አዲስ አበባ፡- ቻይና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለምትሰራቸው ስራዎች ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች፡፡ አሊባባ ኩባንያ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የዲጂታል ተሰጥኦ አካዳሚ እንደሚገነባ ይፋ አድርጓል።
የቻይናው አሊባባ ግሎባል ኢኒሼቲቭስ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ አሶሴሽን በጋራ በመሆን የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በትናንትናው እለት አዘጋጅተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የምጣኔ ሀብትና የንግድ ጉዳይ ሚኒስትር ካውንስለር ያንግ ዪሃንግ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚዋን ለማጎልበት እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ግብይቷን ለማሳደግ በምትሰራው ስራ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡
ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እየሰራች መሆኗንና ይህም የሚበረታታ መሆኑን ያነሱት ያንግ ዩሃንግ፤ ሀገሪቱ በዘርፉ ከቻይና ጋር ያላት ጥምረት ይበልጥ እየጎለበተ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቱክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መንግሥት በኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከነዚህ ስራዎች ውስጥ ዓለም አቀፍ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን ወደ ሀገር የማስገባት ስራ አንዱ ነው ብለዋል፡፡
አሊባባን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የዲጂታል አካዳሚ ለመክፈት ማሰቡ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ስኬት ማሳያ ነው ያሉት ዶክተር ይሽሩን፤ አካዳሚው ወጣቱን በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጥን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳመላከቱት፤ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ለንግድ ብቻ ሳይሆን በዲጂታል ግብይት ሥርዓቱ ላይ ለወጣቱ የስራ እድል ለመፍጠርም ጭምር ነው፡፡
አሊባባ ለማቋቋም ያሰበው ዓለም አቀፍ የዲጂታል አካዳሚ በኤሌክትሮኒክስ ግዢ ላይ የፈጠራ ስራ ለሚሰሩ ዜጎች ጥሩ እድል ይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአሊባባ ኩባንያ ከፍተኛ አማካሪ ዳን ሊኡ በበኩላቸው፤ ኩባንያው የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ 11 ሀገራት ጋር እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
ኩባንያው በኢትዮጵያ ወደ ስራ ሲገባ በኤሌክትሮኒክስ ግዢው ዘርፍ በርካታ ስራ ፈጣሪዎችን በሀገሪቷ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ለማስፋፋት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማገዝ አሊባባ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ግሎባል ዲጂታል አካዳሚ ለመክፈት እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን በዲጂታል የግብይት ሥርዓት ላይ ያተኮረ ስልጠና በቻይና እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ሲወስዱ መቆየታቸውንና አሁን የሚቋቋመው ግሎባል ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አካዳሚ በሀገር ውስጥ ስልጠናውን መስጠት የሚያስችል መሆኑን በመድረኩ ገልጸዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥቅምት 20 ቀን 2017 ዓ.ም