የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን ያሟላው የኮሪደር ልማት

ዜና ሐተታ

አዲስ አበባ ከተማን እንደስሟ ውብ ለማድረግ እየተተገበሩ ካሉ ሥራዎች መካከል አንዱ በተመረጡ የከተማዋ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የመንገድ ኮሪደር ልማት ግንባታ ነው። የኮሪደር ልማቶቹ ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነትን ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።

የኮሪደር ልማቶቹ አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የብስክሌት እና እግረኛ መንገዶች፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን ታሳቢ ያደረጉ እና ሌሎችም ዘርፈ-ብዙ ጉዳዮችን አካተዋል። በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከል ፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ ቦሌ፣ መገናኛ፣ ሜክሲኮ እና ሲኤምሲ ይገኙበታል።

የምዕራፍ ሁለት የኮሪደር ልማት ደግሞ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞችን ያካተተ ነው። ስማርት ሲቲ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የተደገፈ የከተሞችን አሠራር መረጃን ለመለዋወጥ የሚያስችሉ ፈጣን የዳታ ትንተና የሚይዝ ነው።

የቦሌ-መገናኛ ኮሪደር ልማት ላይ የተገጠሙ ቴክኖሎጂዎችን በሚመለከት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ እንደተናገሩት፤ የሃገራችንን የመንገድ ሥራ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ግንባታ በቦሌ መገናኛ ኮሪደር ልማት ተከናውኗል ብለዋል።

በቦሌ መገናኛ ኮሪደር ልማት ወደፊትን ታሳቢ ያደረጉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ ውለዋል ያሉት አቶ ጥራቱ፤ በልማቱ የመንገድ ላይ መብራቶቹ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ፣ የደኅንነት ካሜራ፣ የሚለዋወጡ መብራቶች፣ ከአንድ ማዕከል መቆጣጠር የሚያስችል መሣሪያዎች እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እንዳሉት ነው የገለጹት።

በቦሌ መገናኛ ኮሪደር ልማት ከመጀመሩ በፊት ጨለማ፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ አለመኖሩን አንስተው፤ ከዚህም በላይ ዝቅተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንደነበር ተናግረዋል። አሁን ላይ የመንገድ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ በማጠናቀቅ ስማርት ሲቲን ያሟላ መንገድ ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል ነው ያሉት።

የኮሪደር ልማቱ አራት ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን አንስተው፤ ይህም 10 መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማሳለፍ የሚችል መንገድ በመሆኑ የከተማዋ ትልቁ የመንገድ ስፋት የያዘ መሆኑን አስረድተዋል። መሥመሩ በቦሌ በኩል የሚገቡ ዓለም አቀፍ የእንግዶች መቀበያ መንገድ ነው በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበረውን በማፍረስ እንደገና ተስፋፍቶ ተሠርቷል ብለዋል።

በተለይም መሠረታዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማሳለጥ፣ የትራፊክ ፍሰት ሥርዓቱን ለማዘመን፣ በመንገድ ደኅንነት፣ በወንጀል፣ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን መከላከል፣ የአምቡላንስ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍና ለማዘመን አገልግሎቱን ከአንድ ማዕከል መስጠት የሚያስችሉ እጅግ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንደዋሉም ነው የገለጹት።

የኮሪደር ልማት ሥራው በቀን 24 ሰዓት በሳምንት ሰባቱንም ቀናት እንዲሠራ የቅርብ ክትትል በመደረጉ ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል ነው ያሉት።

አዲስ አበባን ከወረዳ እስከ ማዕከል ማራኪና ሳቢ፣ ቀልጣፋ የአሠራር ሥርዓት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀምም ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ዕውን በማድረግ፣ ለነዋሪዎቿ ምቹና ተመራጭ ከተማን የመገንባት እሳቤ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ለከተማዋ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶቹ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የፌዴራል እና የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ተቋማት ድጋፍ እና አጋርነት ለፕሮጀክቶቹ መፋጠን የራሱ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገጽታዋን ማሻሻልና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

መገናኛ የሚገኘው የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድ በ45 ቀናት ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋል ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ሥራው ከተጀመረ ሦስተኛ ቀኑን መያዙንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማው ከተማችንን ለመኖር ምቹ ማድረግ፣ ማደስ፤ ገጽታዋን ማሻሻል እና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነውም ብለዋል።

ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በአጠቃላይ 2,817 ሄክታር መሬት በሚሸፍን እና 132 ኪሎ ሜትር ርዝመት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You