በክልሉ 14 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል ከለማው መሬት 14 ሚሊዮን ኩንታል የሩዝ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በክልሉ በሩዝ ሰብል የሚሸፈነው ማሳ እንዲሁም የሚሰበሰበው ምርት ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል።

የ2016/2017 ዓ.ም የምርት ዘመን በክልሉ 270 ሺህ 910 ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 150 ሺህ 225 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝ እየለማ ይገኛል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት በሩዝ ምርት ከተሸፈነው ማሳ 14 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያዋ አስታውቀዋል።

የማሳ ሽፋኑ ባደገ ቁጥር የምርት መጠኑ የሚጨምር በመሆኑ ክልሉ ምርት እንዲጨምር የማሳ ሽፋኑን ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።

በምርታማነትም በሄክታር 49 ኩንታል ይገኝ ነበር አሁን ላይ እያደገ መጥቶ በሄክታር 53 ነጥብ ሦስት የኩንታል ሩዝ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

እንደ ወይዘሮ እንዬ ገለጻ፤ የሩዝ ምርት ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ የመጣበት ምክንያት ክልሉ ሩዝ ማምረት የሚችሉ አካባቢዎችን ወደ ማምረት እንዲገቡ ትኩረት ሰጥቶ በመደገፉ ነው ።

ሩዝ ማምረት እየቻሉ ወደ ምርት ያልገቡ አካባቢዎችን ለይቶ ድጋፍ በማድረግ፣ ሥልጠናዎችን በመስጠት እና በተወሰነ መልኩ ክልሉ ዘር በማቅረብ እንዲሁም አምራቾች ዘር እየተገበያዩ እንዲጠቀሙ በማመቻቸት ጠንካራ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በአብዛኛው የሩዝ ማሳ በክላስተር እንደሚለማ የተናገሩት ባለሙያዋ፤ በአጠቃላይ በዘንድሮው የምርት ዘመን በሩዝ ምርት ከተሸፈነው ማሳ 115 ሺህ ሄክታሩ በክላስተር የሚለማ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሩዝ ልማት በበለጠ እንዲያድግ መሬቱ በዘመናዊ ትራክተር መታረስ እንዳለበት ጠቁመው ፤ የሩዝ መፈልፈያ ማሽን እጥረት ለሩዝ ልማት ተግዳሮት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ሩዝ አምርቶ ለማስፈልፈል አላስፈላጊ ወጪ እንደሚያወጣ ተናግረው፤ ችግሩን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በክልሉ በሩዝ ሰብል የተሸፈነው ማሳ 82 ሺህ 270 ሄክታር መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም አራት ሚሊዮን 486 ሺ ኩንታል ሩዝ ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።

መዓዛ ማሞ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You