ዜና ሐተታ
ሳምንቱን ሙሉ የደራ የእህል ግብይት የሚካሄድበት ሥፍራ ነው እህል በረንዳ፡፡ ይህ የገበያ ስፍራ የተለያዩ እህል ጭነው በሚገቡና አራግፈው በሚወጡ ብዛት ያላቸው የጭነት መኪኖች ትርምስ ይስተዋልበታል፡፡ከየአቅጣጫው ተጭነው የሚገቡ የእህል ዓይነቶች እህል በረንዳ ይራገፋሉ፡፡
ሰሞኑን በከተማችን ሲናፈስ የነበረውን የእህል ዋጋ ውድነት መነሻ «የአቅርቦት እጥረት ነው» የሚል የሚናፈሰውን ወሬ እውነትነት ለማረጋገጥ ወደ እህል በረዳ አቅንቻለሁ፡፡በእህል በረንዳ የአንድ ጤፍ ዝቅተኛ ዋጋ በኪሎ 118 ብር ፣ አንደኛ ደረጃ ነጭ ጤፍ ደግሞ በኪሎ 146 ብር እና ከዚያ በላይ ሲሸጥ ተመልክቻለሁ።
እህል በረንዳ በጤፍ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው አቶ ሸምሱ መሀመድ (ስማቸው የተቀየረ) እንደሚሉት፤ በእህል በረንዳ ቀይ ጤፍ በኩንታል ከ11 ሺህ 800 ብር እስከ 12 ሺህ 200 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። ማኛ ጤፍ ደግሞ 14 ሺህ 600 እና ከዚያ በላይ እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።
እህል በረንዳ ገበያ የሚሸምቱት አብዛኞቹ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የእህል ነጋዴዎች ሲሆኑ፤ ወደ ህብረተሰቡ እየወረደ ሲመጣ ዋጋው ሊጨምር ይችላል ያሉት አቶ ሸምሱ፤ እስከ ህዳር ወር ድረስ ወይም ከታኅሣሥ ወር በኋላ አዲስ የእህል ምርት ወደ ገበያ እስኪገባ ድረስ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ማኛ ጤፍ በሐምሌ ወር ይሸጥ ከነበረው አንፃር አሁን ላይ እስከ አንድ ሺህ ብር ገደማ ጭማሪ መኖሩን የገለጹት አቶ ሸምሱ፤ ጭማሪው በአርሶ አደሩ እጅ ላይ ያለው የምርት መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህም ባለፈ በየአካባቢው የሚከሰቱ ድንገተኛ የጸጥታ ችግሮች ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
የስንዴ ነጋዴ የሆኑት አቶ ሺበሺ ግርማ (ስማቸው የተለወጠ) በበኩላቸው፤ የአንድ ኪሎ ስንዴ ዋጋ በጅምላ ከ65 እስከ 67 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው። የችርቻሮ ዋጋው ደግሞ ከ70 እስከ 75 ብር ድረስ እየተገበያዩ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም ከሐምሌ ወር አንፃር በትንሹ በአንድ ኪሎ የሶስት ብር ጭማሪ እንዳለ ገልጸዋል።
አሁን ላይ በገበያው ላይ የምርት አቅርቦት አለ። ነገር ግን መጠኑ ከነሐሴ ወር ጀምሮ እየቀነሰ ነው ያሉት አቶ ሺበሺ ግርማ፤ ይህም እስከ ህዳር ወር ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የዚህም መንስዔው አምና የተመረተው ምርት መጠን እየቀነሰ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ሌላው በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር መኖር የመንገድ መዘጋጋት ፈጥሯል። ይህም በገበያው ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው። ተጽዕኖው በተለይ ከአማራ ክልል የሚመጣው ምርት ላይ ይታያል ያሉት አቶ ሺበሺ ግርማ፤ የምርት አቅርቦት መጠኑ ከ2015 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ህዳር ወር ከነበረው አንፃር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ላይም በሸመታ ላይ የነበሩ ወይዘሮ አለሚቱ ታደሰ (ስማቸው የተለወጠ) እንደተናገሩት፤ በየዕለቱ እየጨመረ የመጣው የጤፍና የጥራጥሬዎች ዋጋ አሳሳቢ እንደሆነና መንግሥትም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል። ለዚህም በየአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር መፍታት ዋነኛው የመፍትሔ አካል መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም አንድ ኪሎ ምስር ከ170 እስከ 220 ብር ድረስ እየገዙ እንደሆነ ጠቁመው፤ በሌሎች የጥራጥሬ የእህል ዓይነቶች ላይም የዋጋ ጭማሪው ከፍተኛ እንደሆነና ያሉበት ሁኔታም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ከአራቱም ማዕዘን እህል በሰላም ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ቢሆን ዋጋው ሊቀንስ እንደሚችል ተናግረዋል።
እናም በእህል በረንዳ ባደረግነው የገበያ ቅኝት ገብስ አንድ ኪሎ 115 ብር፣ በቆሎ 47 ብር፣ ለሽሮ የሚያገለግል ሽምብራ 125 ብር፣ ተቆልቶ ወይም ተቀቅሎ የሚበላው ሽምብራ ደግሞ 90 ብር እንዲሁም ቀይ ዘንጋዳ 60 ብር በኪሎ እየተሸጠ መሆኑን ተመልክተናል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም