እስራኤል ወታደራዊ መሪዎች ሀገሪቱ በጋዛና ሊባኖስ በወታደራዊ ዘመቻዎች ማከናወን የፈለገቻቸውን ዓላማዎች በሙሉ ማሳካቷን አመልከተዋል፡፡ እስራኤል በወታደራዊ ኃይል የምትችለውን ሁሉ እንዳሳካች የገለጹት አዛዦቹ፣ ፖለቲከኞች ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜው አሁን መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ከፍተኛ ጄነራል ከሰሞኑ በሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኙ መኮንኖች ጋር ወቅታዊ የጦርነቱን ሁኔታ ለመገምገም በነበራቸው ስብሰባ፤ የግጭቱ ከዚህ በኋላ መቆየት እምብዛም ጥቅም የለውም ማለታቸው ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ኢታማዦር ሹም ሄርዚ ሄልቪ እንደተናገሩት፣ “በጋዛ የሰሜን ጋዛ ብርጌድ አዛዥን ብንገድል ለቡድኑ ሌላ ውድቀት ነው፤ ነገ ምን እንደሚገጥመን አላውቅም። ነገር ግን ይህ ጫና ወደ ተጨማሪ ስኬቶች እንድንቀርብ ያደርገናል” ማለታቸው ተገልጿል፡፡
በሊባኖስ ሄዝቦላህ ላይ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት አሁን በሚገኝበት ደረጃ አንድ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እድሉ አለ ሲሉ ኢታማዦር ሹሙ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትራቸው ዮአቭ ጋላንት “በጋዛ ፍፁም ድል የሚለው ሃሳብ ከንቱ ነው” ሲሉ በነሀሴ ወር ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጋር በዝግ በተደረገ ስብሰባ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርትም “የተሻሻሉ የዘመቻ ግቦች በሌሉበት ባልጠራ ኮምፓስ እያደረግን ያለነው ውግያ የዘመቻውን ውጤት ይጎዳል” ማለታቸውም ተዘግቧል፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ ትኩረት መደረግ የሚገባው በጋዛ የቀሩትን ታጋቾች ማስለቀቅ መሆኑን በመግለጽ፣ ከሃማስ ምንም አይነት ወታደራዊ ስጋት አለመኖሩን ማረጋገጥና የሲቪል አገዛዝን ተግባራዊ ማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በጋዛ “ፍፁም ድል” ለማስመዝገብ ደጋግመው ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ይህን ሃሳብ ለመቀበል የሚችገሩ ይመስላል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም