የገቢ እቅዱን ለማሳካት የታክስ መሠረቱን ማስፋት፤ ሕገወጥነትንም መከላከል የግድ ያስፈልጋል!

በ2017 በጀት ዓመት መንግሥት የሀገር ውስጥ ገቢን አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊዮን ለማድረስ ታቅዷል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ወደ ታክስ ሥርዓቱ ያልገቡትን በማስገባት፣ አዳዲስ የታክስ አይነቶችን ተግባራዊ በማድረግ፣ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በማዘመንና ታክስ በመሰብሰብ፣ የሚወጣ ወጪን ውጤታማ በማድረግ፣ የታክስ ሥርዓቱንም ወደ ክልሎች በማውረድ ያቀደውን ገቢ ለማሳካት አቅጣጫ ተቀይሶ እየተሠራ ነው።

ምክንያቱም መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገትን የማፋጠን ከፍተኛ ሃላፊነት አለበት። ይሄን ኃላፊነት ለመወጣት ደግሞ የራሱ የገቢ ምንጭ ያስፈልገዋል። በዚህ መልኩ በአንድ ሀገር ለመንግሥታዊ ሥራዎች ማስኬጃ ሀብት የማሰባሰቢያ የገቢ ምንጮች መካከል ዋነኛው ግብር ነው።

ለዚህም ነው በአግባቡ ግብር መሰብሰብ የቻለ ሀገር የተፋጠነ ልማት ማከናወን የሚችለው፤ የተረጋጋች ሀገርንም ሲፈጥር እና አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታንም ሲያረጋግጥ የሚታየው። ይሄ በማድረጉም ልማትን ያስቀጥላል፤ የተረጋጋና ቀጣይነት ያለውን ብልጽግናንም ያመጣል።

ግብር የዜጎች ሁሉ መብትም ግዴታም ነው። በአንድ ሀገር የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር፣ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባሮቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉና በግለሰብ ደረጃ ሊሟሉ የማይችሉና የጋራ መገልገያ የሆኑ እንደ መንገድ፤ ጸጥታና ደህንነት፤ ትምህርትና ጤና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚቻለው አስተማማኝ ግብር ሲኖር ነው።

በአጠቃላይ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት እና የመንግሥታት ሀገር የመምራት አቅም እና ብቃት የሚመዘንበት ብቻ ሳይሆን፤ የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ግስጋሴ የሚለካበትም ቁልፍ ተግባር ነው። በመሆኑም፣ ያለ ግብር መንግሥት ሊንቀሳቀስ፣ ሀገርም ልትለማ አትችልም።

ስለዚህ ግብር መክፈል ለሀገር ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች መረጋገጥ ካለው ፋይዳ አንጻር አስፈላጊ ከመሆኑም ባሻገር በአንዲት ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ግብር መክፈል ግዴታም ጭምር ነው። ይህንም ተግባራዊ አለማድረግ ደግሞ የወንጀልና አስተዳደራዊ ቅጣቶችንም ያስከትላል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ግብር አስፈላጊነትና ግዴታ ከተደነገገው በተጨማሪ በፌዴራል ታክስ አስተዳደርር አዋጅ ቁጥር 983/2008 አንቀጽ 116 እና በተመሳሳይ ድንጋጌዎች ግብርን አለመክፈል፤ ማጭበርበር፣ ግብር መሰወር፣ ቫት ማጭበርበር እና በጠቅላላው ከታክስ ጋር ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎች በእስር እና እንደየ ወንጀሉ ክብደት በብርም የሚያስቀጡ ናቸው። ግብር ማጭበርበርና መሰወር ሕጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ቢሆንም በሀገራችን ከግብር ጋር ተያይዞ በርካታ ወንጀሎች ይፈጸማሉ። ይህ ደግሞ መንግሥት እሰበስበዋለሁ ብሎ ያቀደውን የግብር መጠን እንዳይሰበስብ እንቅፋት ይሆናል።

ለአብነትም የሽያጭ መጠንን ዝቅ በማድረግ የሚፈጸም ግብር መሰወር፤ ግዢን ዝቅ በማድረግ የሽያጭ መጠን እንዲቀንስ እየተደረገ የሚፈጸም የግብር ስወራ፤ የተጨማሪ እሴት ታክስ የተለያዩ የማስከፈያ ምጣኔዎች ያለአግባብ በማቀያየር የሚፈጽም የግብር ስወራ፤ የተሰበሰበን ታክስ (VAT) ለመንግሥት አለመክፈል፤ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕገወጥ መንገድ በማስገባት ሊሰበሰብ የሚገባ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማስቀረት፤ ሐሰተኛ የታክስ ተመላሽ መጠየቅ፤ በሀሰተኛ ደረሰኝ ገቢ መሰብሰብ እና የመሳሰሉት የግብር ሥራዎችና ማጭበርበሮች ይከናወናሉ።

እነዚህ ተግባራት በየአመቱ የሚፈጸሙ የግብር ማጨበርበርያ ስልቶች ሲሆኑ በዚህም መንግሥት በርካታ ገቢዎችን እንዲያጣ ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። ይህ ደግሞ እንደሀገር የተቀየሱ እቅዶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዳይሆኑ በማድረግ አድገትን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው።

በልማት ግስጋሴ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ እድገት እና ብልጽግናዋን ለማሳካት በቂ የገንዘብ ምንጭ ያስፈልጋታል። ዋነኛው የገቢ ምንጭ ደግሞ የሀገር ውስጥ ገቢ ነው። ዘንድሮ እንደ ሀገር የተያዘው የገቢ ዕቅድ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ነው። ይህ እቅድ ሀገሪቱ በ2016 በጀት ዓመት ካስገባችው ጠቅላላ ገቢ ከሁለት እጥፍ በላይ ነው።

ስለዚህም የታየዘው እቅድ ግዙፍ ከመሆኑ አንጻር ከወትሮው በተለየ መልኩ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ዜጎች እንዲሠሩ በመበረታት የታክስ መሠረቱን ማስፋት እና በታክስ ማጭበርበር ላይ የሚታዩ ሕገወጥ አካሄዶችን እየተከታተሉ ማረም የግድ ይላል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You