ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ወሳኝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ

ሞሮኮ በቀጣዩ ዓመት ለምታስተናግደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚያስችሉት የማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣይ ቀናት ይካሄዳሉ። በ12 ምድቦች ተከፍለው በመፎካከር ላይ ከሚገኙት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)ም ሦስተኛ የምድብ ደርሶ መልስ ጨዋታውን ያካሂዳል። በምድብ 8 ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው ቡድኑ ከነገ በስቲያ ከጊኒ አቻው ጋር ወሳኙን ጨዋታ ያደርጋል።

በምድቡ አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ትናንት ጨዋታዎቹ ወደሚከናወኑበት አቢጃን ማቅናቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመላክታል። በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ቡድኑ ከታንዛኒያ ጋር በነበረው የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ የሚታወስ ነው። ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር በነበረው ቀጣይ ጨዋታ ደግሞ የ2 ለምንም ሽንፈትን አስተናግዷል። የምድቡ ሦስተኛ ጨዋታም ከነገ በስቲያ የሚከናወን ሲሆን፤ በዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ታንዛኒያ አቻዎቹ ሽንፈትን ከተቀበለው ጊኒ ጋር ይገናኛል።

ለዚህ ጨዋታ ከቀናት በፊት ተሰባስቦ ዝግጅት ሲያከናውን የቆየው ቡድኑ ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ሁለቱን ቀንሶ የኮትዲቯር ጉዞውን አድርጓል። ይህ የደርሶ መልስ ጨዋታም ቡድኑ በማጣሪያው ተፎካካሪ ሆኖ የመቀጠሉን ሁኔታ የሚለይ ወሳኝ ጨዋታ በመሆኑ ትኩረት የሚያደርጉበት መሆኑንም አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመላክተዋል። ቡድኑ በተደረገለት ጥሪ መሰረት 20 የሚሆኑት ተጫዋቾች አስቀድመው የተሰባሰቡ ሲሆን፤ በውጪ ሀገራት ክለቦች የሚጫወቱ ሦስት ተጫዋቾችን ጨምሮ የተቀሩት ዘግየት ብለው ቡድኑን መቀላቀላቸውን አሰልጣኙ ጠቁመዋል። የደርሶ መልስ ጨዋታው የሚከናወነው ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ማለትም ጥቅምት 02 እና 04/2017 ዓ.ም መሆኑ ፉክክሩን ይበልጥ ከባድ እንደሚያደርገው እርግጥ ነው። ይሁንና በመርሃ ግብሩ ለሁለቱም ቡድኖች በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም።

ሁለቱ ጨዋታዎች ቡድኑ በማጣሪያው የመቆየቱን ጉዳይ የሚወስኑ ሲሆን፤ በድምር የሚገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ መሆን አለመሆኑን ጨዋታዎቹ የሚታዩ ይሆናሉ። በተለይ ተጋጣሚውን የጊኒ ብሄራዊ ቡድን ጥሎ ማለፍ የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ቡድኑ ወደ ስፍራው የተጓዘው ለማሸነፍ መሆኑንና ያለው ብቸኛ ዕድልም ማሸነፍ ብቻ መሆኑንም አሰልጣኙ አስረግጠዋል። ምክንያቱ ደግሞ በቀጣይ በሚኖረው መርሃ ግብር መሰረት ቡድኑ የሚገጥማቸው ታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎን በመሆኑ ከባድ ሊሆን ይችላል።

‹‹ቡድኑ በራሱ ሜዳ የሚጫወት ቢሆን ኖሮ ታንዛኒያን እናስተናግድ ነበር፤ ነገር ግን ስለማንችል አስቸጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ከጊኒ ጋር የሚኖሩትን ሁለቱን ጨዋታዎች ለሁለቱም ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ መሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም የሚገኘው ድምር ውጤት ለቀጣዮቹ ጨዋታዎች ወሳኝ በመሆኑ አቅማችንን አሟጠን ለመጫወት ጥረት እናደርጋለን›› ብለዋል። ዋሊያዎቹ በማጣሪያው አስቀድመው ባደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ የነበራቸውን አቋም ጨምሮ በተለይ በአጥቂ በኩል ችግር እንዳለበት አሰልጣኙ በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ነጥብ ማስመዝገብ ቀጣይ እጣቸውን ለሚወስነው ለዚህ ወሳኝ ጨዋታ አሰልጣኙ ያላቸውን እቅድ በተመለከተም ያላቸውን አቅም ሁሉ አውጥተው ለመጠቀም እንደሚጥሩ ነው ያነሱት። ከዚህ ቀደም በአጥቂ ቦታ እንዲጫወቱ የተደረጉ ተጫዋቾች ውጤታማ ባለመሆናቸው እንደ አቤል ያለው እና መሃመድኑር ናስር ባሉ ተጫዋቾች ተተክተዋል። በመሆኑም ፊት መስመር ላይ የነበረውን ክፍተት በተሻለ ሁኔታ ይሸፍናሉ በሚል ይጠበቃል።

እንደአጠቃላይ ቡድናቸው ባለፉት ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩትን እንዲሁም ሌሎች ከዚህ ቀደም ያልተጠሩ አዳዲስ ተጫዋቾችን መጨመር የተገባ በመሆኑ የተለየ ነገር ይታያል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አሰልጣኝ ገብረመድህን ጠቁመዋል። በታንዛኒያው ግጥሚያ ተጫዋቾች ከእረፍት ተመልሰው ወደ ውድድር መግባታቸው በተወሰነ መልኩ ጨዋታው ላይ እንዳያተኩሩ አድርጎ ነበር። በአካል ብቃት ረገድም የተሟላ አልነበሩም። አሁን ግን እነዚህ ችግሮች ስለተቀረፉ በታክቲክና በጨዋታው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ለመሥራት ተችሏል። ስለዚህም ካለፈው ጨዋታ የተሻለ ነገር ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You