የእናቶችን ሞት መቀነስ የሚያስችሉ የምርምር ጽሑፎች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእናቶችን ሞት በአምስት ሺህ መቀነስ የሚያስችሉ የምርምር ጽሑፎች ይፋ አደረገ፡፡

ኢንስቲትዩቱ እናቶች በቅድመ ወሊድና ከወሊድ በኋላ ለሚገጥማቸውና ለሞት ለሚዳረጉበት የደም መፍሰስ ችግር መፍትሔ ይሆናል የተባለ የተለያየ የምርምር ጽሑፍ ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፎቹን በውይይት ለማዳበር በተዘጋጀ መርሐ ግብር መክፈቻ ላይ የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዶክተር አደራጀው መኮንን እንደተናገሩት፤ ይፋ የሆኑት ጥናታዊ ጽሑፎች በተለያዩ አራት ተመራማሪዎች የተጠኑና በጤናው ዘርፍ ለውሳኔ ሰጪ አካላት ቀርበው ለውሳኔ አሠጣጥ የሚረዱ ናቸው፡፡

ጥናታዊ ጽሑፎቹ በኢንስቲትዩቱ የሥርዓተ ጤና ምርምር ዳይሬክቶሬት መጠናታቸውን የጠቆሙት ዶክተር አደራጀው፤ የሀገራችንን የጤና ሥርዓት ለማሳደግና ለማበልፀግ ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ንድፈ ሃሳቦችን ለውሳኔ ሰጪው አካል አዘጋጅቶ ማቅረብ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በእርግዝናና ወሊድ ወቅት እናቶችን ለሕልፈት በመዳረግ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው የጤና ሕመሞች በመቀነሱ ረገድ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን የጠቀሱት ዶክተር አደራጀው፤ ሆኖም አሁንም የዓለም ጤና ድርጅት በ2030 ለመድረስ ካስቀመጠው ግብ አንፃር የሚፈለገውን ያህል አለመድረሱን ጠቁመዋል፡፡

አራቱ ጥናታዊ ጽሑፎች ለውሳኔ ሰጪው አካል ደርሰው ሲተገበሩ የእናቶችን ሞት በከፍተኛ መጠን የሚቀንሱና የዓለም ጤና ድርጅት በ2030 ለመድረስ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያስችላሉ ተብሎ በመታሰብ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከወሊድ በፊትና በኋላ የሚከሰት ከተገቢው መጠን ያለፈ የደም መፍሰስ፤ ውርጃ፣ ረዥም ምጥ፣ የማህፀን መተርተር እናቶችን ለሞት ከሚዳርጉ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውንም አመልክተው፤ ጥናታዊ ጽሑፎቹ ለእነዚህ የእናቶች ጤና ችግሮች መፍትሔ በሚሆኑበት ዙሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉንና ገንቢ ግብዓቶች ማሰባሰብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስን አስመልክተው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የዕውቀት ሽግግርና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ ፊርማዬ ቦጋለ በበኩላቸው፤ የእርግዝና እና የወሊድ ወቅት በተለይም ከወሊድ በኋላ የሚከሰት ደም መፍሰስ በአሁኑ ወቅት እናቶችን ለሕልፈት ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ100 እናቶች ውስጥ ከአራት እስከ ስድስት የሚደርሱት ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም ለደም መፍሰስ አደጋ ሊጋለጡና ሕይወታቸውንም ሊያጡ ይችላሉ ያሉት ተመራማሪዋ፤ በተደጋጋሚ ማርገዝ፣ ከአምስት በላይ ልጅ መውለድ፣ የሚወለደው ልጅ የክብደት መጠን፣ የእንግዴ ልጅ ቅሪት በማህፀን ውስጥ መቅረት እናቶችን ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የደም መፍሰስ የሚያጋለጡ እንደሆኑም አመልክተዋል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፋቸው እነዚህን የእናቶች የጤና ችግር ለመቀነስ እንደ ዓለም የጤና ድርጅት፤ እንደ ጤና ሚኒስቴር፤ እንደ ኢንስቲትዩቱ እየተሠራባቸው ያሉ ወጥ ተግባራት ላይ ተደማሪ መፍትሔ የሚያመጣ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የፖሊሲ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሁለት መፍትሔዎችን ስለማስቀመጡም የጠቀሱት ተመራማሪዋ፤ ጥናቱ የእናቶች ሞትን አሁን ካለበት ስምንት ሺህ 321 ወደ አምስት ሺህ መቀነስ ያስችላልም ብለዋል፡፡

በመድረኩ ከዚህ በተጨማሪ የእናቶችን ህይወትን ለመታደግ የሚረዱ ስልቶች እና መንገዶች የሚጠቁም እና የማህጸን በር ካንሰር ምርመራን በማሻሻል ሞትን መቀነስ የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በውይይት ዳብረዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You