የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ 2025 ዓ.ም እቅድ ውስጥ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ አስቻይ ከሆኑት የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ቁልፍ እና ዋነኛው እንደሆነም ይነገራል። የፋይዳ መታወቂያ የሁሉንም ነዋሪ ረቂቅ ባዮሜትሪክ መረጃን በመውሰድ ወደ ልዩ መለያ ከመቀየር ባለፈ ተቋምን ከተቋም፤ ከተማን ከክልል፤ ከተማን ከከተማ እና ዞንን ከዞን በማሰናሰል፤ እስከ ዛሬ ሊኖረን ያልቻለን የተሳለጠ በልዩነት የመታወቅ ሥርዓትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑም በተደጋጋሚ ተገልጿል። በእርግጥ በተለይ በመንግሥት አስተዳደር በኩል ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ሀብት ከማወቅ ጀምሮ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ሁነኛ መንገድ መሆኑ አጠራጣሪ አይደለም ።
የፋይዳ ልዩ ቁጥር ማለት ለአንድ ግለሰብ በፋይዳ መታወቂያ ሥርዓት አማካኝነት የተሰጠ የመታወቂያ ሥርዓት ነው። ይህ ባለ አስራ ሁለት አሀዝ ቁጥር ኮድ አንድን ሰው በልዩነት ለመለየት እና አገልግሎቶችን ለመስጠት እንደዋነኛ መለያ ያገለግላል። ልዩ ቁጥሩም አንድ ሰው ከተሰጠው በኋላ እስከ ህልፈተ ሕይወቱ ሊገለገልበት የሚያስችለው ይሆናል። በመንግሥት በኩል አስተዳደርን በተገቢው መንገድ ተደራሽ ለማድረግም ሆነ ሕገወጦችንና ሕገወጥነትን ለመቆጣጠር የሚያስችለው መሆኑ ግልጽ ነው። ይህ እንደተጠበቀ የፋይዳ መታወቂያ በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበሩ ለዜጎችም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የዛሬ የጽሁፌ ማጠንጠኛም ታዲያ ግን ዜጎች ስለምን የፋይዳ መታወቂያን ለመያዝ አልተሯሯጡም የሚል ነው።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ለዜጎች የመለያ መታወቂያ መሰጠት ከጀመረ ብዙ ዘመን አልሆነውም። እስከ ቅርብ ጊዜም ይሰጡ የነበሩት መታወቂያዎች በቀላሉ ተመሳስለው ለመሰራት / ለፎርጅድ የታጋለጡ በመሆናቸው ዛሬም ድረስ ከአንድ በላይ መታወቂያ ያላቸው በርካቶች ናቸው። ከአንድ በላይ መታወቂያ የሚኖራቸው ሰዎች ደግሞ በምንም መስፈርት ይሁን በየትኛውም ዘመን ቢኖሩ አንዳች የተደበቀ ዓላማና የማጭበርበር ተልእኮ እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው።
እንግዲህ ጨዋታው የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። እነዚህ አካላት የሚያጭበረብሩት ወይንም ራሳቸውን በተለያየ ማንነት እየገለጹ የሚከሰቱት መንግሥትን ለማወናበድ ብቻ አይሆንም። በእርግጥ በሕገወጥ መንገድ መሬት ለመውረር፤ ግብር ለመደበቅና አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት፤ በመንግሥት ንብረትና አስተዳደር ላይ ወንጀሎችን ከሰሩ በኋላ በአዲስ ማንነት ለመከሰት መታወቂያ ሁነኛ መንገድ ሆኖ ቆይቷል ። ዛሬም አለ።
ነገር ግን ከመንግሥት ባልተናነሰ ምን አልባትም በባሰ መልኩ ግለሰቦች ላይ ወንጀል የሚሠሩና የሚያጭበረብሩ አካላትም ወንጀል ከሠሩ በኋለ ራሳቸውን የሚደብቁት በመታወቂያ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አዲስ አበባ ላይ የማጭበርበር ወይንም ሌላ ወንጀል የፈጸመ አካል ወደሌላ አካባቢ ሲሄድ ከአለባበሱ ቀጥሎ የሚቀይረው ነገር ቢኖር መታወቂያውን ነው። በእንቅስቃሴ ወቅት ፤ ሆቴል ማረፍ ቢያስፈልግ፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀም ቢያስፈልግ አዲስ በአዲስ መታወቂያ ብቻ የፈለገውን መከወን ይችላል። እስከ ቅርብ ጊዜ በተለያዩ ስምና አድራሻዎች በአንድ ባንክ የተለያዩ ደብተሮችን አውጥተው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች መገኘታቸውን በተደጋጋሚ ስንሰማ ቆይተናል።
በመሠረቱ የመታወቂያ አሰጣጥ ሥርዓታችንም ሆነ የመታወቂያ አገልግሎት ወሰናችን የተዛባ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሱ የተጭበረበረ ነበር ለማለት ያስደፍራል። ለምሳሌ ዛሬም ድረስ አንድ ሰው በበርካታ የግልም ሆነ የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማቶች አገልግሎት ለማግኘት ሲቀርብ እንደ ቀበሌ መታወቂያ ሁሉ የመንጃ ፈቃድ የሥራና ሌሎች ማንነቴን ይገልጽልኛል የሚላቸውን ነገሮች ማቅረብ ይችላል።
በግልባጩ የመንጃ ፈቃድ ለማግኘት ደግሞ ማንኛውም ሰው ከየትኛውም አካባቢ በያዘው የነዋሪነት መታወቂያ በየቦታው በሀሰተኛ መንገድ ከሚዘጋጀው ጀምሮ መጠቀም ይችላል። ምክንያቱም የመታወቂያው መነሻ ጋር በመሄድ መታወቂያው ከሚመለከተው አካል የተሰጠ መሆኑን ለማጣራት የሚካሄድ አሠራር ወይንም የሚደረግ ጥረት ባለመኖሩ ነው። በዚህ ረገድ አንዳንድ ቦታዎች በውስን ጉዳዮች ላይ ወንጀል ተሠርቶ ከተገኘ ወይንም መታወቂያው አጠራጣሪ ሲሆን የሚወሰዱ ርምጃዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም።
በዚህም በርካታ ግለሰቦች ከባንክ አካውንታቸው በሀሰተኛ መታወቂያ ተዘርፈዋል። ያልወከሉት ሰው ወክሎኛል ብሎ ብዙ ንብረት ሀብታቸውን ዘርፏቸዋል። ሕጋዊ ውክልና አለኝ በሚል ቦታቸውን የተነጠቁ የተሸጠባቸው በርካቶች ናቸው። በዚህ ረገድ ሀብት ንብረታቸውን ሀገር ቤት አስቀምጠው በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የበለጠ ተጋላጭ ሆነው ቆይተዋል። እኔ አስከማውቀው ጊዜ ድረስ የውልና ማስረጃ ሠራተኞች የሚቀርብላቸውን የማንነት መግለጫ መታወቂያ ሲያረጋግጡ የነበረው በዓይን በማየት ብቻ ነበር። በዋናነትም የማጣራት ሥራ የሚሠራው መታወቂያው ጊዜ ያለፈበት ነው ወይንስ አይደለም ታድሷል ወይንስ አልታደሰም በሚለው ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነው።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው በዚህ ሂደት ካለፈ በኋላ የሚሰጠው የውክልና ማስረጃ ፎቶ እንኳን አይለጠፍበትም ነበር። ይህም ማለት አንድ ሰው በየትኛውም ሁኔታ ያገኘውን ውክልና የሚመሳሰል ተመሳሳይ መረጃ የያዘ መታወቂያ ማሠራት ከቻለ በቀላሉ የሁሉም ነገር በር ተከፈተ ማለት ነው። ከዓመት በፊት በፖሊስ የቴሌቪዥን ፕሮግራም የቀረበልንና በሕይወት እያሉ እንደሞቱ ተደርጎ ከባንክ አካውንታቸው ብር የተወሰደባቸው እናት ታሪክ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።
በነገራችን ለይ በውርስ ጉዳይ፤ በፍቺ ጉዳይ፤ እና በሌሎችም ሀሰተኛ መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸው ለምስክርነት የሚቀርቡ ሰዎች መኖራቸውን ምን ያህሎቻችን እናውቅ ይሆን ?። ከጎዳና ለይ ተነስተው ሰልባጅ ሱፍ ለብሰው ሀሰተኛ መታወቂያ ተሰጥቷቸው ምስክር በመሆን ስንቱን ለመከራ የሚዳርጉ መኖራቸውንስ ምን ያህሎቻችን እናውቅ ይሆን።
በተጨማሪ ከቤት ሠራተኛና ቤት ተከራይ ጀምሮ አየር ላይ በተሠሩ መታወቂያዎች ወንጀልና ዘረፋ የተከናወነባቸውን ቤት ይቁጠረው። በሀሰተኛ መታወቂያ ወንጀል የሠሩ ግለሰቦች ደግሞ በሌላ ሀሰተኛ መታወቂያ አዲስ ማንነት ተላብሰው አዲስ ሕይወት መጀመር ለእነሱ ድንች የመላጥ ያህል ቀላል ነው። ምክንያቱም መንገዱንም አጠቃቀሙንም ጠንቅቀው ያውቁታልና ነው። በጣም በርካቶችም በትዳር ላይ ትዳር ሲመሰርቱ ለአዲሱ ጎጇቸው ማድመቂያ አዲስ ማንነትና አዲስ ህልውና የሚሰጣቸው ይኽው በየመንደሩ የሚፈበረክና ሙሰኛ የቀበሌና የወረዳ ሹሞች የሚሰጡት መታወቂያ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ተቋማት ያሉ በሙስና የተዘፈቁ አገልጋዮችም መታወቂያን ምክንያት በማድረግ ሙስና እና የማጭበርበር ተግባራትን እንዳያከናውኑ አደብ የሚያሲዝ ይሆናል። በመሠረቱ ሊያጭበረብር ሊዘርፍ ሊሰርቅ ያላሰበ ሰው ሁለት መለያ ሊይዝ የሚፈልግበት ሁኔታ አይኖርም። በመሆኑም የመንግሥት አቅም እስካልተገደበ ድረስ ሁላችንም ዛሬ ነገ ሳንል የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት ልንሆን ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የመንግሥትም ሆነ የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥርዓቱን በተከተለ መንገድ ወደዚህ አሠራር ሊገቡ ይገባል። ሥርዓቱን ተከትለው ስል ቀድመው በማሳወቅና የመዘጋጃ ጊዜ ለተገልጋዮቻቸው በመስጠት ተደራሽ የሚያደርጉትን አገልግሎት በሙሉ በፋይዳ መታወቂያ አማካይነት ሊሆን ይገባል የዛሬው ነው። ቸር እንሰንብት ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም