ሰሜን ኮሪያ ለቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መልዕክት ነው ያለችውን የአሕጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓ ተገለጸ፡፡ ሚሳኤሉ ከ7 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ከፍታ እና አንድ ሺህ ኪሎሜትር ርቀት ተጉዟል ተብሏል፡፡
ፒዮንግያንግ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀን ተመሳሳይ ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል ይጠበቃል፡፡
“በኪም የመሪነት ዘመን ሰሜን ኮሪያ የሀገሪቱን መከላከያ ኃይል ፍፁም የበላይነትን በማስጠበቅ ትልቅ ደረጃ ያደረሰውን ወሳኝ የሚሳይል ሙከራ ተደርጓል” ሲል የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኬሲኤንኤ ዘግቧል፡፡
ሁዋሶንግ 19 የተባለው አሕጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል የኒውክሌር አረርን መሸከም የሚችል ሲሆን 7 ሺህ ኪሎሜትር ከፍታ መምዘግዘጉ ነው የተሰማው፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሣሪያን መሸከም የሚችሉ የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን በማምረት ረገድ የማይቀለበስ ደረጃ ላይ መድረሷን ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ የዜና አገልግሎት የደቡብ ኮሪያን ጦር ጠቅሶ እንደዘገበው ሚሳኤሉ በከፍተኛ ፍጥነት ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ አቅራቢያ ንጋት ጠዋት አንድ ሰዓት አካባቢ ነው የተወነጨፈው፡፡
በምሥራቅ ባሕር ከመውደቁ በፊትም አንድ ሺህ ኪሎሜትሮችን እንደተጓዘ ጦሩ ያሰራጨው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነው አሕጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በመጪው ማክሰኞ ከሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተደረገ ነው።
ተንታኞች እንዳሉት የሰሜን ጠብ አጫሪ ድርጊት ዓላማው የኒውክሌር መሣሪያዎችን ወደ አሜሪካ የማድረስ አቅሟን ለማሳየት ነው ።
የደቡብ ኮሪያ የደኅንነት ተቋማት የፒዮንግያንግ ሙከራ በዛሬ ብቻ እንደማያበቃ እና ኅዳር አምስት ማክሰኞ በ2024 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀን ተመሳሳይ ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ሁዋሶንግ 19 የተባለው ሚሳይል 1 ሺ አንድ ነጥብ ሁለት ኪሎሜትር በ7687 ከፍታ ለ86 ደቂቃዎች መጓዙ ተዘግቧል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ድርጊቱን አውግዘው የፀጥታው ምክር ቤትን የውሳኔ ሀሳብ የተላለፈ ነው ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ ከምዕራቡ ዓለም እና ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ጋር የተካረረ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ፒዮንግያንግ ወደ ሩሲያም 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በመላክ እየተወቀሰች ትገኛለች፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም