መንግሥት ሐምሌ 22 ቀን 2106 ዓ/ም ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቷን ይፋ ካደረገበት ወቅት አንስቶ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። አንዳንዶች እንዲያውም ዘግይቷል ሲሉ ሌሎች ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ ‹‹አበቃላት›› የሚል አስተያየትም እስከመስጠትም ደርሰው ነበር። ሆኖም ባለፉት ሦስት ወራት የታየው ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ እና የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ቀደም ብሎ መተግበር ይገባው እንደነበር ያሳየ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመን ስትፈተንባቸው ከቆየችባቸው ተግዳሮቶች ውስጥ የመጠባበቂያ ገንዘብ እጥረት አንዱ ነው። ለዘመናት ያህል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ውስጥ የነበረው የመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ የሳሳ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሀገሪቱ ችግር ቢገጥማት ፈተናውን እንዴት ትወጣው ይሆን የሚል ስጋትን ሲጭር የቆየ ነው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላ የሀገሪቱ የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት በከፍተኛ መልኩ ለውጥ አምጥቷል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለክፉ ቀን ብላ የምታስቀምጠው የመጠባበቂያ ገንዘብ ባለፉት ሦስት ወራት 161 በመቶ አድጓል፡፡ የግል ባንኮች ሪዘርብ በ29 በመቶ አድጓል። ይህም ለዘመናት በስጋትነት ሲነሳ የነበረውን የሀገሪቱን የመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችት አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተፈታ መሄዱን የሚያመላክት ነው፡፡
በገቢ ረገድ የታየውም እመርታ የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ውጤታማነትን ያሳየ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ኮንትሮባንድን እና የታክስ ስወራን በእጅጉ በመቀነስ ሀገራዊ ገቢን እያሳደገ ነው። ባለፉት ሦስት ወራት 180 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል። ዘንድሮ በሦስት ወራት ብቻ የተሰበሰበው ገቢ በ2010 ከገባው 176 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ገቢ የላቀ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚው በፈጠረው ምቹ ሁኔታም ዘንድሮ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል። ያለፉት ሦስት ወራት አፈጻጸም የሚያሳየውም የታያዘው ዕቅድ እንደሚሳካ ነው፡፡
በተመሳሳይም የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ከፍተኛ በሆነ መልኩ እንዲጨምር አድርጎታል። ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን ይህም አፈጻጸም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው። ይህም አፈጻጸም ሀገሪቱ በዚህ ዓመት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት እንደምትችል የሚያሳይ ነው። ይህም ለኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ነው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኮንትሮባንድ እና ብልሹ አሠራሮችን በመከላከል አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ወርቅን የመሳሰሉ በኮንትሮባንድ ይወጡ የነበሩ ምርቶች ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገቡ አድርጓቸዋል። ባለፉት ሦስት ወራትም ወርቅ 500 ሚሊዮን ዶላር ያስገባ ሲሆን ይህም ወርቅ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች በገቢ የመጀመሪያውን ደረጃ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ምክንያት ከውጭ የሚላክ የገንዘብ መጠን ወይም ሬሚታንስም ጨምሯል። ከውጪ ወደሀገር ውስጥ የሚገባው የሬሚታንስ ገቢ ባለፉት 3 ወራት 24 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦበታል። ይህም በውጭ ሀገር የሚገኙ ዜጎች በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም ገንዘባቸውን በቀጥታ በሕጋዊ መልኩ በባንክ እንዲልኩ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው እና በሀገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱ ዕድል እንደፈጠረላቸው የሚያመላክት ነው፡፡
በሌላ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሀገር ውስጥ ተተኪ ምርቶች እንዲበራከቱ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች እንዲቀንሱ በማድረግ ረገድ አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። ባለፉት ሦስት ወራትም ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች በ1 ነጥብ 3 በመቶ ቀንሰዋል። በምትኩም የሀገር ውስጥ ምርቶች ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የተገበረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጉልህ የሆኑ ለውጦችን እያመጣ መሆኑን ባለፉት ሦስት ወራት የተገኙት ውጤቶች ምስክር የሚሆኑ ናቸው። ስለዚህም የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሊቀጥል እና የታየውን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ወደ ተሟላ ብልፅግና ማድረስ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም