የቦትስዋና ገዥ ፓርቲ ከ58 ዓመት በኋላ በምርጫ ተሸነፈ

የአፍሪካዊቷ ቦትስዋና ገዥ ፓርቲ ከ58 ዓመት በኋላ በምርጫ መሸነፉ ተገለጸ፡፡ አምቤሬላ ፎር ዲሞክራቲክ ቸንጅ የተባለው ፓርቲ ሥልጣን እንደሚረከብ ተመላክቷል።

የቦትስዋና ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ቢዲፒ) ሀገሪቱ ነፃነቷን ካገኘችበት ከ1966 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የቆየ ሲሆን፤ በምርጫው እስከ ዛሬ ድረስ አንድ መቀመጫ ብቻ ማሸነፉን የቢቢሲ ዘገባ ጠቅሷል።

በቦትስዋና ተዓምራዊ የሚባሉ ለውጦች ቢመዘገቡም በቅርብ የተመዘገበው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት እና ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር የቢዲፒን ተወዳጅነት እንዳደበዘዘው ተመላክቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ማሲሲ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ሥልጣን ለቀን በሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሂደቱ ላይ እንሳተፋለን”። ማሲሲ ደጋፊዎቻቸው እንዲረጋጉ እና ከአዲሱ መንግሥት ጎን እንዲቆሙም አሳስበዋል።

ቀደም ብለው የተደረጉ ቆጠራዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ዱማ ቦኮ የሚመራው ዩዲሲ ፓርቲ 25 መቀመጫዎችን አግኝቷል።

ፓርቲው በፓርላማ አብላጫ ድምፅ ለማግኘት ከሚያስፈልገው 31 መቀመጫዎች በላይ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ከቢዲፒ በተገነጠሉት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ላን ካማ የሚመራው ቦትስዋና ፓትሪዮቲክ ፍሮንት (ቢፒኤፍ) አምስት ድምፅ ያገኘ ሲሆን፤ የቦትስዋና ኮንግረስ ፓርቲ (ቢሲፒ) እስካሁን ሰባት መቀመጫዎችን አግኝቷል።

ፕሬዚዳንት የሚመረጠው በፓርላማው ስለሆነ ፓርላማው ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደርገው ስብሰባ ቦኮን ቀጣዩ መሪ አድርጎ ይመርጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አምቤሬላ ፎር ዲሞክራቲክ ቸንጅ (ዩሲዲ) የተባለው ፓርቲ ሥልጣን እንደሚረከብ የተገለጸ ሲሆን፤ የዩዲሲ ደጋፊዎች በዋና ከተማዋ ጋቦሮኒ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው ተብሏል፡፡

ከ2018 ጀምሮ ሀገሪቱን የመሩት ማሳሲ ያልተሳካውን የቢዲፒ ፓርቲ ዘመቻ መርተዋል። ፕሬዚዳንቱ ፓርቲያቸው “ለውጥ” ሊያመጣ ይችል እንደነበር፣ ነገር ግን መራጮች የሚጠበቅበትን ሠርቷል ብለው አምነዋል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በጋዤጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You