ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራች አገር ናት። ወራሪ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር በመዳፋቸው ስር ሊያስገቧት አስበው ብዙ ሞክረዋል። መሰል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ካደረጉት ወራሪዎች መካከል አውሮፓዊቷ ኢጣሊያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። የፍራንቼስኮ ክሪስፒዋ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የሽንፈት ካባ በድል ለማካካስ በማሰብ በፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሎኒ እየተመራች አሰቃቂ ወረራ በመፈፀም ለአምስት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ቅን ተገዢዋ ለማድረግ ጥረት አድርጋም ነበር።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎች እንዲሁም በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ በጠመንጃ አፈሙዝ መቅደድ ጀመረች።
እንዲህ እንዲህ እያለች በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች። መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ።
ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ያልተዘመረላቸው ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ናቸው።
ዑመር ሰመተር በ1871 ዓ.ም በኦጋዴን አካባቢ ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ። ለአካለ መጠን ከደረሱም በኋላ የኤልቡር ገዢ በመሆን አገልግለዋል። ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀል የያዘችውን የረጅም ጊዜ ዓላማ ለማሳካት ባደረገችው ወረራ ወቅት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት ጋር ተሰለፉ። ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የጫረችው የወልወል ጠብ (Wal-wal Incident) የተከሰተው ደግሞ ዑመር ሰመተር በነበሩበት በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ነበር።
ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት (Italian East Africa Colony) አካል ለማድረግ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅና ጊዜ ስትጠብቅ ቆየች። እ.አ.አ በ1922 ወደ ስልጣን የመጣው ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የውርደት ማቅ እንደሚበቀልና ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት አካል እንደምትሆን መዛት የጀመረው ገና በጠዋቱ ነበር።
ለዚህም እንዲያመቸው የኢጣሊያ መንግሥት ራስ ተፈሪ መኮንን ኢጣሊያን በጎበኙበት ወቅት ‹‹ቪቫ ኢትዮጵያ›› እያለ ወዳጅ መስሎ ሸነገላቸው። እስከ አፍንጫው የታጠቀ በርካታ ጦር በኤርትራና በሌሎች የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት አካባቢዎች ላይ ያከማች ጀመር። የጦሩን ውጤታማነት አስተማማኝ ለማድረግም ሀኪሞችን፣ ሰላዮችንና ሌሎች ሙያተኞችን አብሮ አጓጓዘ። ‹‹ኢትዮጵያውያን›› የግዛት ባላባቶችን በጥቅም በመደለል ማስኮብለሉንና መረጃ መመንተፉንም ተያያዘው። በጨካኝነታቸው የታወቁትን እነ ኢሚሊዮ ዴ ቦኖ፣ ፒየትሮ ባዶሊዮ፣ ሩዶልፎ ግራዚያኒና ሌሎች የጦር አለቆችን ወደ ምስራቅ አፍሪካ ላከ።
ጣሊያን ይህንን ዝግጅት ካጠናቀቀች በኋላም ኢትዮጵያን የምትወርበት አጋጣሚ መጠባበቅ ጀመረች። ረቡዕ ዕለት፣ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም የኢጣሊያ ወታደሮች በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ሱማሌላንድ (British Somaliland) መካከል ያለውን ወሰን ለመከለል የተላኩትን ሰዎች ይጠብቁ በነበሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ከፈቱባቸው። (ኢጣሊያ በአካባቢው ያለው የኢጣሊያ ሱማሌላንድ ግዛቷ ስለሆነ ወታደሮቿ በአካባቢው ነበሩ)
ውጊያ ተደረገና በሁለቱም ወገኖች በኩል ሰውነት ቆሰለ፤አካል ጎደለ … የሰው ሕይወት ጠፋ። ኢትዮጵያም ስሞታዋን ለኢጣሊያ መንግሥት ስታቀርብ፤ የኢጣሊያ መንግሥት ይባስ ብሎ የተበደለ መሆኑን በመግለፅ የሚከተሉትን ‹‹የመደራደሪያ ጥያቄዎች›› አቀረበ።
፩.የወቅቱ የሐረርጌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም ወልወል ድረስ ሄደው እዚያ የሚገኘውን የኢጣሊያ የጦር መሪ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ አንድ የኢትዮጵያ የጦር ጓድ ለኢጣሊያ ሰንደቅ ዓላማ ሰላምታ እንዲሰጥ፣ በኢትዮጵያ በኩል ለተደረገው የማጥቃት እርምጃ ኃላፊ የሆኑት ባለስልጣኖች ሁሉ ተይዘው የኢጣሊያን ሰንደቅ ዓላማ እጅ ነስተው እንዲሻሩና ተገቢውን ቅጣት በአስቸኳይ እንዲያገኙ፣
፪. የኢትዮጵያ መንግሥት ለቆሰሉት፣ አካላቸው ለጎደለውና ለሞቱት የኢጣሊያ ወታደሮች ካሣ የሚሆን 200ሺ ማርቴሬዛ (ጠገራ ብር) እንዲከፍል፤ እንዲሁም
፫. በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈፅመው ከባድ ጥፋት ያደረሱት ዑመር ሰመተር ተይዘው ለኢጣሊያ መንግሥት እንዲሰጡ … በማለት የለየለት የትዕቢት ጥያቄ አቀረበ።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የኢጣሊያን ሃሳብ ሳይቀበል ቀረ፤ ጉዳዩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ቢጥርም ሳይሳካ ቀረ። ከዚህ በኋላ ፋሺስት ኢጣሊያ ለ40 ዓመታት ያህል ስትዘጋጅበት የቆየችውን እቅድ እውን ለማድረግ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን መውረር ጀመረች። በዓለም አቀፍ ሕግጋት ፈፅሞ የተከለከሉ የጦር መሳሪያዎችን (የጦር አውሮፕላን፣ የመርዝ ጋዝ፣ …) ጭምር በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ በጣም ከባድ የሆነ የጦር ወንጀል ፈፀመች።
ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት እወስዳለሁ ብላ ወልወል ላይ የጫረችው እሳት በሁለቱም ወገኖች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር። በኋላም እርቀ ሰላም አወርዳለሁ ብላ ቃል ስትገባም ድርድር ስታቀርብ የግጦሽ መሬት ከኢትዮጵያ ግዛት ተቆርሶ እንዲሰጣት ስትጠይቅ ‹‹በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ በደል የፈፀመው ዑመር ሰመተር እጁ ተይዞ ተላልፎ ይሰጠኝ›› ብላ ጠይቃ ነበር። ዑመር ሰመተርም ይህን ሲሰሙ ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ›› ብለው በመመለስ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረር እንድትታቀብ ደጋግመው ያስጠነቅቁ ነበር።
በወልወል የተጫረው እሳት በሰሜንም ቀጠለ፤በመላው አገርም ተዳረሰ። ዑመር ሰመተር ከደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት ጋር በመሆን የፀረ-ፋሺስት ትግሉን ተያያዙት። በተለይም የሰለጠነው የዑመር ሰመተር ጦር ገርለጉቤ ከተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ ስለነበር እየተወረወረ ጠላትን መውጫ ቀዳዳ በማሳጣት ታላቅ ጀብዱ ፈፅሟል። ኤልቡር በተባለው ቦታ ላይ ዑመር ሰመተር በስድስት ባታሊዮን የጠላት ጦር ተከበቡ። የሰዎቻቸውን አቅምና የጦሩን ሁኔታ ተመልክተው ቦታ ለቀቁ፤አንዳንድ ሰዎችም መሳሪያ አስረከቡ። ከአምስት ወራት በኋላ ዑመር ሰመተር ጦራቸውን አጠናክረው ሱማሌውን፣ ዐማራውን፣ ትግሬውን፣ ኦሮሞውን እንዲሁም ከሌላው የአገሪቱ ግዛት የተውጣጣውን ኅብረተሰብ አስከትለው በ1930 ዓ.ም ገደማ አንድ ሌሊት በጠላት ጦር ላይ አደጋ ጣሉ። ከስድስቱም ባታሊዮን ጦር የሞተው ሞቶ ሌላውም ተማረከ። መሳሪያዎቹንም ማረኩና ተመልሰው ሺላቦ ላይ ሰፈሩ።
አሁንም የኢጣሊያ ጦር ሺላቦ ድረስ እየመጣ ቢያስቸግር እንደገና ገጥመው ድል አደረጉት። ብዙ የጠላት ጦር አባላትንም ገደሉ። ዑመር ሰመተር ከደጋው የኢትዮጵያ ክፍል በሚላክላቸው የሰው ኃይል፣ መሳሪያና ስንቅ እየተጠናከሩ እንደገና ቆራሄ ላይ ከጠላት ጦር ጋር ገጥመው አመድ አደረጉት። በመጨረሻም ከጠላት ምሽግ ውስጥ ገብተው የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅና የማይረሳ ገድል ፈፅመዋል።
ከዚህ በኋላ ወደ ደገሃቡር ተመልሰው ከበላይ አዛዦቻቸው ጋር ተገናኙ። በዚህም ወቅት የጦሩ የአንዱ ክፍል አዛዥ የነበሩት ደጃዝማች ገብረማርያም የዑመርን ጀግንነት ተመልክተው በኦጋዴን አውራጃ ካሉት የአካባቢው ተወላጆች ወታደር መልምለው እንዲቀጥሩ ፈቀዱላቸው። በዚህም ጊዜ የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰጣቸው። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር ጠላትን በማንበርከክ በገርለጉቤ፣ በቆራሄ፣ በሃነሌ … የሚያስደንቅ ጀብዱ ፈፀሙ። ደጃዝማች አፈወርቅ ከሞቱም በኋላ ወታደሩን እያረጋጉ ሲዋጉ ቆይተው በመጨረሻ እርሳቸውም በስድስት ጥይት ቆስለው ስለነበር ወደ ጂግጂጋ ተመለሱ። ፊታውራሪ ዑመር ሰመተር የደረሰባቸው ቁስል እጅግ ከባድ ስለነበር ለጦርነት መሰለፍ ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ። የጦር መሳሪያ የሚገኝበትን ዘዴ እየቀየሱ፣ ሕዝቡም ካለው የማረሻ በሬና ሌላም ቁሳቁስ እያዋጣ በመሸጥ ጥይትና ጠመንጃ እየገዛ ትልቅ ውጤት አስገኝቶ ነበር።
በኋላም ቁስላቸው እጅግ እየበረታባቸው ስለሄደ ወደ ሃርጌሳ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከሃርጌሳ ተነስተው ኬንያ ገቡ። ከኬንያ ወደ ለንደንም ተወስደው ነበር። ከዚያም የቀረውን የጦርነት ጊዜ በስደት ላይ ሆነው ካሳለፉ በኋላ ነፃነት ሲመለስ ወደ አገራቸው ገቡ። ስድስቱ ጥይት በአካላቸው ውስጥ እንዳለ ነበር ወደ አገራቸው የተመለሱት።
ነፃነት ከተመለሰ በኋላ አርበኛው ሁሉ እየፎከረና እያቅራራ ጀግንነቱን ሲያስመሰክር ፊታውራራ ዑመር ሰመተር በምድረ ኦጋዴን ከጦር የተረፉ ጀግኖች ናቸው ካሉበት በመብራት ያስፈለጓቸው። ቀጥሎም የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጣቸውና የኦጋዴንና ጂግጂጋ ገዢ ሆኑ። ይሁን እንጂ በአካላቸው ውስጥ ያሉት ጥይቶች እረፍት ነሱዋቸው፤ ቁስሉም እያመረቀዘ አስቸገራቸው። በሐረር ከተማ ሃኪሞች ባሉበት ቦታ ሁሉ እየተዘዋወሩ ቢታከሙም መዳን ግን አልቻሉም።
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ለአገራቸው ትልቅ ቁም ነገር ሰርተው መጋቢት 6 ቀን 1936 ዓ.ም፣ በተወለዱ በ65 ዓመታቸው አረፉ። ስርዓተ ቀብራቸውም ሐረር ከተማ ውስጥ በሚገኘው መስጊድ በሙሉ ወታደራዊ ስነ-ስርዓት ተፈፅሟል።
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ከመሞታቸው በፊት እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹ … የአገሬን ሕዝብ የፈጀው ጠላት በጀግኖች ክንድ ተረግጦ ሲወጣ በዓይኔ ተመልክቻለሁ። የመገዛት፣ የመዋረድና የመረገጥ እድል ምን እንደሆነ አይቻለሁ። እንደተራራ ንብ በየምሽጉ እየገቡ የሚነድፉ ኢትዮጵያውያን ዘር በመሆኔም ኮርቻለሁ። በታሪክ የሰማሁትን የዓድዋ ጀግኖች ጀብዱ ለማስመስከር ልጆቻቸው በኦጋዴን የጣሊያንን አንገት ሲቆርጡ አይቻለሁ። የዚህ ሕዝብ ልጅ በመሆኔ አሁንም እኮራለሁ። የማዝነው ግን መላው ሱማሌዎች ተባብረው የአንዲት ኢትዮጵያ ልጅ ሆነው በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ሲጠቃለሉ ሳላይ በመሞቴ ነው። በመቃብርም ውስጥ ምኞቴ ይህ ነው።››
ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የባሕል፣ የሐይማኖትና የቋንቋ ልዩነት ለአገር አንድነት መሰናክል መሆን እንደሌለባቸው ሲያስገነዝቡም ‹‹ … ቅኝ ገዢዎች በፈጠሩት ክፉ ሴራ አንዳንድ አገሮች እየተለያዩ ኖረዋል። የተለያዩትም በመጀመሪያ ከታሪክ ጋር ያልተያያዘ ድንበር በማበጀት፤ቀጥለውም በሐይማኖትና በጎሳ እየተመካኘ ነው። ባሕል፣ ሐይማኖትና ቋንቋ አንዱን ወገን ከሌላው ሊለዩ የሚችሉ ምክንያቶች አይደሉም። በሕንድ በመቶ የሚቆጠሩ ሐይማኖቶችና ቋንቋዎች አሉ ሲባል ሰምቻለሁ፤በሌሎቹም አገራት እንዲሁ። ይሁን እንጂ ሰዎች የተለያየ ቋንቋ በመናገራቸው ከመሰረታዊ ታሪክ ሊፈናቀሉ አይገባም። አሁንም ኢምፔሪያሊስቶች በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የሚሸርቡት ሴራ ለታሪክ የተጋለጠ ነው። ጠላትን ተባብረን ከአገራችን ያስወጣን ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዢዎች ቀብረውት የሄዱት ቦንብ ቀኑን ጠብቆ እየፈነዳ ወገን ከወገኑ ሊፋጅበት አይገባም። እኛ ሱማሌዎችም ከሌሎች ሱማሌዎች ጋር ተባብረን ከአንዲት ኢትዮጵያ ጋር ተቀላቅለን በሰላም መኖር አለብን።
ኦጋዴን በጦር ሜዳ፣ በሐረርም ጠቅላይ ግዛት በአስተዳዳሪነት ስላለሁ እንዳሁኑ የአልጋ ቁራኛ ሳልሆን ከሰሜን፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብ እንዲሁም ከመሐል ኢትዮጵያ የመጡ የአገሪቱን ተወላጆች ተመልክቻለሁ። ከነደጃዝማች ነሲቡ እና ከነደጃዝማች አፈወርቅ ጋር ሆኜ ተዋግቻለሁ። ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከኦጋዴን ሱማሌ ወይም ከሌላው ሱማሌ የሚለው አንዳችም ነገር ዐይቼ አላውቅም። ባሕል፣ ሐይማኖትና ቋንቋ ሌላ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ምኞቴ በምስራቅ ክፍላችን ያሉ የተበታተኑ ሱማሌዎች አንድ ሆነው ኢትዮጵያዊነታቸውን ሲያስከብሩ ይታየኛል።
በጠመንጃ ሰደፍ ያስወጣነው ጠላት መልኩን ለውጦ ከእናት አገር ሊለይ ታሪክ ሰራሽ ሳይሆን ሰው ሰራሽ ችግር እየፈጠረ ነው። ሕዝባችን ይህን ተረድቶ አንድነቱን ማጠናከር አለበት …›› ብለው ተናግረው ነበር።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 3/2011
አንተነህ ቸሬ