የዋልያዎቹን የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ የሚወስኑ ፍልሚያዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) በ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛ እና አራተኛ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬና በመጪው ማክሰኞ ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገው የሀገር ውስጥ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ከቀናት በፊት ወደ ኮትዲቯር አቅንተዋል፡፡

ዛሬ በገለልተኛ ሜዳ አቢጃን አላሳኔ ኦታራ ስቴዲየም ምሽት 1፡00 ሰዓት የሚጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ2025 በሞሮኮ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመቅረብ ያላቸውን ተስፋ የሚወስን ሲሆን፣ ዋልያዎቹ ከ2021ዱ የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ በኋላ ወደ ውድድሩ ለመመለስ ይፋለማሉ፡፡

ኢትዮጵያና ጊኒ እኤአ ከ1976 ጀምሮ ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ዋልያዎቹ ማሸነፍ የቻሉት አንዱን ብቻ ነው፡፡ ይህም እኤአ 2002 ላይ በሜዳቸው 1 ለምንም ያሸነፉበት ሲሆን ቀሪዎቹን ስድስት ጨዋታዎች ጊኒ ድል አድርጋለች፡፡ ከነዚህ ድሎች መካከል ጊኒ ሦስቱን በሜዳዋ ነበር ማሸነፍ የቻለችው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በቅርቡ ባለፈው መጋቢት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ጊኒ 3ለ2 እና 2ለ0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኳስና መረብ ማገናኘት ካልቻሉ አምስት ሀገራት አንዷ ነች። ባለፉት ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎቿ 19 ጊዜ ካደረገቻቸው የግብ ሙከራዎች አንዱ ብቻ ነው ለግብ የቀረበ የነበረው። ይህ የቡድኑን የግብ ሙከራ ንፃሬ 5 በመቶ ብቻ ሲሆን በማጣሪያው ከሚሳተፉ ሀገራት ሁሉ ዝቅተኛው ነው። ይህም የዋልያዎቹን የአጥቂ ችግር የጎላ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

ጊኒ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገቻቸው ጨዋታዎች የበላይነት ቢኖራትም ከሁለት ወር በፊት በጊዜያዊነት ከተሾሙት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ቻርልስ ፓኩዊል ጋር ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለችም፡፡ በተለይም ባለፉት አራት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች አንድም ማሸነፍ አልቻለችም። ሦስት ተሸንፍ አንዴ የአቻ ውጤት አስመዝግባለች። ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈችውም መጋቢት 2023 ላይ ኢትዮጵያን 3ለ2 ነበር። ዋልያዎቹ በተለይም ከአጥቂ ችግር ጋር በተያያዘ ከተጋጣሚያቸው ጊኒ በባሰ መልኩ የተዳከሙበት ወቅት ላይ መገኘታቸው እንጂ የጊኒን የበላይነት ለመቀልበስ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ያም ሆኖ የአሠልጣኝ ገብረመድኅን ስብስብ አሁንም በነዚህ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነገር ፈጥሮ ወደ ድል በመመለስ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎውን ተስፋ የማለምለም ዕድሉ ከእጁ አልወጣም፡፡

አሠልጣኝ ገብረመድኅን ከቀናት በፊት ሁለቱን ጨዋታዎች በተመለከተ የመጨረሻውን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍም ሆነ ላለማለፍም ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሁለት ቀን ልዩነት ነው ጨዋታውን የምናደርገው። የአንድ ቀን እረፍት ነው የሚኖረው።

በዚህ ሁለት ጨዋታ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመግባታችን ጉዳይ የሚወሰን ይሆናል። በድምር ውጤት የምናገኘው ተስፋ ሰጪ ነው አይደለም የሚለውን ነገር በዛው ጨዋታ ላይ ነው የምናየው። በዚህ በድምር የምናገኘው በተለይ ተጋጣሚያችንን ጥሎ ከማለፍ አንፃር ጥሩ ጠቀሜታ ስላለው የግድ የምንሄደው ለማሸነፍ ነው። ያለን ዕድል ማሸነፍ ነው። ሌላ ዕድል አይኖረንም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ የሚቀሩ ጨዋታዎች ሁለት ናቸው።

ስለዚህ በሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ እኛ የምናገኘው ታንዛኒያን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎን ነው። ስለዚህ ከባድ ሊሆን ይችላል ብለን እናስባለን። በእርግጥ በሜዳችን ብንጫወት ኖሮ ታንዛኒያን በሜዳችን እናገኛለን ብለን እናስብ ነበር፣ ነገር ግን አሁን አናገኝም ስለዚህ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

ስለዚህ አሁን ይሄንን ሁለት ጨዋታ በተመሳሳይ ሀገር ነው የምንጫወተው፣ ምናልባት ከተማው ሊቀያየር ይችላል ግን ዞሮ ዞሮ ለሁለታችንም አንድ ነው። እነሱ ከሜዳቸው ውጪ ነው እኛም ከሜዳችን ውጪ ነው የምንጫወተው እና በዚህ በድምር ውጤት የምናገኘው ውጤት ያው ሊያሳልፈንም ሊጥለንም ስለሚችል ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ያለንን አቅም አሟጥተን ተጫውተን አሸንፈን ተስፋችንን ለማብራት ጥረት እናደርጋለን። በማለት ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማጣሪያው ከሁለት ጨዋታ አንዱን በዲሞክራቲክ ኮንጎ 3ለ0 ተሸንፍ ከታንዛኒያ ጋር ደግሞ 0ለ0 ተለያይታ በአንድ ነጥብና ሦስት የግብ ዕዳ ከምድቧ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ጊኒ ከሁለቱ የማጣሪያ ጨዋታዎቿ በዲሞክራቲክ ኮንጎና ታንዛኒያ ተሸንፋ አንድም ነጥብ ሳትይዝ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች። ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሦስቱንም ጨዋታዎቿን በማሸነፍ ምድቧን በዘጠኝ ነጥብ ስትመራ ታንዛኒያ በአራት ነጥብ ትከተላለች።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You