“ኢትዮጵያውያን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን የመግዛት ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል”  – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን እጃቸው ላይ የቀረበውን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን የመግዛት ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ በቀጣይ በሆቴል ዘርፍ የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ እንደሚኖርም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮ ቴሌኮም ለኢትዮጵያውያን የ10 በመቶ አክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ትናንት ይፋ ሲያደርጉ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያውያን የኢትዮ ቴሌኮም ድርሻን በሽሚያ ሊገዙ ይገባል:: ይህን ዕድልም በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ትርፋማ በመሆኑ ስቶክ ማርኬትን ለማለማመድ 10 በመቶው ለሽያጭ ቀርቧል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስቶክ ማርኬት በይበልጥ ጥቅም ላይ መዋል ስላለበት ኢትዮጵያውያን ዕድሉን ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ገልፀዋል::

ከኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻ ለሽያጭ ቀርቦ በሚገኘው ትርፋማነት ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል ሲሉ አመላክተዋል። በዲጂታል ኢትዮጵያ ሥራዎች የታየው ውጤታማነት ለዚህ የአክሲዮን ሽያጭ አብቅቶናል በቀጣይም በሆቴል ዘርፉ የድርሻ ሽያጭ ይኖራል ሲሉ ጠቁመዋል::

በቀጣይም በሆቴል ዘርፍ ኢንቨስትመንቱን ለማስፋፋት የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ እንደሚኖር ጠቁመው፤ የካፒታል ማርኬት ልምምድና የአክሲዮን ድርሻ በመሸጥ ኢንቨስትመንትን በጋራ ማከናወን የሚቻልበትን ልምድ ማዳበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የምዕራፍ አንድ የአክሲዮን ሽያጩ ትናንት በቴሌ ብር አማካኝነት የተጀመረ ሲሆን፤ የአንድ አክሲዮን ብር 300 ሲሆን ዝቅተኛው የአክሲዮን መጠን 33 በመሆኑ ዝቅተኛው የአክሲዮን ግዥ 9ሺህ 900 ብር መሆኑ ይፋ ተደርጓል::

በአክሲዮን ሽያጩ እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸው 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን መደበኛ አክሲዮኖች ከዝቅተኛው 9 ሺህ 900 ብር ወይም 33 አክሲዮኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው 999 ሺህ 900 ብር ወይም 3 ሺህ 333 አክሲዮኖች መግዛት ይችላል፡

ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ሼር ካምፓኒነት መቀየሩን የተቋሙ ኃላፊ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል::

የ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጩ ከትናንትና ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል፡፡ ይሁንና አጠቃላይ የአክሲዮን ድርሻው መጠን ከተጠቀሰው ቀን በፊት ተሸጦ ከተጠናቀቀ እስከተገለጸው ቀን ድረስ ላይቆይ እንደሚችል ታውቋል፡፡

ጌትነት ተስፋማርያም

አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You