላቶቻችን አጀንዳ አስፈጻሚ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችንን እንቅልፍ ነስቷቸዋል።

ታዲያ ከሰሞኑ የአማራና የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የፖለቲካ አዋቂ ሰዎች “ፖለቲካል ኢሊትስ” በሀገረ አሜሪካ ተገናኝተው መወያየታቸውን ተከትሎ፤ አንድ ተምሮ ያልተማረ ምሑር ነኝ ባይ፣ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ፍርፋሪ ለቃሚ ከወደ ዋሽንግተን “የአማራና የኦሮሞ ብሔረሰብ ጥምረትን በማንቋሸሽ የጥላቻ መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ ሰው ፕሮፌሰር የሚል ማዕረግ ተሰጥቶታል እንጂ፤ እንደኔ አይደለም፡፡ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መመረቅ ይቅርና ፊደል የቆጠረ አይመስለኝም። ምክንያቱም ሰውየው በስደት የሚኖርባት ሀገረ አሜሪካ ዛሬ ላይ በሁሉም ነገር የዓለም ቁንጮ ለመሆን የበቃችው፤ በ54ቱም ግዛቶቿ የሚኖሩ ሕዝቦቿ ልዩነትና መከፋፈልን ወደጎን ብለው አንድነትን በመምረጣቸው ነው። በአንድነት፣ በኅብረት፣ በተሠራች ሀገር ላይ ተደላድሎ ተቀምጦ፤ ሳይማር ያሰተማረውን ሕዝብ ከፋፍሎ ለተኩላ ለመስጠት ከሚሠራ በላይ ቂል ያለ አይመስለኝም።

ሰውየው በንግግሩ የታሪክ ድሃ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል። ለአብነት ዓድዋ ላይ “ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ” ተብሎ የተገጠመው ፊታውራሪ ገበየሁ ቢሰዋ፤ ባልቻ አንድ ስንዝር እንኳን ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ልቡ አላመነታም። ይልቁንም መድፍ ብቻውን እያገላበጠ ከወንድሙ ገዳዮች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ወንድሙ የተሰዋለትን የሀገሩን ነፃነት አስከበረ እንጂ። ታዲያ ከዚህ በላይ ጥምረት፣ ፍሬ፣ ውሕደት፣ ኅብረት … ከወዴት አለ?

ከዓድዋው ሽንፈት ከ40 ዓመት በኋላ ዳግም የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ወሮ በቆየበት አምስት ዓመት ውስጥ፤ የሁለቱ ብሔር ተወላጅ ጀግኖች አርበኞች እነ በላይ ዘለቀ፣ አብቹ … ከሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆች ጋር ተናበው ጠላትን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተው፣ ዶጋ አመድ አድርገው ዳግም አንገቱን አስደፍተው ወደመጣበት የሸኙት። ታዲያ በአንድነት ቁሞ የሀገርን ነፃነት ከማስጠበቅ በላይ ምን ፍሬ አለ?

ደግሞስ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ አንዱ የአንዱን ቋንቋ፣ ባሕል፣ ወግ ወርሶ ተጋምዶ እየኖሩ ካሉ ከነዚህ ብሔረሰቦች ሕዝብ በላይ ምን ዝምድና፣ ኅብረት፣ ፍሬ፣ አለ? እስኪ ንገሩኝ በአንድ ኩንታል ውስጥ ተቀላቅሎ ያለን ነጭና ጥቁር ጤፍ፤ ጥቁርና ነጩን ለየብቻ መለየት የሚቻለው ማነው? ማንም ነጩን ለብቻ፣ ጥቁሩን ለብቻ መለየት አይችልም። በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ተጋብቶ ተዋልዶ የሚኖረውን የአማራና የኦሮሞ ብሔረሰቦችን ሆነ ሌሎችን ብሔረሰቦች ማንም መለየት መነጣጠል አይችልም።

ለጊዜው በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ለዘመናት ተከባብረውና ተደጋግፈው የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ለመከፋፈል በሚጎነጎነው ሴራ ፈተናው ሊበረታ ይችላል። ዳሩ ግን ከኅብረትና ከአንድነታቸው የሚለያቸው ማንም የለም። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያለን ብሔር ብሔረሰቦች መነጣጠል እስከማንችል ድረስ ተዋሕደናል!

በመሆኑም በውጭም በሀገር ውስጥም ያላችሁ ተማርን የምትሉ ሰዎች ሳይማር ያስተማራችሁን ማኅበረሰብ አዳዲስ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ በማፍለቅና በማሸጋገር ሕዝብና ሀገርን መጥቀም ካልቻላችሁ፤ ቢያንስ ተጋብቶ፣ ተዋልዶ፣ ተስማምቶ በሠላም ከሚኖረው ሕዝብ እጃችሁን አንሱ። ቸር ሰንብቱ!

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን  ጥቅት 27/207 ዓ.ም

 

Recommended For You