ሳይንስ ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ስራዎች መፍለቂያ ነውና ተመራማሪዎች በአካባቢያቸውና በማህበረሰቡ ውስጥ የተመለከቱት ችግር ለመቅረፍ ጥረት ያደርጋሉ።እነዚህ የፈጠራ ስራዎች በፈጣሪዎቹ አዕምሮና የፈጠራ ክህሎት ልክ ለልዩ ልዩ ግልጋሎት ይውላሉ።በተለይም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ትኩረት በማድረግ የምርምርና የፈጠራ ስራ መስራት ፋይዳው ከፍተኛ ነው።በፈጠራ ስራ አካል ጉዳተኞችን የሚረዱና እገዛ የሚያደርጉ መሳሪያዎችን በምርምር ማግኘትና ተግባራዊ ማድረግ አገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
አንዳንዴ ወጣቶች ከእድሜያቸው በላቀ መልኩ ለአገራቸው መልካም ተግባር ሲሰሩና የማህበረሰባቸውን ችግር ለመቅረፍ ሲታትሩ ሲታይ አገሪቱ በተተኪ ትውልድዋ መልካም ተስፋና ብሩህ ራዕይ ለመሰነቅዋ ምስክር መሆን ያስችላል።ዛሬ በሳይንስ አምዳችን ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን አዲስ ዲዛይንና ሞዴል መኪና በግል ምርምርና ጥረቱ ተግባራዊ ያደረገ ወጣትና የምርምር ስራው ምንነት ላይ ያጠናቀርነውን ፅሁፍ በዚህ መልክ አቅርበንላችኋል።
ትውልድና እድገቱ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን አረካ ከተማ ነው።ገና የ18 ዓመት ወጣትና የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነው ወጣት አጃዬ ሞደር።በምርምር ስራ ዘርፍ ለአገሩ ብዙ አበርክቶን ለመወጣት በአፍላ እድሜው ተግቶ በመስራት ላይ ይገኛል።መልካም ወላጅ ለልጁ ትልቅ ቦታ መድረስ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው።ይሄም በወጣት አጃዬ ቤተሰብ በእውን ታይቷል።የብረታ ብረት ስራ መተዳደሪያቸው ያደረጉት የወጣት አጃዬ አባት አቶ ሞደር ለወጣቱ አጃዬ ወደ ምርምር ስራ ለመግባት መሰረት ጥለውለታል፡፡
አጃዬ ልጅ እያለ የወዳደቁ እቃዎችን በመቀጣጠል ለጥቅም እንዲውሉ እየጣረ፣ አዳዲስ ነገሮችን እየሞከረና እየፈጠረ ከትምህርቱ ጎን ለጎን ብርቱ ጥረት ያደርግ ነበር።አጃዬ ዛሬ ላይ በአይነቱ አዲስ የሆነና በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን መኪና በራሱ ዲዛይን በመስራት እና አገልግሎት ላይ በማዋል በ2011 በተካሄደው የፈጠራና ምርምር ስራ አገር አቀፍ ውድድር ተካፍሎ በኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሽልማትን አግኝቷል።
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ አጃዬ የፈጠራ ስራው ለመስራት ያነሳሳው አካል ጉዳተኞች እንደሌላው የህብረተሰብ ክፍል ወደፈለጉበት ቦታ ለመድረስ የሚያስችላቸው መሳሪያ ወይም አጋዥ ቁስ የሌላቸው በመሆኑ ነው።ይህን ችግራቸውን በመገንዘቡ በቀላሉ የሚጠቀሙበት፤ ያለ ችግር የፈለጉበት ቦታ እየሄዱ፤ እንደ ሌላው ሰው የሚፈልጉትን እንዲያሳኩ የመፈለግ ብርቱ ምኞት ውስጡ አደረ፡፡
ይህ በጎ ፍላጎት ያላሰለሰ ጥረትና ወገናዊ ተቆርቋሪነት ለምርምር ስራው በር ከፈተለት ሁሌም የተለያዩ ዲዛይኖችን በመሞከር አባቱ የሚሰሩት ብረታ ብረት መስሪያ ቦታ በመሄድና በመሞከር በብዙ ጥረትና ትጋት ቀድሞ ያሰበው ውጥኑን ማሳካት ቻለ።በአይነቱ አዲስ የሆነና በአካል ጉዳተኞች በቀላሉ ሊነዳ የሚችል አዲስ ሞዴል ተሽከርካሪ መኪና መፍጠር ቻለ፡፡
ይህ ለአካል ጉዳተኞች እንዲሆን በልዩ ዲዛይን የሰራው መኪና ከመኪናው ሞተር ውጪ ሙሉ በሙሉ የተሰራው በተመራማሪው ነው።ተሸከርካሪው ሰው የመጫን አቅሙም ከ4 እስከ 4 ሰው በምቾት ማሳፈር ይችላል።ለምርምር ስራው ተደጋጋሚ ሙከራና ከወጣቱ ኪስ ከፍ ያለ ገንዘብ እና አቅም የላቀ ጥረት ትዕግስት እንደጠየቀው ተመራማሪው ያስረዳል።
የተመራማሪ አጃዬ የፈጠራ ስራ የሆነው ተሽከርካሪ በሊትር እስከ 40 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችልና ከአካል ጉዳተኞች በተጨማሪ ማንኛውም ሰው ሊያሽከረክረው የሚችል መሆኑ፤ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ሞዴል ያለው በተለየ ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን መኪና በአገር ውስጥ አለመሠራቱ አዲስ እንደሚያደርገውና በዋጋው አሁን ካሉት ሌሎች መኪኖች እጅግ ያነሰ መሆኑን የፈጠራ ባለሙያው ይገልፃል፡፡
ቀድሞ ያሉ መኪኖች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው እንዳልተሰሩና ለማሽከርከር እንደሚቸገሩ፤ አሁን የራሱ የፈጠራ ስራ የሆነው አዲስ ሞዴል ተሽከርካሪ ይህንን የአካል ጉዳተኞች ችግር እንደሚቀርፍ ይናገራል።ከሞተሩ በቀር ሙሉ የመኪናው አካል በተመራማሪው የተሰራው ይህ በተለይ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ተደርጎ የተሰራው ተሽከርካሪ በአዲስ ዲዛይን ከባለ ሁለት እግር ሞተር ላይ “ሞተር” በመውሰድ እና በመግጠም የተሳካ ውጤት ማግኘት አስችሎታል።
የምርምር ስራው የተለያዩ እውቅናና ሽልማት ያስገኘለት ሲሆን፤ የዘንድሮው የፈጠራና የምርምር ስራ አገራዊ ሽልማት ላይ ቀርቦ በኢትዮጵያ
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ነው።ከእዚህ በተጨማሪም ለመኪናው ተጨማሪ ዲዛይን ማስተካከያና የተሻለ አድርጎ መስራት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደተበረከተከለት እና አሁንም የምርምር ስራው በሚፈልገው ፍጥነትና መልክ ማድረግ የሚያስችለው በቂ ባይሆንም የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገለት መሆኑ ይገልፃል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ተመራማሪው ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በራሱ ጥረት በሰራውና በብዙ ልፋት ከስኬት ካበቃው መኪና በተሻለ ዲዛይንና ከበፊቱ የዲዛይንና የሞዴል ማስተካከያ ያደረገለት መኪና በመስራት ላይ መሆኑ የሚናገረው ወጣት አጃዬ መኪናው ከ90 በመቶ በላይ ስራው መጠናቀቁን ይገልፃል።በራሱ ክህሎትና የፈጠራ አቅም በተሻለ ሞዴል በመስራት ላይ የሚገኘው አዲሱ ተሽከርካሪ 10 ሰዎችን የመጫን አቅም እንዳለውና አሁን ከተማ ላይ ከውጪ አገር ተገዝተው እየመጡ የታክሲ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ታክሲዎችና ባጃጅ ተሽከርካሪዎች መተካት እንደሚችል ይገልፃል፡፡
ገና ከጅምሩ የፈጠራ ስራው ሀሳብ ከመፀነሱ ጀምሮ ውጤት ላይ ለመድረስ ብዙ ጊዜ እንደፈጀበት የሚገልፀው ወጣት አጃዬ፤ የፈጠራ ስራው የሆነው ይህ መኪና ከ150 ሺ እስከ 200 መቶ ሺህ ብር በሆነ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ እንዳቀደና ይህ ዋጋ ሌሎች ገበያ ላይ ካሉ መኪኖች በእጥፍ እንደሚቀንስና አካል ጉዳተኞች ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር በማየት ዋጋው አስተያየት በማድረግ የቀረበ መሆኑን ያስረዳል፡፡
የምርምር ስራው ሲጀምር ከተማሪነቱ ጎን ለጎን የተለያዩ መኪና ላይ የሚለጠፉ እስቲከሮች ዲዛይን በማድረግና በመሸጥ ባጠራቀመው ገንዘብ ለፈጠራ ስራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ይገዛ እንደነበረና በወጣትነቱ የፈጠራ ስራው እንዲሳካ ማድረግ ያለበትን ብዙ መስዋዕትነት እንደከፈለ ይገልፃል።የምርምር ስራው ሲሰራ ከሚያስልግ ብርቱ ጥረትና ሙከራ ሲከሽፍ ከሚገጥም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት እና መሰልቸት በመታቀብ ለምርምር ስራው ውጤት መትጋት ወሳኝ ነጥብ እንደሆነ ወጣቱ ተመራማሪ ይናገራል፡፡
ወጣት ተመራማሪ አጃዬ አሁን ከሚሰራው የምርምር ስራ በተጨማሪ ለፊልም ቀረፃ የሚያገለግል ድሮን የተባለ አየር ላይ በመንሳፈፍ ምስሎችን የሚያስቀር መሳሪያ መስራትንና ዲዛይኑን አሻሽሎ ለገበያ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ይናገራል።ምርምር ማድረግና የተመለከትኳቸው ማህበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ሁሌም ጥረት አደርጋለው የሚለው ተመራማሪ ወደፊት የተለዩ የፈጠራ ስራዎችን ለማድረግ እቅድ እንዳለው ያስረዳል፡፡
በአገር ደረጃ ለምርምር ስራ የሚደረገው ድጋፍ እጅግ አነስተኛ መሆኑን የሚናገረው ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ የእርሱ ፈጠራ የሆነው መኪና የራሱ ያላሰለሰ ጥረትና የቤተሰቡ ድጋፍ ባይታከልበት ኖሮ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ መድረስ አይችልም ነበር ይላል።
በተለይ አዲስ የምርምር ስራ የሚያካሂዱ ወጣቶች ለፈጠራ ስራቸው ሙሉ ጊዜና ትኩረት በመስጠት የታዳጊ አገራቸውን ችግር ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለባቸው የሚለው ወጣቱ ባለ ብሩህ አዕምሮው ተመራማሪ የፈጠራ ባለሙያዎች ለሚገጥማቸው ችግር እጅ ሳይሰጡ በትዕግስት ካሰቡበት ለመድረስ እና አላማቸውን ለማሳካት መጣር ዋነኛ ግባቸው ሊሆን እንደሚገባ ይመክራል።
ተመራማሪው በሚኖርበነት ቀበሌና አካባቢ ወጣቶች ብዙ የምርምር ስራዎች እንደሚሰሩ የሚናገረው አጃዬ፤ ወጣቶቹ የምርምር ስራቸው ድጋፍ በማጣትና ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡበት አጋጣሚ በማጣታቸው ምክንያት ስኬታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ ይገልፃል።ለዚህም ፈጠራን ለማበረታታት ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን በያሉበት እያደነ የፈጠራ ስራቸው ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል በማለት በወጣትነቱ በታደለው ንቁ አዕምሮ በጎ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2011
ተገኝ ብሩ