አዲስ አበባ፡- የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።
በሴቶች የመሬት ይዞታ መብት ላይ ያተኮረ “ለሴቷ መሬት እንቁም” (Stand For Her Land) የተሰኘ የውይይት መድረክ በትናንትናው እለት ተካሂዷል። በመድረኩ በቅርቡ የጸደቀው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት ስዩም በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አዲሱ የገጠር መሬት አስተዳደር አዋጅ ከውርስና ጋብቻ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የሴቶች የመሬት አስተዳደር መብቶች ላይ ያተኮረ ነው።
በተለይም በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ያለው ኋላ ቀር አመለካከት ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዳይሆኑ፣ የውርስ መሬት እንዳይካፈሉ እንዲሁም መሬት ቢኖራቸው እንኳን ማስተዳደር እንዳይችሉ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በታሻሻለው አዋጅ በተለይም ሴቶች በውርስ የመሬት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ በግልጽ ተቀምጧል ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ገነት ገለጻ፤ ብዙ ጊዜ አዋጆች ጸድቀው አተገባበር ላይ ችግር አለ፤ ይህን አዋጅም ተግባራዊ ለማድረግ የማህበረሰቡ ባህልና ወግ መሰናክል ሊሆን ስለሚችል በትኩረት መስራት ይገባል።
ስለሆነም የሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብትን ለማረጋገጥ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአዲሱ አዋጅ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 13 ነጥቦች ተካተዋል፤ አዋጁ የሴቶች መሬት ባለቤትነት እድልን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
አዋጁን ወደ መሬት ለማውረድ ሴቶች ላይ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩና በማህበረሰቡ ተሰሚነት ካላቸው አካላት በተለይም ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
መሬት ሀብት ነው የሚሉት ወይዘሮ ገነት፤ ሴት ልጅ የመሬት ባለቤት ካልሆነች ሰብዓዊ መብቷን ለማስከበር ኢኮኖሚዋ ጥቅሞቿን ለማሳደግ ይረዳታል ሲሉ አንስተዋል።
በሀቢታት ፎር ሂውማኒቲ ኢትዮጵያ የስታንድ ፎር ኸር ላንድ ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት ወይዘሮ ናርዶስ እሸቱ በበኩላቸው፤ የውይይት መድረኩ ሴቶች በመሬት ይዞታቸው ላይ የመወሰንና የመጠቀም መብት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል።
አላማውም የተሻሻለውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ለሴቶች ምን አይነት እድል ይዞ እንደመጣ ግንዛቤ መፍጠር ነው ብለዋል።
የነበረው አዋጅ ሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ አልነበረም የሚሉት ወ/ሮ ናርዶስ፤ አዲሱ አዋጅ ግን የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት መብትን በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዋጁ መጀመሪያ ላይ ሴቶች የመሬት፣የንብረት መጠቀምና የማስተዳደር መብትን ለማስጠበቅ የሚረዱ አንቀጾች በዝርዝር መቀመጣቸውን ጠቁመው፤ ይህም ከቀድሞው አዋጅ ጋር ሲነጻጸር ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።
ሕግ ተርጓሚና አስፈጻሚ አካላትም አዲሱ አዋጅ ትኩረት በሰጠው የሴቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በስታንድ ፎር ኸር ላንድ ፕሮጀክት በተደረገ ጥናት ሴቶች የመሬት ባለቤትነት መብታቸው በተለያዩ ምክንያቶች ሲነጠቁ መጠየቅ እንዳለባቸው ግንዛቤው እንደሌላቸውና ሕጉንም አውቀው ወደ ፍርድ በሚሄዱበት ወቅት አፈጻጸም ላይ ክፍተት እንዳለ ማወቅ ተችሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል ባህላዊ አሰራሮች ለወንዶች ያደሉ መሆናቸው ሴቶች በመሬት ባለቤትነት ዙሪያ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸዋል።
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም