የልጅን ለቅሶ ሽሽት

በወጣትነቱ በፍቅር የወደቀው ወጣት ዳዊት ሰለሞን ትዳር ለመመስረት ያለቅጥ ቸኩሏል። ገና በ17 ዓመቱ ከፍቅርተ ቶሎሳ ጋር በጥድፊያ ፍቅር ውስጥ ሲገባ፤ ስለወደፊት ሕይወቱ እምብዛም አልተጨነቀም። ሲያያት ውሎ አቅፏት ቢያድር አይጠግባትም። ፍቅርተ ምንም እንኳን የዳዊትን ያህል ባትሆንም፤ በፍቅር ውስጥ ገብታለች። ሆኖም የሁለቱም ቤተሰቦች ልጆቻቸው በፍቅር መውደቃቸውን አልወደዱትም።

ወጣቶቹ በፍቅር ከመውደቅ አልፈው፤ በትዳር ለመጣመር ሲወስኑ ስለቤተሰቦቻቸው አልተጨነቁም። የአካባቢው ሰው ገሚሱ ‹‹ አይን ይብላችሁ…›› እያለ ሲያንጓጥጣቸው፤ ገሚሱ ‹‹ጎሽ…›› እያለ እየካባቸው፤ ለተወሰኑ ወራት ፍቅራቸው አገር መንደሩን አስደነቀ። ብዙ አልቆዩም፤ ዳዊት 18 ዓመት ሲሞላው፤ ፍቅርተ ደግሞ ገና በ17 ዓመቷ ትዳር መሰረቱ።

ፍቅርተ እና ዳዊት ትዳር ውስጥ ሲገቡ፤ ምን ሰርተው በምን መልኩ ራሳቸውን እንደሚያስተዳድሩ አልወሰኑም፤ አለመወሰን ብቻ ሳይሆን ምን በልተው በምን አይነት መጠለያ ውስጥ እንደሚኖሩ አላሰቡበትም። ቤተሰብ ሳይፈቅድ እና ሳይደሰት፤ ሽማግሌ ተልኮ ልጃችሁን ለልጃችን ሳይባባል፤ በደፈናው ተያይዘው ተጋብተናል ብለው ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ አቀኑ።

ትዳር

ዳዊት እና ፍቅርተ ትዳር መሰረትን ብለው በጋራ ለመኖር ቢወስኑም፤ ገንዘብ ስለሌላቸው ብዙ መቆየት ተሳናቸው። ዳዊት በትምህርቱ ከ10ኛ ክፍል አልዘለቀም። እንኳን በቅጡ ትምህርቱን አጠናቆ ዲግሪውን ላልጫነ ወጣት ቀርቶ፤ ትምህርቱን በማዕረግ አጠናቅቆ ዲግሪ ለያዘውም መከራ የምታሳየዋ አዲስ አበባ ለዳዊትም ሆነ ለባለቤቱ ፈታኝ ሆነችባቸው።

ፍቅርተ ቤት ውስጥ ያለምንም ሥራ ያለ በቂ ገንዘብ ውላ ስታድር፤ መከፋት ጀመረች። ዳዊት የፋብሪካ ሰራተኛ የመሆን ዕድሉን ስላገኘ፤ ቀን ሲሰራ ውሎ ማታ ለመኝታ ይገባል። ፍቅርተን እንደቀደመው በፍቅር ሊያጫውታት አልቻለም። ጊዜ የለውም፤ ቤት ከገባ በአብዛኛው ከፍቅርተ ጋር ስለውሎዋ ሳያወራ፤ ሳያመሽ ቶሎ ይተኛል። በለሊት ተነስቶ ወደ ሥራ ይሔዳል።

ሰው በተለይም ዳዊት ከጎኗ ሆኖ እንዲያጫውታት የምትፈልገዋ ፍቅርተ ዳዊት ሲተኛ ትበሳጫለች። በእንዲህ መልኩ አንድ ዓመት አለፈ። ፍቅርተ ዳዊትን ብትወደውም ለመለየት አሰበች። ነገር ግን እርሱን ትታ የምትሔድበት አልነበረም። ከዳዊት ጋር ትዳር ስትመሰርት ከቤተሰቦቿ ጋር ተለያይታለች።

አንዳንድ ቀን ተከፍታ ስታለቅስ ትውላለች። ሲመሽ በተስፋ ዳዊትን ትጠብቃለች። ዳዊት ግን ቤት ሲደርስ እንደነገሩ የቀረበለትን እራት ቀምሶ፤ ቶሎ ይተኛል። ዳዊት ፍቅርተን አይቶ ማልቀሷን አያውቅም። እንደውም ሙሉ ትኩረቱን እየነፈጋት ሔደ። ግራ የገባት ፍቅርተ ቀስ በቀስ ከአከራይዋ ጋር መነጋገር ጀመረች። ከሌሎች ተከራይ ጎረቤቶችቿ ጋር ማውራት እና ሚስጥሯን ማካፈል ጀመረች። ሁሉም እንድትወልድ መከሯት። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ገና በ18 ዓመቷ ፀነሰች።

ዳዊት የፍቅርተ መፀነስ አላስደሰተውም። ልጅ ወልዶ ማሳደግ ቀርቶ፤ ፍቅርተ እና ራሱን በትክክል ለማኖር ተቸግሯል። ፍቅርተም ብትሆን ጎረቤቶቿ መክረዋት እንጂ ልጅ ወልዶ የማሳደግ ጉዳይ እጅግ ሊከብዳት እንደሚችል ገምታለች። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ ባልና ሚስቱ በተፀነሰው ልጅ ዙሪያ መግባባት ላይ ደረሱ። ዳዊት ፅንሱን አስወርጂ አላት። ፍቀርተ ዳዊት ያላትን በመስማት ውርጃ ይካሔድበታል ወደ ተባለ አንድ የጤና ተቋም አመራች።

በጤና ተቋሙ ውስጥ ያለው ባለሞያ ማስወረድ እንደማትችል እና ፅንሱ ሶስት ወር እንዳለፈው አረዳት። ለማስወረድ ከሞከረች ሕይወቷ ላይ ከባድ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል መከራት። ፍቅርተ ለዳዊት በጤና ባለሞያው የተነገራትን በሙሉ ነገረችው። ዳዊት ለማመን ተቸገረ። በፍፁም ልጅ መውለድ አልፈለገም። ፍቅርተ ዳዊትን እንደምንም ተማፅና እና ብዙ ለምናው ልጁ እንዲወለድ እንዲፈቅድ አስገደደችው። ብዙም ሳይደሰት እንደተከፋ ተስማማ። ፍቅርተ እንደወጉ እርጉዝ ሆና ታየች። እንዳይደርስ የለም የመውለጃ ጊዜዋ ደረሰ።

የፍራኦል ውልደት

ፍቅርተ ለመውለድ ቀኗ ሲገፋ እንደብዙዎቹ ነፍሰ ጡሮች የገንፎ ዕህል አላስፈጨችም። ቤቴን ላሳምር ብላ አልተጨነቀችም። ለነገሩ የገንፎ እህል ለማስፈጨትም ሆነ ቤት ለማሳመር ብትፈልግም አትችልም። ምክንያቱም የፍቅርተ እና የዳዊት ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው። አንዳንዴ ምንም እንኳ እንደማንኛውም ነፍሰጡር ሴት መብላት ብትፈልግም፤ በቤቱ የሚበላ ስለማይኖር ምግብ ሳትበላ የምትውልባቸው ቀኖችም ነበሩ።

ሆዷ እየገፋ ወሯ እየገባ ሲሔድ፤ ዳዊት መጨነቅ ጀመረ። አንዳንዴ እርሷን ላለማየት እንቅልፍ እስኪጥላት አምሽቶ መግባቱን ተያያዘው። አምሽቶ ይገባል፤ ሳታየው ማልዶ ይወጣል። ቤት መግባቱን የምታውቀው እኩለ ለሊት ላይ ከጎኗ ተኝቶ ስታገኘው ብቻ ነው። ቃላትን ሳይለዋወጡ ሳምንታት ተቆጠሩ። ምጧ ሲመጣ ጎረቤቶቿ ስልክ ደወሉለት። ዳዊት ስልክ አንስቶ ምላሽ አልሰጠም። አፋፍሰው ጤና ጣቢያ ወሰዷት። ዳዊት አጠገቧ ሳይደርስ ለጇን ተገላገለች።

ፍቅርተ ዳዊት እና ቤተሰቦቿ ሳይኖሩ፤ በባዕዳን ተከባ በሰላም በመገላገሏ ከዘመድ በላይ (ፍራኦል) ስትል ለልጇ ስም አወጣችለት። ዳዊት ፍቅርተ በሰላም መገላገሏን ከሰማ በኋላ አጠገቧ ተገኘ። በእርግጥም ልጅ መውለድ መቻሉን አየ። አቅፎ የሕፃኑን ግንባር ሳመ። ልጁን እና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ገባ።

ፍራኦል የፍቅርተን ጡት ቢመጠምጥም አይበቃውም። በቂም የሚበላም ሆነ የሚጠጣ ነገር ስለማታገኝ ጡቷ አያግትም። ፍራኦል ሲርበው አምርሮ ያለቅሳል፤ አንዳንዴ ከማልቀስ አልፎ አጥግቡኝ በሚል ድምፀት ይጮሃል። ዳዊት የፍራኦልን ለቅሶ መስማት አይችልም። ማታ ቤት ሲገባ ፍራኦል ካለቀሰ፤ ዳዊት ለፍቅርተ ‹‹ልጅሽን ዝም አሰኚው።›› ብሎ ይጮህባታል። ደንግጣ ብንን ትልና መልሳ ልጇን አቅፋ አብራ ታለቅሳለች።

ሽሽት

ዳዊት መጨነቅ የማይፈልግ ሰው ሆኖ፤ ገና በለጋነቱ እርሱ ሳይጠነክር ትዳር መስርቶ ልጅ መውለዱ ቁጭት ውስጥ ከተተው። ሰርቶ የሚያገኘው ገቢ አነስተኛ በመሆኑ፤ ለልጁ ወተት መከራየትም ሆነ በየቀኑ መግዛት ከበደው። ፍቅርተ የሚሰጣት ገንዘብ እንደማይበቃት ስትነግረው ቀድሞም አትውለጂ እያልኩሽ የወለድሽው አንቺ ነሽ ብሎ ደጋግሞ ከመውቀስ ባሻገር፤ ‹‹ እኔ መጨነቅ አልፈልግም። እንደውም ልጅሽን ይዘሽ የትም መሔድ ትችያለሽ።›› እያለ ፍቅርተን ማበሳጨት የየዕለት ተግባሩ አደረገው።

ፍቅርተ በበኩሏ ምንም እንኳ የዳዊት ፍቅር ቢለቃትም ለልጇ ስትል መታገስን መረጠች። ሆኖም ትዕግስቷ ብዙ አልዘለቀም። ልጇ ስድስት ወር ሆኖት ምግብ ሲጀምር፤ ሕፃኑን ፍራኦል ቤት ውስጥ ለዳዊት ጥላለት ለመሔድ ወሰነች። ከልጇ የርሃብ ለቅሶም ሆነ ከባሏ ከዳዊት ወቀሳ ለመሸሽ መጥፋት መፍትሔ እንደሆነ አሰበች። ከማሰብ አልፋ የባሏን የመውጫ ሰዓት ጠብቃ ልጇን አስተኝታ ቀድማ በመውጣት ከአካባቢው ርቃ ሔደች።

ዳዊት እንደለመደው አምሽቶ ቤት ሲገባ ፍቅርተ ቤት ውስጥ የለችም። ሽንት ቤት ሔዳ ይሆናል ብሎ ቢጠብቃትም አልተመለሰችም። በጥበቃ ለሊቱ ተጋመሰ። እናቱ አስተኝታው የሄደችው ሕፃን ፍራኦል ከእንቅልፉ ሲነቃ ፍቅርተ የለችም። እንደለመደው ማልቀስ ጀመረ። የተወለደ ቀን ብቻ ያቀፈው አባቱ ግራ ገብቶት አንስቶ አቀፈው። ፍራኦል ግን ማልቀሱን አላቆመም። ዳዊት ግራ ገባው፤ ለሊቱን ሙሉ ቆሞ አቅፎት አደረ። ጠዋት ሲነጋለት ሕፃኑን ይዞ ወደ አምቦ ጉዞ ጀመረ።

ዳዊት ፍራኦልን ይዞ ወደ አምቦ ለመሔድ የወሰነው ፍቅርተን አገኛታለሁ ብሎ አስቦ ነበር። ነገር ግን ፍቅርተ አምቦ አልተመለሰችም። ልጁን ይዞ ወደ ቤተሰቦቹ ሔደ። ለእናቱ ‹‹ፍቅርተን እስካገኛት ተንከባከቢልኝ›› ብሎ ለእናቱ ሰጠ። እናቱ ዳዊትን አስጠነቀቁ። በሳምንት ውስጥ ልጁን የማይወስድ ከሆነ ቤቱ ድረስ በመሔድ እንደሚመልሱለት ነገሩት። ዳዊት ልጁን ፍራኦልን ለእናቱ ሰጥቶ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።

ሥራ ቀርቶ በየመንገዱ ፍቅርተን ቢፈልጋትም ሊያገኛት አልቻለም። ለፖሊስ ጣቢያ አመለከተ። ነገር ግን አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደተባለው አውቃ የጠፋቸውን ፍቅርተ በቀላሉ ልትገኝ አልቻለችም። ዳዊት በአራተኛው ቀን ተመልሶ ወደ ሥራ ገባ። እናቱ ፍራኦልን ያሳድጉታል ብሎ ቢመኝም እንዳሰበው አልሆነም። የዳዊት እናት ከአምቦ ጊንጪ አካባቢ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ልክ በሳምንቱ ለዳዊት ልጁን ሰጥተው፤ ወደ አምቦ ተመለሱ።

ፍራኦል እናቱ ጥላው ከጠፋችበት ቀን ጀምሮ ከበፊቱ በባሰ መልኩ አልቃሻ ሆኗል። ዳዊት እናቱ ልጁን ፍራኦልን ጥለውበት ሲሔዱ፤ በኪሱ ምንም ዓይነት ገንዘብ አልነበረም። ወተት መግዛት አልቻለም። ዳዊት ልጁን የሚያበላው እና የሚያጠጣውን ነገር አጣ። መብላት እና መጠጣት የፈለገው ሕፃን ፍራኦል፤ ደጋግሞ ሲያለቅስ ዳዊት ከማባበል ይልቅ መበሳጨት ጀመረ። አልጋ ላይ ወረወረው ፍራኦል ሲያለቅስ ቆይቶ በድካም እንቅልፍ ወሰደው።

የሕፃኑ አባት ለሊቱን ሙሉ ሲያለቅስ የነበረው ፍራኦል እንቅልፍ ስለወደው ተደሰተ። እርሱም ከጎኑ ተኛ። ነገር ግን ከእንቅልፍ መንቃት አይቀርምና ፍራኦል ነቅቶ እንደተለመደው ማልቀሱን ቀጠለ። ቀድሞ የተበሳጨው ዳዊት የሚያደርገው ጠፋው። የጊቢው ሰዎች የሕፃኑን ለቅሶ ቢሰሙም፤ ዳዊትን እናግዝህ አላሉትም። ዳዊትም ጠይቆ መታገዝ አልፈለገም። ነገር ግን ከለቅሶ ድምፅ መሸሽ ፈለገ። እንደሚስቱ ጥሎ ለመጥፋት አላሰበም። ሌላ ሃሳብ መጣለት። ሕፃኑን ገድሎ እጁን ለፖሊስ ለመስጠት ወሰነ።

በጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ አምስት ሰዓት አካባቢ ዳዊት የልጁን የሕፃን ፍራኦልን አንገት አነቀ። የሕጻን ነፍሱ በሲቃ ተጨነቀች። እንደአቅሙ ነፍሱ እንዳትወጣ ተወራጨ። ሆኖም የገጠመው ክንድ ብርቱ ነበር እና ተሸነፈ፤ ትንፋሹም ላትመለስ አመለጠች። አሁን እንደቀደመው ነቅቶ በድጋሚ የሚያለቅስበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ አከተመ። የዳዊት ጭንቅላት አረፈ። አባት ዳዊት የሕፃኑን የለቅሶ ድምፅ ሽሽት መጨረሻው ሕፃኑን በመግደል ተጠናቀቀ።

ድርጊቱን የፈፀመው ዳዊት ቀድሞ እንዳሰበው እጁን ለመስጠት አልደፈረም። ይልቁኑ ተደብቆ ማንም ሳያውቅ የሕፃኑን አስክሬን በማዳበሪያ ጠቅልሎ ቆሻሻ ላይ ለመጣል ወሰነ። የሕፃኑ የለቅሶ ድምፅ ማቆምን ተከትሎ ጎረቤቶች መከታተል ጀመሩ። ዳዊት ቀስ ብሎ የሕፃኑን አስክሬን ከጊቢ ይዞ ሲወጣ፤ ጎረቤቶቹ ተመለከቱት። እየተከታተሉት የት ምን እንደሚያደርግ አጣሩ።

ዳዊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ማንጎ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ የቆሻሻ መጣያ ሥፍራ ላይ የሕፃኑን አስክሬን በማዳበሪያ ጥሎ ሸሸ። የተከተሉት ሰዎች የጣለውን ማዳበሪያ ሲያዩ የሕፃኑን አስክሬን አገኙ። በፍጥነት ለፖሊስ በማመልከታቸው ዳዊት ሰለሞን በዛው ቅፅበት በቁጥጥር ስር ዋለ።

የፖሊስ ምርመራ

የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ በፍጥነት ቦታው ላይ የደረሰው የፖሊስ ምርመራ ቡድን የሕፃን ፍራኦልን አስክሬን በጥንቃቄ በማንሳት ለቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ለፎረንሲክ የምርመራ ክፍል አስክሬኑን ላከ። ሳይውል እና ሳያድር በዕለቱ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አዋለው። የምርመራ ቡድኑ የወንጀሉን መነሻ፣ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሁኔታ የሚያመላክቱ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አደራጅቶ እና አዳብሮ ለአቃቤ ሕግ አቀረበ።

የክሱ ዝርዝር

አቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ ከፖሊስ የምርመራ ቡድን የቀረበለትን መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አዳብሮ ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል ሲል ክስ ለመመስረት የወንጀል ዝርዝሩን አቀረበ።

አቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ እንዳብራራው፤ የ21 ዓመት ዕድሜ ያለው ተከሳሽ ዳዊት ሰለሞን በጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ማንጎ ሰፈር በሚባል አካባቢ ከቀኑ 5 ሰዓት አካባቢ ‹‹ሕፃኑ ለቅሶውን አላቆም አለኝ›› በሚል ሰበብ የሕፃኑን አንገት አጥብቆ በመያዝ ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል። አልፎ ተርፎ የሕፃኑን አስክሬን በማዳበሪያ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ወስዶ በመጣሉ በተራ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል።

በተጠርጣሪው ዳዊት ሰለሞን ላይ የስምንት ምስክሮች ቃል የተደመጠ ሲሆን፤ ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከፎረንሲክ የምርመራ ክፍል የአስክሬኑን የምርመራ ውጤት በተመለከተም በቁጥር ጰሀ8/1529 በጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም የተሰጠ የሟች የሞት ምክንያትን የሚያስረዳ የሕክምና ማስረጃ ቀርቧል። የተከሳሽ የእምነት ክህደት ቃል እና የሟች የአሟሟት ሁኔታ እና የወንጀል ድርጊት አፈፃፀሙን የሚያሳይ 36 ፎቶ እና ተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃሉን ሲሰጥ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል የያዘ ሲዲም ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።

ውሳኔ

ተከሳሽ ዳዊት ሰለሞን በተከሰሰበት ተራ ሰው የመግደል ወንጀል ጉዳዩ በፍርድ ቤት ክርክር ሲታይ ቆይቶ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን ተሰጥቷል። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ፍርድ ቤቱ ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት በአስራ አንድ ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You