ኢትዮጵያዊው የረጅም ርቀት ኮከብ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የዓለም ግማሽ ማራቶን ክብረወሰንን አሻሽሏል። የ2024 ቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ትናንት ሲካሄድ ወጣቱ ድንቅ አትሌት ርቀቱን በ57:30 ሰዓት በማጠናቀቅ ክብረወሰኑን በእጁ አስገብቷል። ያጠናቀቀበት ሰዓትም ቀድሞ የዓለም ክብረወሰን ከነበረው ሰዓት በአንድ ሰከንድ የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል።
የርቀቱ የቀድሞ የዓለም ክብረወሰን ከሦስት ዓመት በፊት 2021 ላይ በሊዝበን ግማሽ ማራቶን በዩጋንዳዊው ኮከብ አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ የተመዘገበ ሲሆን ሰዓቱም 57:31 እንደነበር ይታወሳል።
በዝናባማ የአየር ፀባይ የተካሄደው ውድድር የሙቀት መጠኑን ቢያረግበውም የነበረው ወበቅ ለአትሌቶች ምቹ እንዳልነበረ የዘገቡ መገናኛ ብዙኃን ዮሚፍ የቫሌንሲያ ጎዳናዎች ፈተና ሳይበግረው አዲስ የዓለም ክብረውን ጨብጧል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀውለታል።
በውኃ የተጥለቀለቁ የቫሌንሲያ ጎዳናዎች አሯሯጮችን በእጅጉ ፈትነው ከአራት ኪሎ ሜትር በኋላ ወደፊት መግፋት አልቻሉም። በዚህ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ዮሚፍ ሌሎች አትሌቶችን አስከትሎ አምስት ኪሎ ሜትሩን 13:38 በሆነ ሰዓት አገባዷል። ይህ ግን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለማሻሻል በቂ አልነበረም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያኑ ገመቹ ዲዳ እንዲሁም የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር ባለድሉ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከኬንያውያኑ አትሌቶች ቪንሰንት ላጋትና ኢሳይ ኮይች ጋር ውድድሩን በማፍጠን 10 ኪሎ ሜትሩ በ27:12 ደቂቃ ሊገባደድ ችሏል።
አስራ አምስት ኪሎ ሜትሩ በ40:56 ከተገባደደ በኋላ ዮሚፍ ከተፎካካሪዎቹ አትሌቶች ተነጥሎ ፍጥነቱን በመጨመር በመጨረሻ ባደረገው ትግል የዓለም ክብረወሰኑን ለማሳካት በቅቷል።
ዮሚፍን ተከትለው የሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ኬንያውያን አትሌቶች አጠናቀዋል። ዳንኤል ማቲኮ 58:17 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሲሆን ኢሳይ ኮይች በሦስት ሰከንድ ዘግይቶ ቀጣዩን ደረጃ በመያዝ አጠናቋል። ኢትዮጵያዊው ገመቹ ዲዳ ደግሞ በ58:39 ሰዓት አራተኛ ሆኖ ፈፅሟል።
በሴቶች መካከል በተካሄደው ተመሳሳይ ውድድር የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባይመዘገብም በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈች አትሌት ፈጣን ሰዓት ተመዝግቧል። የመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሯን ያደረገችው ኬንያዊቷ አትሌት አግኒስ ንጌቲች ቀዳሚ ሆና ባጠናቀቀችበት ፉክክር 1:03:04 ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። ይህም ሰዓት በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሮጠች አትሌት የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት ሲሆን በርቀቱ ታሪክም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት መሆን ችሏል።
ኬንያዊቷ ባለድል ላስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት በረጅም ርቀት ተስፋ የተጣለባት ኮከብ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ውድድሩ ከመጀመሪያ አንስቶ በማፍጠን ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራት። ኬንያዊቷ አትሌትና እጅጋየሁ በተለይም አስረኛው ኪሎ ሜትር እስኪገባደድ ድረስ አስደናቂ ፉክክር በማድረግ የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን የመስበር ዕድል ነበራቸው። ብርቱው ፉክክር እስከመጨረሻ ባለመቀጠሉ ግን 2021 ላይ በዚሁ በቫሌንሲያ ማራቶን ለተሰንበት ግደይ ያስመዘገበችው 1:02:52 የሆነው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ሳይሻሻል ቀርቷል።
እስከ ውድድሩ አስራ አምስተኛ ኪሎ ሜትር ድረስ ድንቅ ፉክክር በማድረግ የማሸነፍም እድል የነበራት እጅጋየሁ ታዬ በመጨረሻ በመዳከሟ ደረጃ ውስጥ መግባት አልቻለችም። 1:04:14 በሆነ ሰዓት አራተኛ ሆና ፈፅማለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ወጣት አትሌት ፎይተን ተስፋዬ ግን በመጨረሻ ባሳየችው ድንቅ ብቃት ርቀቱን 1:03:21 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆናለች። ኬንያዊቷ ሊሊያን ካሴይት ደግሞ 1:03:32 በማጠናቀቅ ሦስተኛውን ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም