ትኩረት የሚሹት የኢትዮጵያውያን የቤት ሥራዎች

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ገበታ ለትውልድና ለሀገር፣ የሌማት ትሩፋት፣ ኮሪደር ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣የክረምት በጎ አድራጎትና የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ተግባር በመግባታቸው ውጤቶች ታይተዋል።

በድህነት ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ለማሻሻል ከሚከናወኑ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያዎች፣ የተለያዩ የኢንቨስትመንትና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ባለፈ ወጣቶች በእራሳቸው ተነሳሽነት የስታርት አፕ አውዱን በመቀላቀል ተስፋ ሰጪ ውጤት እያሳዩ ይገኛል።

በኢትዮጵያ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ምን መሰራት አለበት? የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተፈፃሚነት ምን ይመስላል? በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶች ለሀገራዊ ስኬቶች እንቅፋት እንዳይሆኑ ምን መሰራት አለበት? ግጭቶችን ለመፍታት ምንስ እየተሰራ ነው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሞጋ አባቡልጉ ለኢፕድ እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሃሳብና የተግባር አንድነት መገንባት፤ ጠንካራ የስራ ባህል ማዳበር እንዲሁም ግጭቶችን በምክክር በመፍታት የሕዝብ አንድነትን መፍጠር ይገባል።

በሀገሪቱ እየታየ ላለው እድገት የማህበረሰቡን ግንዛቤ መፍጠር፤ የመጣውን እድገት ማመን፤ የተሰራውን ስራና የተገኘውን ለውጥ መቀበል፤ ለሃሳብና ለተግባር የአንድነት መንፈስ መገንባት፤ ቁርጠኝነትን ማሳደግ፤የታቀደውን እቅድ ለማስፈፀም በቆራጥነት መነሳት፤ ብሔርተኝነትን ማስወገድ፤ ግጭትን በምክክር መፍታት እና ሰላምን ማስፈን የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል ዋነኛ መሆኑን ይገልጻሉ።

በሀገሪቱ ሁለተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ሊኖር እንደማይገባ በመግለፅ፤ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ከቀረ እድገትን ለማምጣት እየተሰራ ያለው ስራ በተፈለገው ፍጥነት ልክ እንዳይሄድ እንደሚያደርገው ይጠቅሳሉ።

በሌማት ትሩፋት፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ በገበታ ለሀገር፤ በውጪ ንግድ፤ በቱሪዝም፤ በክረምት በጎ አድራጎት፤ በስንዴ ምርት፤ በማዕድን ምርት፤ በኢንቨስትመንትና በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ያብራራሉ።

እንደ አቶ ሞጋ አባባል፤ የእርስ በርስ ግጭት ለሀገር ሁለተናዊ እድገት እንቅፋት ነው፤ ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮና የሰው ሀብት ያላት ለሁሉም የምትበቃ ሰፊ ሀገር ናት፤ ያላትን ሀብት ሌት ከቀን ሰርቶ መለወጥ እንጂ በተራ ብሔርተኝነት መበላላት አያስፈልግም። ለችግሮች ተቀራርቦ በመነጋገር ወደ አንድ ሀሳብ መምጣት፤ በልዩነቶች ላይ የመነጋገር ልምድ የለም፤ ይህ ደግሞ ወደ ግጭት እየወሰደ ይገኛል። ተቀራርቦ በመነጋገር እና በመግባባት የሕዝብ አንድነትን መገንባት ያስፈልጋል።

ሌላኛዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ አልማዝ አሰሌ በበኩላቸው፤ ከቅርብ አመታት ወዲህ መንግሥት የሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የክረምት በጎ አድራጎት፤ የማዕድ ማጋራት፣ የገበታ ለትውልድና ለሀገርና የመሳሰሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ ትልቅ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን ይገልጻሉ።

መንግሥት አቅጣጫዎችንና ፖሊሲዎችን በማስቀመጥ ተግባራዊነታቸውን ተከታትሎ በማስፈፀም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገትን አስመዝግቧል። የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮና የሰው ሀይል ሀብት በሙሉ አቅም መጠቀም፤ በትብብር፣ በቅንጅት፤ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።

መንግሥት ፕሮጀክቶችን ተፈፃሚ በማድረግ በኩል ፈጣን ስራ እየሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ ፕሮጀክቶችን በጊዜና በወቅታቸው ሰርቶ በማጠናቀቁም የሚታይ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን ያስረዳሉ። እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችንም አጠናክሮ ለማስቀጠል የተጀመሩ የልማትና የእድገት ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚያስፈልግ ያብራራሉ። በተጨማሪም የሃሳብና የተግባር አንድነትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ያመለክታሉ።

የሀገርን ሁለተናዊ እድገት ለማሳካት በሚደረግ ግብግብ ውስጥ የሚገጥም ተግዳሮት አለ፤ በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች ፈተናዎች ናቸው። ፈተናዎችን ፈትቶ ሰላምን ለማስፈንና እድገትን ለማስቀጠል መንግሥት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው። በተጨማሪም የምክክር ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በኮሪደር ልማት፤ በሌማት ትሩፋት፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ በማዕድን ምርት፣ በስንዴ ምርት፤ በውጪ ንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በመሰል ዘርፎች ትልቅ ስኬት ተመዝግቧል፤ የተመዘገበውን እድገት ለማስቀጠል ሀገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሀይል ሙሉ ለሙሉ መጠቀም፤ ግጭትን ማስወገድ አስፈላጊ ነው ያሉት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ታደለች አማረ ናቸው።

ኢትዮጵያ በብዙ ነገሮች ባለፀጋ የሆነች ሀገር ናት። በተለይ የተፈጥሮና የወጣት የሰው ኃይል ሀብት ተጠቃሽ ነው። ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት፣ ወጣት ኃይሏንም አስተባብሮ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ሀገራዊ መግባባት የሚያስገኘውን ሁለንተናዊ ትሩፋት በማሰብ ግጭትን ማስወገድና ለጋራ እድገት በጋራ የመቆም እሴትን ማዳበር እንደሚገባም ያመለክታሉ።

መንግሥት እያስመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተጨማሪም በምክክር ኮሚሽን ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረው ጥረት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በየተመረጡበት አካባቢ በመሄድ ሀገራዊ መግባባት እንዲመጣ እያደረጉት ያለው አስተዋፅኦ መቀጠል እንዳለበት ይገልጻሉ።

ታደሠ ብናልፈው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/ 2017 ዓ.ም

Recommended For You