አዲስ አበባ፡- የኅብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል እቅድ ነድፎ በአዲስ መልክ ለመሥራት መዘጋጀቱን መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ገለጸ።
በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ጊደይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ድርጅቱ በሀገር ደረጃ ከሚጠቀሱ ታላላቅ የልማት ድርጅቶች መካከል ተጠቃሽ ነበር። ይሁን እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት ውድመት አገግሞ በአዲስ መልክ ተጨማሪ ዕቅዶች አውጥቶ ለመሥራት ዝግጅት አድርጓል።
ድርጅቱ በተሟላ መልኩ ምርት እንዲጀምር ጥረቶች እየተደረጉ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ቀደም ሲል በሲሚንቶ ፋብሪካዎች እና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ጀርባ በመሆን የኢንጂነሪንግ ሥራ ሲያከናውን የነበረ ሲሆን፤ በተጨማሪም የመኪና መለዋወጫ ዕቃ እና መገጣጠሚያ እንዲሁም ሁለገብ የኢንጂነሪንግ ሥራዎች ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ተቋሙ ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች በመተካት በራሱ በማምረት ቴክኒካል እና ኬሚካል ሥራዎች የመሥራት ልምድ ማካበቱን ጠቅሰዋል። እንደ ከዚህ ቀደሙ ከፍተኛ የነዳጅ ተሳቢ መኪኖች እና ሌሎች ተጨማሪ ከቀላል እስከ ከባድ የኢንጂነሪንግ ሥራዎች ለመሥራት ዕቅዶች በማውጣት ወደ ሥራ እየገባ መሆኑን አስረድተዋል።
በትራንስፖርቴሽን ዘርፍ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እና የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር በማምረት ከቢዝነሱ ባሻገር አጠቃላይ የኅብረተሰቡ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ እቅድ መንደፉን በመጥቀስ፤ ስያሜውን በማደስ (ሪብራንድ) በማድረግ ወደ ተግባር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የተቋሙ የሰው ኃይል በዕውቀት እና በክህሎት የተደራጀ መሆኑን የገለጹት አቶ ተሰማ፤ ሆኖም ግን ቀደም ሲል በደረሰበት ችግር ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና እና የፖለቲካ ችግር ቢፈጠርበትም ሁሉንም ተቋቁሞ ያለ ምንም ድጋፍ አብዛኛው ሠራተኛ እስከ አሁን በጥንካሬ ሥራውን እየቀጠለ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ለቀጣይ የተያዙ ዕቅዶች ተቋሙ ካጋጠሙት ችግሮች እንዲላቀቅ እና በ2017 ዓ.ም የተሻለ ሥራ ለመሥራት ግቦችን እንዲያስቀምጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም