ፍቃዱ ደርበው እና አያልሰው አባይ ጓደኛሞች ናቸው። ከሕፃንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ መልካሙን እና መጥፎውን ጨዋታ እየተጫወቱ አድገዋል። ምንም እንኳ ወንድማማቾች ባይሆኑም አንድ አካባቢ ተወልደው አብረው በማደጋቸው አስተሳሰባቸው እጅግ ተቀራራቢ ነው። በ2013 ዓ.ም ሁለቱም 24 ዓመት ሲሞላቸው አንዱ ያሰበውን ሲገልፅ፤ ሌላኛው በፍጥነት መስማማቱን ያሳውቃል። ሃብታም መሆን የሚችሉበትን መንገድ ሲያውጠነጥኑ በቀላሉ ሠርተውም ገንዘብ ማግኘት አንችልም በሚል ተማምነው ዝርፊያ ላይ ለመሠማራት ተስማሙ።
የእነፍቃዱ ጉዳይ አስገራሚ የሚሆነው አንደኛው እንዝረፍ ሲል፤ ሌላኛው ይቅርብን አይልም። ሁለቱም በሚሰርቁበት መንገድ ላይ ይነጋገራሉ፤ አንዱ ተነጥሎ ስርቆትን ፈርቶ እንያዛለን መሥራት ይሻለናል ብሎ አይቃወምም። በተደጋጋሚ ፍቃዱ ደርበው ከበድ ያሉ የዝርፊያ ሃሳቦችን ያቀርባል፤ አያልሰው አይቃወምም፤ አብሮ ይሳተፋል። በፍቃዱ የታዘዘውን ይፈፅማል።
ፍቃዱ መኪና ለመዝረፍ አሰበ። ሃሳቡን ለጓደኛው ነገረ። አያልሰው አልተቃወመውም። መኪና የሚሰርቁበትን ሁኔታ ለማጥናት ቢነጋገሩም፤ መኪናው ከተሠረቀ በኋላ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ማሰብ እና ዘዴ ማግኘት አቃታቸው። አያልሰው በስርቆቱ ተስማምቶ ‹‹ እንደውም ‹ መኪና የሚያርዱ ሰዎች አሉ› ይባላል።›› ለእነርሱ እንሽጥላቸው ሲል፤ ፍቃዱ በበኩሉ ‹‹ እነርሱን ከየት እናግኛቸው? ›› ሲል ጠየቀ። ደጋግመው ሲያስቡ መኪና መስረቅ ቀላል አልሆነላቸውም።
ሌላ ቀላል ነው ብለው በሚያምኑበት ጉዳይ ላይ መነጋገር ጀመሩ። የሰው ቤት መዘረፍ አዋጭ እንደማይሆን ተማመኑ። ምክንያቱም በግለሰብ ቤት ገብተው ብዙ በቀላሉ የሚገኝ ሀብት አይኖርም። የሚገኘው ሀብትም ተሸጦ ብዙ ገንዘብ አያስገኝም በሚል ተነጋገሩ። አንዳንዴ ደግሞ በቤት ውስጥ ዝርፊያ ትልቅ ሀብት ቢገኝም፤ ብዙ ገንዘብ ያለው ሰው መሳሪያ ስለሚኖረውና እነርሱ ደግሞ መሳሪያ ስለሌላቸው በቀላሉ ሊጎዱ እንደሚችሉ ተማመኑ። የመካከለኛ ነዋሪውን ሀብት ለመዝረፍ ቢሞክሩ እና ትልልቅ ዕቃ ቢሠርቁ የሚያስቀምጡበት እንደሌለ እና ቢሸጡም ብዙም እንደማያዋጣቸው ተወያዩ።
በድጋሚ እንደገና እያሰላሰሉ ጊዜ ሰጥተው ቢያስቡም የተሻለ ገንዘብ ሊያገኙበት የሚችሉትን እና በቀላሉ የሚሠረቅ ነገርን በተመለከተ ማሰብ አቃታቸው። በመጨረሻም ይሆንልናል ብለው ያመኑበትን በየአካባቢው ጥናት አድርገው አንድ የሚያውቁትን ባጃጅ ለመስረቅ ተነጋገሩ። በነገሩ ላይ ሁለቱም ተስማምተው ዕቅድ ማውጣት ጀመሩ። ባጃጇ ከቆመችበት ቦታ ላይ ቁልፍ ሳይገኝ አንስቶ መውሰድ የሚታሰብ አይደለም። ስለዚህ መላ ብለው የወሰዱት ምሽት ጉዳይ እንዳላቸው አስመስለው ከሹፌሩ ጋር በመነጋገር ኮንትራት ይዘው ባጃጁን መቀማት ጥሩ ሃሳብ መሆኑን አመኑ። ባጃጁን ከነጠቁ በኋላ ወልዲያ ወስደው በየተራ እንደሚሠሩበት እና በሂደት ሌላ ባጃጅ ገዝተው በየግላቸው እንደሚሰሩ መግባባት ላይ ደረሱ።
ውንብድና
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ስሙ ጉልት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፤ ፍቃዱ እና አያልሰው የባጃጁን አሽከርካሪ ፍቃዱ ተሾመን ኮንትራት አራት ሰዓት አካባቢ እንደሚፈልጉት ነገሩት። የዘነበ ጎሽዬ ንብረት የሆነውን ባጃጅ የሚያሽከረክረው ፍቃዱ ሥራ አገኘሁ ብሎ በደስታ ተስማማ። የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-23956 የሆነውን ባጃጅ ተኮናትረው በፍቃዱ ተሾመ አሽከርካሪነት ወደ ቆሬ ማምራት ጀመሩ። ፍቃዱ ተሾመ መንገዱን እያየ ሲያሽከረክር አያልሰውን እና ፍቃዱ ደርበው በፍፁም አልተጠራጠረም። እነርሱ ግን ለዝርፊያ አስበው ስለወጡ ሁለቱም በምልክት እየተነጋገሩ ከኋላ ቁጭ ብለው የሚመቻቸው ቦታ ላይ እስኪደርሱ መጠባበቃቸውን ቀጠሉ።
ሐምሌ በመሆኑ ዝናቡ በስሱ እየዘነበ ነው። ፍቃዱ ተሾመ እንዳይበርደው ጃኬት ደርቦ የአንገት ልብስ ጠምጥሟል። ከኋላ የተቀመጡት ወንበዴዎች ምንም አያወሩም። ፍቃዱ ተሾመ ሁኔታው ትንሽ ቢቀፈውም ሥራ ነውና መንገዱን ቀጠለ። ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ቦታው ባቱ ኮንደሚኒየም አካባቢ ሲደርሱ ፍቃዱ ደርበው በምልክት ለአያልሰው ውጋው አለው። አያልሰው እንደተባለው ተነስቶ የባጃጁን መሪ ይዞ ሲያሽከረክር የነበረውን ፍቃዱ ተሾመን በያዘው የሽንኩርት ቢላዋ አንገቱን ወጋው። ፍቃዱ ደርበው ፈጠን ብሎ ፍቃዱ ተሾመ ራሱን እንዳይከላከል በአንገቱ ላይ የጠመጠመውን ልብስ ከኋላው አጥብቆ በማሰር አነቀው።
አያልሰው ፍቃዱን አንገቱን ብቻ ሳይሆን ደግሞ የቀኝ ትከሻውን ሲወጋው ፍቃዱ ተሾመ የባጃጁን በር ከፍቶ ከባጃጁ ላይ ወደቀ። አስፓልት ላይ የወደቀው ፍቃዱ ተሾመ ደሙ መፍሰስ ጀመረ። እነአያልሰው ደግሞ በምንም መልኩ ሊከተላቸው እንደማይችል አረጋግጠው ባጃጁን ተራ በተራ እያሽከረከሩ ከከተማ ይዘው ወጡ። ፍቃዱ ተሾመም የወደቀው በክፉ ሰዓት በመሆኑ ደሙ ሲፈስ ሐኪም ቤት የሚያደርሰው ሰው በማጣቱ እዛው በወደቀበት ሕይወቱ አለፈ።
የተገታው ጉዞ
ፍቃዱ ደርበው እና አያልሰው ምንም ዓይነት ፍርሃት አይነበብባቸውም። ከመፀፀት ይልቅ እንደውም ዘና እያሉ ቁርስ ቡና እየተገባበዙ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ልክ ከከተማ እንደወጡ ወደ ሸዋሮቢት ማምራት ጀመሩ። ቀን መንገድ ላይ እያረፉ፤ እየበሉ እና እየጠጡ እንዲሁም ሌሊት እና ምሽት ላይ እየነዱ ሸዋሮቢት ደረሱ። ሸዋሮቢት ሌላኛው ጓደኛቸው ታርጋ አዘጋጅቶ እየጠበቃቸው ነበር። ታርጋውን ከቀየሩ በኋላ ባጃጅዋን ወልዲያ ወስደው ማሽከርከር እንደሚችሉ እርግጠኞች ሆኑ። አሁን ይበልጥ እንደፈለጉት ባጃጁ የእነርሱ መሆኑ አስደሰታቸው።
እንደተለመደው ሸዋ ሮቢትም ሲዝናኑ ቆይተው አብረው በሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በባጃጁ ከሸዋሮቢት ወጥተው ወደ ወልዲያ ሊሔዱ ተነሱ። ሁለቱም ወልዲያ ገብተው የሚያገኙትን ገንዘብ በማሰብ ፊታቸው ላይ ደስታ ይነበባል። ሆኖም አንድ ያላሰቡት ሁኔታ ተከሰተ።
በግምት ከቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ አስቆማቸው። ፖሊስ ያስቆማቸው ተጠራጥሮ ነው። ባጃጁን ከዚህ በፊት ሸዋሮቢት አካባቢ አይቶት እንደማያውቅ ርግጠኛ ነው። ፖሊሱ እነፍቃዱ ደርበው ከባጃጁ እንዲወርዱ አዘዛቸው። እነፍቃዱ እየፈሩ ከባጃጁ ወረዱ። ርቀው እንዲቆሙ ከነገራቸው በኋላ ፖሊሱ ባጃጇን መፈተሽ ጀመረ።
ፖሊሱ በባጃጁ ከኋላ መቀመጫ ጀርባ ቢላዋ ታየው፤ ወንጀል መፈፀሙን የሚያረጋግጥ ከባድ ማስረጃ አገኘ። ፍቃዱ ደርበው እና አያልሰው ፍቃዱ ተሾመን የወጉበትን ቢላዋ መንገድ ላይ ሳይጥሉት በመቅረታቸው በባጃጁ ውስጥ የተገኘው ቢላዋ ለእነርሱ መያዝ ምክንያት ሆነ። ወልዲያ ለመድረስ ያለመው የወንበዴ ቡድን ከመንገድ ላይ ቀረ። ጉዞ ወደ ወልዲያ ሳይሆን እዛው ሸዋሮቢት ቀሩ። የቢላዋውን መገኘት ተከትሎ ወዲያው ቡድኑ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የወንጀሉ ዝርዝር
ፖሊስ ምርመራ ማካሔድ ጀመረ። መረጃ እና ማስረጃውን አሰባስቦ ድርጊቱን እንደፈፀሙ አረጋግጦ ለዐቃቤ ሕግ አቀረበ። ዐቃቤ ሕግም የወንጀሉን ዝርዝር አዘጋጅቶ ክስ ለመመስረት ለፍርድ ቤት አቀረበ። በወንጀል ዝርዝሩ እንደተብራራው፤ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና 671/2/ ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል።
የ24 ዓመት ዕድሜ ያለው ፍቃዱ ደርበው የመኖሪያ አድራሻው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር አዲስ እንዲሁም፤ አያልሰው አባይ አለሙ ዕድሜው 24 ዓመት ሲሆን የሚኖረው በተመሳሳይ መልኩ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 የቤት ቁጥር አዲስ የሚል አድራሻ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ወጣቶች ተገቢ ያልሆነ ብልፅግናን ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፤ በሐምሌ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ባጃጅ በኃይል ለመስረቅ ተስማምተው እና ተዘጋጅተው ተንቀሳቅሰዋል።
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ጉልት በሚባለው አካባቢ በመሔድ ሟች ፍቃዱ ተሾመን ይነዳት የነበረውን ንብረትነቱ የዘነበ ጎሽዬ የሆነውን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-23956 ባጃጅ ተኮናትረው ወደ ቆሬ እንዲወስዳቸው ተስማምተው ተሳፍረዋል። በኋላም ሁለቱም ከሟች ኋላ በመቀመጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ልዩ ቦታው ባቱ ኮንዶሚኒየም ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ 1ኛ ተከሳሽ ፍቃዱ ደርበው ውጋው ብሎ ለአያልሰው በምልክት ነግሮታል። 2ኛ ተከሳሽም አስቀድመው አዘጋጅተውት በነበረው ቢላዋ ፍቃዱ ተሾመን አንገቱን ሲወጋው 1ኛ ተከሳሽ ፍቃዱ ሟች ፍቃዱ ተሾመ ራሱን እንዳይከላከል በለበሰው ልብስ አንገቱ ላይ አንቆ ይዞታል።
አያልሰው ማለትም 2ኛ ተከሳሽ በድጋሚ ሟችን ትከሻው አካባቢ ሲወጋው፤ ሟች ከባጃጁ ወርዶ አስፓልት ዳር ወድቆ ብዙ ደም ፈሶት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል። 1ኛ ተከሳሽ ባጃጁን እየነዳ ወደ ወልዲያ ወስደው ለመሸጥ አስበው እየተጓዙ እያለ ሸዋሮቢት ሲደርሱ፤ ሌላኛው ተከሳሽ የባጃጅ ሰሌዳ አስቀምጦላቸው አብረው ወደ ወልዲያ እየሔዱ በሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5፡00 ላይ ጨፋ ሮቢት ሲደርሱ ፖሊስ ይዟቸዋል።
በመጨረሻም ፖለስ ባጃጁ ሲፈተሽም ሟችን የወጉበት ቢላዋ የተገኘ ሲሆን፤ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆናቸው ተከሰዋል በማለት የክስ ዝርዝሩ ያብራራል።
ማስረጃ
እነፍቃዱ ደርበው በፈፀሙት ወንጀል ተከሳሽ ሆነው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የተለያዩ ማስረጃዎች ቀርበውባቸዋል። 14 የሰው ምስክር ፍርድ ቤት ቀርበው የመሰከሩ ሲሆን፤ ተከሳሾቹ የሰጡት የእምነት ክህደት ቃል፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አቤት ሆስፒታል በነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥር ጳሀ8/708 የተፃፈ እና የተሰጠ መረጃ የቀረበ ሲሆን፤ በተፃፈው ደብዳቤም የሟች አስክሬን የምርመራ ውጤት ቀርቧል። የወንጀሉን አፈፃፀም እንዲሁም ሟች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የሚያሳይ እና በክሱ ላይ የተገለፀው ባጃጅ በፎቶ ቀርቧል።
ውሳኔ
ተከሳሽ እነፍቃዱ ደርበው ደምሴ በከባድ የውንብድና እና ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ፤ የልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በመጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም ክስና ማስረጃው ከሕግ ጋር አገናዝቦ የወንጀል ፈፃሚዎቹን ያርማል ሌሎችን ያስተምራል ብሎ ባተመነበት እያንዳንዳቸው በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም