ሀገር ወዳዱ ወታደር

ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ከጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸውን ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መሥዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ በተለያዩ የሙያ መስኮች ማለትም በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ከልጅነታቸው ጀምሮ ወደሚፈልጉት የውትድርና የሙያ መስክ ተሰማርተው ጠንካራ ወታደር ሆነው የሚወዷትን ሀገራቸውን በሙሉ ጀግንነትና ፍቅር በማገልገል የሚታወቁት ጄነራል ከበደ ጋሼ አንዱ ናቸው።

ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ጋሼ ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተ ኪዳን እና ከአባታቸው ከ፲ አለቃ ጋሼ ተክለ ጊዮርጊስ በነሐሴ ወር 1923 ዓ.ም. በቀድሞው አጠራር በአርሲ ጠቅላይ ግዛት ልዩ ስሙ ቦረራ በሚባል ሥፍራ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአቅራቢያቸው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንዳሉ ፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም. አገራችንን በግፍ በመውረሯ የተነሳ አባታቸው በስመ ጥሩው አርበኛ በፊታውራሪ ኃይሌ አባ መርሳ አዝማችነት ሥር ጠመንጃ ያዥ ሆነው ወደ ጦር ሜዳ ሲዘምቱ፤ ጄኔራል ከበደ ከወላጅ እናታቸው ጋር ወደ አጎራባች አገር ኬንያ አስቸጋሪ ጉዞ በማድረግ ተሰደዱ፡፡

እዚያም በስደት ዓለም ሆነው ትምህርታቸውን በመቀጠል፤ የአማርኛንና የእንግሊዘኛ ቋንቋን በመማር የመለስተኛ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ጠላት ድል ተመትቶ ከወጣ አምስት ዓመት በኋላ፤ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በቤተሰባቸው እንክብካቤ ቆይተዋል፡፡ በ1937 ዓ.ም. በብሪቲሽ የወታደራዊ ቡድን በሚታገዘው በምድር ጦር መገናኛ መምሪያ (በሲግናል) ውስጥ በልጅ ወታደርነት ደንብ ተቀጥረው ዕድሜያቸው የሚጠይቀውን ወታደራዊ የእግረኛ ሥልት ትምህርትን ከሬድዮ ኦፕሬተርነት ሥልጠና ጋር በማጣመር ከወሰዱ በኋላ በአጥጋቢ ውጤት ተመርቀዋል፡፡

ጄኔራል ከበደ ወታደራዊ ግልጋሎታቸውን በምድር ጦር መገናኛ መምሪያ በመቀጠል በ1945 ዓ.ም. ኤርትራ ከእናት ሃገሯ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል በተወሰነበት ወቅት፤ በኮሎኔል አበበ ገመዳ የሚታዘዘው 12ኛ ብርጌድ አሥመራ እንዲገባና የጠቅላይ ግዛቱን ሰላምና ፀጥታ እንዲያስከብር በታዘዘበት ወቅት ለብርጌዱ የሚያስፈልጉትን የጦር ሜዳ ሬዲዩ መገናኛ አውታሮችን ከዘረጉት ቀደምት የሠራዊቱ አባላት መካከል አንዱና ዋናው ነበሩ።

ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ጋሼ በሠራዊቱ ውስጥ ባሳዩት ፈጣን እንቅስቃሴና ብቃት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጦር ትምህርት ቤት በኋላ የገነት ጦር ትምሕርት ቤት በተባለው የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ተቋም በ1947 ዓ.ም. የተሰጠውን የመግቢያ ፈተና በጥሩ ውጤት በማለፋቸው በጦር ትምህርት ቤቱ የ16ኛ ጊዜ ተወዳዳሪ እጩ መኮንን በመሆን ለስምንት ወራት የተሰጠውን የአዛዥነት ትምህርት ብልጫ አሳይተው 1ኛ ሆነው አጠናቅቀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በም/መ/እልቅና ማዕረግ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እጅ ባለ ዘውድ ብቸኛ የመኮንንነት ቀበቶ ለመሸለም በቅተዋል፡፡

ጄኔራል ከበደ መኮንን ከሆኑበት ከ1948 ዓ.ም. ጀምሮ ወታደራዊ አገልግሎታቸው እስከተቋረጠበት እስከ 1980 ዓ.ም በምድር ጦር ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሆለታ ገነት በሬዲዮ ጥገና አስተማሪነት፤ በምድር ጦር ተግባረ ዕድ መገናኛ በትምህርት ቤት አዛዥነት፣ በምድር ጦር አዛዥነትና መምሪያ ኮሌጅ በተማሪነት በመቀጠልም በመምህርነት አገልግለዋል።

በሀገር ወዳድነታቸው ስነምግባራቸው የሚታወቁት ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ በወታደራዊ መንግሥቱ ከፍተኛ አመራሮች በተያዘባቸው ቂም ከኃላፊነት ከመነሳት በተጨማሪ የነበራቸው ማዕረግ እንዲገፈፍ ተደርጎ ከፍተኛ በደል ደርሶባቸዋል። ነገር ግን በ1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሔደው የሥርዓት ለውጥ ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ለጄኔራል ከበደ ጋሼ በቀድሞ መንግስት የተገፈፈውን ማዕረጋቸውን በመመለስ የጡረታ መብታቸው 1983 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲከበር አድርጎል።

በበላይ አለቆቻቸው ጥቃትና በደል የደረሰባቸው ጄኔራል ከበደ በውትድርና አገልግሎት ዘመናቸው ለፈጸሙት አኩሪ ገድልና ላበረክቱት ክፍተኛ አስተዋጽዖ፣ ያልደበዘዘው የመሥዋዕትነት አሻራ እይካድምና ከኢትዮጵያና ከደቡብ ኮሪያ መንግስታት የሚከተሉትን ኒሻኖችና ሜዳሊያዎች ተሸልመዋል፡፡

ከኢትዯጵያ መንግስት ትየአርበኘነት ሜዳሊያ ባለ አንድ ዘንባባ እና የስደተኝነት ሜዳሊያ ባለ አራት ዘንባባ እንዲሁም የድል ኮከብ ሚዳሊያ አግኝተዋል፡፡ የ15 ዓመት አገልግሎት የብር ሜዳልያ ከኢትዮጵያ መንግስት የተቀበሉ ሲሆን፤ የ20 ዓመት የረጅም ዘመን አገልግሎት የወርቅ ሜዳልያ አግኝተዋል፡፡ ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ደግሞ የሰላም አምባሳደር የወርቅ ሜዳሊያ (በአንገት የሚጠለቅ) በተጨማሪ የዘማች ዓርማ ከኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ተሸልመዋል፡፡

በሕይወት ዘመናቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፉት ጄኔራል ከበደ ከጦር ግንባር እስከ ዓለም አቀፍ መድረክ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው አንድነት፥ ሉዓላዊነትና ክብር ሲሉ ከልጅነት አንስቶ እስከ አዛውንት ዕድሜያቸው ድረስ የከፈሉት መሥዋዕትነት ተዘንግቶ በ1980 ዓ.ም. የተፈጸመባቸው በደል ለከፍተኛ ብስጭትና ሕመም እንደዳረጋቸው ይናገራሉ፡፡

በ1969 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሕብሪተኛው የሶማሊያ መንግሥት እጅግ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀ ሠራዊቱን በማዝመት፣ በየሥፍራው ተበታትኖ ይገኝ የነበረውን የወገን ጦርና የፖሊስ ጣቢያዎችን እየደመሰሰ፤ ግዛታችንን በምሥራቅ 700 ኪ.ሜ፣ በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ በመግባት ወረራ ከፈፀመ በኋላ፤ ወረራውን ለመቀልበስ በአጭር ወታደራዊ ዝግጅት የወገን ፈጣን መልሶ ማጥቃት ዘመቻ እንዲጀመር ጥብቅ ትዕዛዝ ከመንግሥት ከደረሳቸው የወገን የጦር ክፍሎች መካከል አንዱ በደቡብ ጦር ግንባር የተሰለፈው ጀግናው 4ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ነበር።

በምሥራቅና በደቡብ ጦር ግንባሮች በወራሪው ሠራዊት ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ተጀምሮ ጠላት ከያዛቸው በርካታ ቦታዎች እየተቀጠቀጠ የለቀቀ ቢሆንም፤ በተሰጠው ወሳኝ ግዳጅ ከጀግናው 12ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ጋር በመተጋገዝ በደቡብ ግንባር የነበረውን የሶማሊያን ዕብሪተኛ ጦር እያሳደደ መትቶ በመደምሰስ ከአገራችን ግዛት ጠራርጎ በማስወጣት መጋቢት 3 ቀን 1970 ዓ.ም በአገራችን የጠረፍ ከተማ ዶሎ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የመጀመሪያውን ድል ያበሰረው፤ በወቅቱ ኮሎኔል በነበሩት በከበደ ጋሼ ዋና አዛዥነት የተመራው ጀግናው 4ኛ እግረኛ ክፍለ ጦር ነበር።

ኮሎኔል ከበደ ጋሼ፣ በሠራዊቱ ውስጥ በሰጡት የረዥም ጊዜ አገልግሎትና በደበብ ግንባር በፈጸሙት አገርናና ወገንን ያኮራ ገድል ሚያዚያ 15 ቀን 1977 ዓ.ም. በጊዚያዊ ወታደራዊ መንግሥት በብርጋዲየር ጄኔራልነት ማዕረግ የገነት ጦር ትምህርት ቤት ዋና አዛዥ በመሆን ተሹመዋል።

በመቀጠልም በ1980 ዓ.ም. ከገነት ጦር ትምህርት ቤት ወደ ሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ኤርትራ ግንባር የመክት ዕዝ ዋና አዛዥ ሆነው ተዛውረው ከሄዱ በኋላ ከግንባሩ አዛዦች ጋር የነበራቸው የቆየ አለመግባባት ዳግም አገርሽቶ ያለአንዳች ማጣራት በተቀናጀ የቡድን ጥቃትና ርብርብ “ጄኔራል ከበደ ለፓርቲና ለመንግሥት አመራር እንቅፋት ነው፡፡ ›› በሚል ተጨማሪ ሐረግ ተከሰው ከአንድ ዓመት የኤርትራ ቆይታቸው በኋላ፤ በአገሪቱ ፕሬዜዳንት የፖለቲካ ውሳኔ ማዕረጋቸውንና የጡረታ መብታቸውን እንዲያጡ ተደረገ፡፡

ጄኔራል ከበደ ጋሼ ይህንን ሁኔታ በተመለከተ የተሰማቸውን ከፍተኛ የሐዘን ስሜት በ2011 ዓ.ም. ‹‹የመስዋዕትነት አሻራ – ከልጅ ወታደርነት እስከ ጄኔራልነት፣ የአርባ ዓመታት የውትድርና ሕይወቴ ሕያው ምስክርነት፡›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ ‹‹… የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ማዕረግ የሰጡኝ በሕግና በሥርዓት ነው፡፡ ማዕረጌም የሚገፈፈው፤ ሕግ ፊት ቀርቤ፣ ራሴን ለመከላከል ያሉኝን ማስረጃዎች ሁሉ ጦር ፍርድ ቤት አቅርቤ፣ ምስክሮች ለእኔም-በእኔም ላይ ከመሰከሩና ግራ ቀኙ ታይቶ ጥፋተኛ ሆኜ ከተገኘሁ በኋላ እንጂ፣ በአንድ ግለሰብ የፖለቲካ ውሣኔ እንዲህ ዓይነት ከባድ ቅጣት ሊጣልብኝ አይገባም ነበር፡፡ የእኔ ጉዳይ ከፖለቲካ ጋር የሚያገናኘው ምንም ምክንያት አልነበረውም፡፡ ወታደራዊ ነው፡፡ በእኔ እምነት ለወታደራዊ ችግሮች መፍትሄው ወታደራዊ እንጂ፣ ፖለቲካዊ አይደለም፡፡›› ብለዋል።

በጦር ኃይሎች ኅብረት መገናኛ ትምህርት ቤት በአዛዥነት (Joint Communication)፣ በጦር ኃይሎች ኅብረት መገናኛ መምሪያ በመምሪያ መኮንነት፣ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወታደራዊ ዕዝ በደቡብ ኮሪያ ቀዳሚ መምሪያ የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት አገናኝ ጽህፈት ቤት በቡድን መሪነት፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በኅብረት መገናኛ በመምሪያ መኮንነት፣ በደቡብ ግንባር በብርጌድና በክፍለ ጦር ዋና አዛዥነት፣ በሶቪየት ኅብረት ወታደራዊ ትምህርት ቤቶች ጉብኝት በልዑካን ቡድን በአባልነት፣ በሕንድ ሪፑብሊክ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ጉብኝት በልዑካን ቡድን በአባልነት፣ በጦር ኃይሎች ከፍተኛ መኮንኖች አካዳሚ የጥናትና ምርምር መምሪያ በአስተባባሪነት፣ በገነት ጦር ትምህርት ቤት በዋና አዛዥነት እና በመጨረሻም፤ በሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ኤርትራ ግንባር የመክት ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን አገልግለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአገልግሎት ዘመናቸው በትምህርት ረገድ፤ የአንደኛ መለስተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኬንያ በስደት ዘመን የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ክፍል አዲስ አበባ በማታ ትምህርት ቤት፣ የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት በአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት፤ የዕጩ መኮንንነት ትምህርት በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በትምህርት ሚኒስቴር፣ በአ.አ ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ የምሕንድስና ትምህርት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ኢ.አ በጦር ኃይሎች ቋንቋ ትምህርት ቤት፣ የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮርስ በሆለታ ገነት የጦር ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

በተጨማሪም ካንሳስ አሜሪካ በሚገኘው ፎርት ሊቨን ዎርዝ ወታደራዊ ኮሌጅ ከፍተኛ የአዛዥነትና በመምሪያ መኮንንነት ኮርስ፣ በተመሳሳይ ኒው ጀርሲ አሜሪካ በሚገኘው ፎርት ማን ማዝ ወታደራዊ የቴክኒክ ኮሌጅ በመገናኛ መኮንንነት፣ ጆርጂያ አሜሪካ በሚገኘው ፎርት ጎርደን ወታደራዊ የቴክኒክ ኮሌጅ የመስክ ራዲዮ ጥገና ትምህርቶችን በመከታተል፣ አገራቸው ለአርባ ዓመታት ያህል ከልጅ ወታደርነት እስከ ጄኔራል ማዕረግ ድረስ በእግረኛ ጦር አዛዥነት፣ በአሠልጣኝነት፣ በኮሪያ ሪፑብሊክ የኢትዮጵያ ዘማች ሠራዊት አገናኝ ቡድን መሪነት ያገለገሉ! ክፍለ ዘመኑ ካፈራቸው የአገራችን ከፍተኛ ወታደራዊ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ጄኔራል ከበደ ከወይዘሮ ታሪክነሽ አበበ ጋር ሚያዚያ 24 ቀን 1946 ዓ.ም ጋብቻ መሥርተው እስከ ሕልፈተ- ሕይወታቸው ድረስ ላለፉት 71 ዓመታት በትዳር ዓለም ቆይተዋል፡፡ በ1998 ዓ.ም. በሞት የተለየ ልጃቸውን ወጣት ኤርሚያስ ከበደን ጨምሮ ሁለት ወንድና አራት ሴት በድምሩ ስድስት ልጆችንና አሥር የልጅ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምድር ጦር ሠራዊት የትምህርትና የሥልጠና ረዥም ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው፣ ለእጩ መኮንኖች፣ ለመሥመራዊና ከፍተኛ መኮንኖች ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር በመሆን የሥልጠና ማኑዋሎችን ያዘጋጁትና ዘመናዊ ወታደራዊ ሥርዓተ ትምሕርትን የቀየሱት፤ የደቡብ ግንባር ጀግና፥ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ያኮሩት አንጋፋው የጦር ሰው፤ ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ጋሼ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ94 ዓመታቸው መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

እኛም በዚህ ለሕዝብና ሀገራቸው መልካም ያደረጉና በተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ሁሉ የማይነጥፍ አሻራ ማኖር የቻሉ ግለሰቦች ታሪክ አንስተን ለአበርክቷቸው ክብር በምንሰጥበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ የተዋደቁትን የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባል ብርጋዲየር ጄኔራል ከበደ ጋሼን ውድ ሕይወታቸውን አስይዘው በሙያቸው ለሀገር ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመሰገንን። ሰላም!

ክብረአብ በላቸው

 አዲስ ዘመን መስከረም 30/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You