አዲስ አበባ፡- የሀገርና የሕዝብ ኩራት የሆነውን የሰንደቅ ዓላማ ምንነት ለትውልድ በማስረዳት ታሪክን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አባት አርበኞች ገለጹ።
የጥናታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ያለው፣ የሀገርንና የሕዝቡን ማንነት የሚገልጽ ነው።
ጀግኖች አርበኞች በሀገር የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በመከላከል ከብሯን ለማስጠበቅ በጦርነት በሚወድቁበት ወቅት አንደኛውና ዋናው ምልክታቸው ሰንደቅ ዓላማ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለወጣቶች ዋጋ ስለተከፈለበት የሰንደ ቅዓላማ ምንነት፣ ማንነት፣ በዓሉ እንዴት መከበር እንዳለበት እንዲሁም ስለሀገራችን ባህል፣ ታሪክና ዕምነት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ማሳወቅ ከተቻለ የሰንደቅ ዓላማ ክብር ይበልጥ ይገለጣል ብለዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ማክበር ታላቅነትና ለሀገሪቱ ክብር የሚገባ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት የዓድዋ፣ የማይጨው እና ሌሎች ጦርነቶች ሲካሄዱ ሰንደቅ ዓላማ ተይዞ ነው። ድል ሲደረግም ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ይውለበለባል ሲሉ ተናግረዋል።
ሰንደቅ ዓላማ የሚከበርበት ዋናው ምክንያት አባትና እናቶቻችን ሰንደቅ ዓላማ ሀገራችንና ሕዝባችንን ይወክላል በሚል ዋጋ ስለከፈሉብት፣ ደማቸውን ስላፈሰሱበት፣ አጥንታቸውን ስለከሰከሱበት እና የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ስለከፈሉበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሰንደቅ ዓላማችን ደም የፈሰሰበትና የሕይወት መስዋዕትነት የተከፈለበት በመሆኑ ለትውልዱ በአግባቡ ማሳወቅ ይገባል ያሉት ልጅ ዳንኤል መስፍን፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ የሰንደቅ ዓላማ ክብርን፣ የሀገርን ባህልና ታሪክ፣ የወደፊት አቅጣጫዎችን እያስረዱ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
በትምህርት ቤትም ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ ነው ተብሎ የሚተው አለመሆኑን ማስረዳት ከተቻለ ኢትዮጵያን የሚመሩና ጋሻ የሚሆኑ፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፎች እውቀት ያላቸው እንዲሁም ሀገርና ሰላም ወዳድ ዜጎችን ማፍራት ይቻላል ነው ያሉት።
የማንንም ልጅ እንደራሳቸው ልጆች የሚያስተምሩ እና ለትምህርት ፍላጎት ያላቸው መምህራንንም በማፍራት ሀገራችንን ካደጉ ሀገራት ጋር ተርታ ማሰለፍ፣ ታሪኳን እና ባህሏን ለዓለም ሕዝብ ማሳወቅ ይገባል ብለዋል።
ሚዲያዎችም ሰላምን የሚሰብኩ፣ የሀገርን ታሪክና ባህል የሚያጎሉና እውነታዎችን በአግባቡ ለህብረተሰቡ የሚያደርሱ በመሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የሰንደቅ ዓላማ ክብር የሀገርና የሕዝብ ክብር በመሆኑ ሲሰቀልና ሲወርድ ከሕዝቡ አልፎ ንጉሠ ነገሥቱ በመንገድ ላይ ካሉ ይቆማሉ። አሁንም ይህ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የቀድሞው የሥራ አመራር ኮሚቴ አባል ሻምበል ዋኘው ዓባይ ወልደማርያም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የሚከበረው አባቶቻችን ለሰንደቅ ዓላማ ምን ያህል ታማኝ እንደሆኑ ለትውልዱ ለማስገንዘብ ነው።
ቀደም ባሉት ጊዜያት “ተመልከት ዓላማህን፣ ተከተል አለቃህን፣ አክብር ሰንደቅህን” እየተባለ እንደሚነገር አስታውሰው፤ ሰንደቅ ዓላማ የሀገር መለያ አርማ እና የሕገመንግሥቱ መጀመሪያ አንቀጽ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል ሰንደቅ ዓላማ ጠዋት 12 ስዓት ተሰቅሎ ማታ 12 ሠዓት ይወርድ ነበር። ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና ሲወርድ ማንም ከቆመበት አይነቃነቅም፣ መኪና አይነዳም፣ ከብቶች ይታገዳሉ ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜም ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ ሕዝብ መንቀሳቀስ የለበትም ተብሎ በአዋጅ መነገር አለበት። በዚህም የሰንደቅ ዓላማን ክብር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲያውቁት ይሆናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በቀለሞቿ ከዓለም የተለየች ናት። አረንጓዴው ልምላሜና ሀብት፣ ቢጫው ሰላምና ተስፋ፣ ቀዩ ደግሞ ጀግንነት እና መስዋዕትነትን የሚወክል መሆኑን አስታውቀዋል።
ሰንደቅ ዓላማን አባቶቻችን ጠብቀው አሁን ላለንበት ዘመን እንዳደረሱት ገልጸው፤ እኛም ሀገራችንን ለማስጠበቅ በዘመትንበት ቦታ ሁሉ የምናስቀድመው ሰንደቅ ዓላማን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አባቶቻችን ሹመት ሲሰጣቸው ሰንደቅ ዓላማህን ጠብቅ፤ ሕገመንግሥትህን አስከብር ተብለው ይሰጣቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ትውልዱ ሰንደቅ ዓላማን እንዲያከብሩ በትምህርት ቤቶች፣ በሚዲያዎች እና በሌሎች አማራጮች ስለሰንደቅ ዓላማ ክብር በስፋት መነገር እንዳለበት አብራርተዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀንን በዓመት አንድ ቀን ከማክበር ባለፈም በትምህርት ቤቶች፣ በመሥሪያ ቤቶች፣ በሚዲያዎች የሰንደቅ ዓላማ መዝሙሩን መዘመር እና ለሰንደቅ ዓላማው ከብር መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ላለፉት 16 ዓመታት በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ሰኞ የሚከበር ሲሆን ዘንድሮም 17 ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም