በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተካፈሉባቸው የግማሽ ማራቶን ውድድሮች

ይህ ወቅት በምዕራባዊ ሃገራት ሙቀት እጅግ የሚያይልበት በመሆኑ በአትሌቲክስ ስፖርት የሚካሄዱት አብዛኛዎቹ ውድድሮች የግማሽ ማራቶን ናቸው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችም ለዚህ ማሳያ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ተካፋይ ነበሩ። ከታዋቂ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በሆነው የሊዝበን ግማሽ ማራቶን አትሌት ሞስነት ገረመው አሸናፊ በመሆንም አጠናቋል።

በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ የተሰጠው የሊዝበን ግማሽ ማራቶን እአአ ከ1991 በየዓመቱ የሚካሄድ ታዋቂ ውድድር ነው። በማራቶን ሩጫም ስሟ የሚነሳው የፖርቹጋሏ ከተማ ለግማሽ ማራቶን ሯጮች ግን እጅግ ተመራጭና ምቹ እንደሆነች ይነገርላታል። በዚህም ምክንያት ሁለት ጊዜ የዓለም ክብረወሰን የተመዘገበባት ከተማ ልትሆን ችላለች። እአአ በ2010 በርቀቱ ውጤታማ የሆነው ኤርትራዊ አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ 58:23 በሆነ ሰዓት በመግባት የርቀቱን ክብር ሲቀዳጅ፤ በ2021 ደግሞ ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ በአንድ ደቂቃ ፈጥኖ በመግባት የክብረወሰን ባለቤት ሆኗል።

በበርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተመራጭ የሆነው ስፍራው ታላቅ አትሌቶችን በማሳተፍ ተደጋጋሚ ድል የተመዘገበበትም ነው። በወንዶች በኩል ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ በ2002 አሸናፊ በመሆን ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል። በተመሳሳይ እአአ በ2008 ቀድሞ ከነበረው ሰዓቱ ሰከንዶችን አሻሽሎ በመግባት የቦታው አሸናፊ መሆን ችሎ ነበር። በሴቶችም በርካታ ድንቅ አትሌቶች በዚህ ውድድር በመሳተፍ አሸናፊዎች ሆነዋል። በተለይ ተጠቃሽ የሆነችው አትሌት አልማዝ አያና ያለፈው ዓመት የገባችበት የ1:05:30 የሆነ ሰዓት የሊዝበን ግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በመሆን ተመዝግቧል። በአጠቃላይ ሲታይም በቦታው 3ወንድ እና 7 ሴት በጥቅሉ 17 አትሌቶች በአሸናፊነት ስማቸው ተጠቅሷል።

በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደው የዘንድሮው የሊዝበን ማራቶን ላይም በወንዶች ኢትዮጵያ የበላይነቱን መቀዳጀት ችላለች። እአአ የ2019 አሸናፊው አትሌት ሞስነት ገረመው በድጋሚ የቦታው ባለድል በመሆንም ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር ታሪክ መጋራት ችሏል። በማራቶን ውጤታማ የሆነው አትሌቱ በ2018 እና 2019 ቺካጎ እና ለንደን ማራቶኖች ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በመግባት በርቀቱ ያለውን ብቃት ማስመስከሩ የሚታወቅ ነው። ይህንን ተከትሎም በዶሃ የዓለም ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በመወከል ተሳትፎ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሏል። በቀጣዩ ዓመት በተካሄደው የዩጂን ዓለም ቻምፒዮናም በድንቅ አሯሯጥና የቡድን ስራ ለሃገሩ በድጋሚ የብር ሜዳሊያ ማስመዝገቡ አይዘነጋም። የግማሽ ማራቶን ተሳትፎውም እአአ ከ2013 የሚጀምር ሲሆን፤ በበርካቶቹ ውጤታማም ነበር።

ልምድ ያለው አትሌቱ በዚህ ውድድር ላይም ከኬንያዊው አትሌት ጠንካራ ፉክክር ቢገጥመውም በተለመደ ችሎታው እጅ ሳይሰጥ አጠናቋል። የገባበት ሰዓትም 01:03:09 ሲሆን ከዚህ ቀደም በቦታው ከገባበት በደቂቃዎች የዘገየም ነው። በ7ሰከንዶች ብቻ ዘግይቶ የገባው ፒተር ኪፕሲራት ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ኡጋንዳዊው ቪክተር ኬውምቦይ ደግሞ ሶስተኛ ሆኗል። በሴቶች በኩል ኬንያውያኑ አትሌቶች ተከታትለው በመግባት አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነዋል። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓለም ንጉስ ደግሞ 01:10:46 በሆነ ሰዓት ውድድሯን በሶስተኝነት ፈጽማለች።

በጣሊያን ቴልሲያ በተካሄደ ግማሽ ማራቶን በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል። በወንዶች አስማማው ዲሮ 1:03:24 በሆነ ሰዓት በመግባት ቀዳሚ ሲሆን፤ ገላኔ ጉታ ደግሞ 1:12:06 በሆነ ሰዓት በሴቶች አሸናፊ ሆናለች። እዚያው ጣሊያን በተካሄደው የትሬንቶ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይም ያለም ጌጥ ያረጋል በሴቶቹ ምድብ አሸናፊ አትሌት ሆናለች። ሌላኛው ታዋቂ የግማሽ ማራቶን ውድድር የሆነው የእንግሊዙ ካርዲፍ ግማሽ ማራቶን በሳምንቱ መጨረሻ ቢደረግም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ግን ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You