ለሰላም ከሚደረግ የመልካም ምኞት መግለጫ ባሻገር

ኢትዮጵያውያን በዓላትን ሲያከብሩ፣ ድጋፍና የመሳሰሉት ሲደረግላቸው እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ ከሚያስተላልፏቸው መልእክቶች መካከል የሰላም ጉዳይ ይጠቀሳል። ይህ ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት በቀብር ስነስርአትም ወቅት ሳይቀር ይገለጻል። በእነዚህ ስነስርአቶች ሁሉ ኢትዮጵያውያን ይመኛሉ ሰላም እንዲመለስ ፣ እንዲጠበቅ፣ እንዲበዛ፣ እንዲጠናከር።

ከተቀበልነው ሳምንታትን የቆጠረው የ2017 አዲስ አመትን በተቀበሉበት፣ የመስቀል እንዲሁም የብሔሮች ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላትን ባከበሩባቸው ወቅቶችም ይህንኑ ቁርጠኝነታቸውን፣ ከማንነታቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኘውን ማንነታቸው አረጋግጠዋል።

አዲስ አመትን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃንን የመከታተሉ አጋጣሚው የነበራችሁም ሆናችሁ ሌሎች፣ ዜጎች አዲስ አመት እንዴት ለማክበር ምን ያህል እንደተዘጋጁና የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ ተብለው የተጠየቁ ሁሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ሲሰጡ የተደመጠው ምላሽም ይህንኑ ያመላከተ ነበር። ሰላምን አጀንዳቸው ያደረጉ ናቸው።

እንኳን አደረሳችሁ ያልናቸው ሌሎች ወገኖችም ሆኑ፣ በተለያየ አጋጣሚ ስለደህንነታቸውና ስለአዲሱ አመት ያነጋገርናቸው ወገኖች ያሉትን ልብ ብለን ከሆነም እንዲሁ ከመልካም ምኞቶቻቸው መካከል የሰላም ጉዳይ አንዱ ነው።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወዘተም ይህንን ምኞታቸውን ሁሌም ሲገልጹ እንደሚደመጡት ሁሉ፤ በበአላት ወቅት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ ከሚያነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሰላም ዋንኛው ነው።

የተወለዱት እንዲያድጉ፣ የታመሙት እንዲፈወሱ፣ የታረዙት እንዲለብሱ፣ የተራቡት የተጠሙት ይበሉት ይጠጡት እንዲያገኙ ከመመኘታቸው፤ አዝመራው፣ ሀብት ንብረቱ እንዲባረክ ፈጣሪያቸውን ከመጠየቃቸው እኩል ሰላሙን እንዲያመጣላቸው፣ እንዲጠብቅላቸውም መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፤ ፈጣሪያቸውን በእጅጉ ይማጸናሉ። ሀገራቸው ሰላም እንድትሆንላቸው፣ ህዝቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ይመኛሉ።

በተለያየ አጋጣሚ አስተያየታቸው ሲሰጡ የምንሰማቸው ዜጎችም እንዲሁ ለሰላም ቅድሚያ መሰጠት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ፈጣሪ ለሀገራቸውና ለህዝቡ ሰላሙን እንዲያመጣላቸው፣ እንዲመለስላቸው፣ ያላቸውንም ሰላም እንዲጠብቅላቸው፣ እንዲያጠናክርላቸው ይመኛሉ፤ ይህን ሲሉም ሌላው ሁሉ ትርፍ መሆኑን በመናገር ጭምር ነው።

የሰላም ጉዳይ በዘወትር መንፈሳዊ ስነስርአትም አይታለፍም፤ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን ይባላል፤ ጉዳዩ በበዓላት ወቅት ደግሞ ይበልጥ አጀንዳ ተደርጎ ይያዛልና ዜጎች ለሰላም ያላቸውን መልካም ምኞት ከፍ አድርገው ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያውያን እንደየእምነታቸውና ብሄራቸው ሽምግልና ሲቀመጡም ይህን አጀንዳ አይረሱትም። ሲያስታርቁ፣ በጋብቻ ሲያስተሳስሩ፣ ወዘተ ከመልካም ምኞታቸው፣ ምክራቸው ጎንለጎን የሰላም ጉዳይ ይጠቀሳል። ከእያንዳንዱ የምርቃት ስነስርአት በኋላም ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የተመረጡ ሰዎችም ጭምር ይህንኑ ያደርጋሉ።

ይህ ስነስርአት በሰላም እጦት ሳቢያ ብዙ ለቆሰለ ሀገርና ህዝብ አጀንዳ መሆኑ ቢያንስ እንጂ አይበዛም። ስለሰላም ከዚህም በላይ ማድረግ በሚያስፈልግባት ሀገር ውስጥ እንደመኖራችን እነዚህ ስነስርአቶች ቢበዙልን እንወዳለን። ሰላምን ሁሌም ማስታወስ በእጅጉ ይጠቅማል። ሰላም እንዲጠበቅ፣ እንዲመጣ፣ እንዲሰፋ አሁንም ወደፊትም ብዙ ማድረግ እንድንችል አቅም ይሆኑናል።

እነዚህ በመልካም ምኞታቸው ሰላምን የጠቀሱ ወገኖች የሰላም አጀንዳ ሁሌም በውስጣቸው አለ። ለእዚህ ደግሞ ያለፉት መጥፎ የግጭትና የጦርነት ታሪኮች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በሀገሪቱ የተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች ምን ያህል የዜጎችን ህይወት እንደቀጠፉ፣ እንዳመሳቀሉ፣ ሀብት ንብረታቸውን እንደበሉ፣ የሀገርን ሀብትና ንብረት እንዳወደሙ በሚገባ የሚያውቁ ናቸው፤ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሰላም እጦት ልማትን እያደናቀፈ ፣ የህዝብን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለ፣ የሀገርን ገጽታም እየጎዳ መሆኑን የተገነዘቡ ናቸው። ምናልባትም በአንድም ይሁን በሌላ በዚህ የሰላም እጦት ተጎጂ ሊሆኑም ይችላሉ። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሳ የሰላም አጀንዳ ዋነኛ አቀንቃኝ ናቸው።

ሰላም የልማት ዋና መሳሪያ ከሚባሉት መካከል ሊጠቀስ ይገባዋል። የካፒታል፣ የመሬትና የሰው ኃይል ያህል ሰላም ለኢንቨስትመንትና ሌሎች የልማት ስራዎች በእጅጉ ያስፈልጋል። ይህን ሁኔታ አይደለም በሰላም እጦት ብዙ ዋጋ የከፈለች ሀገርና ህዝብ ማንም ይገነዘበዋል። እነዚህ ወገኖች ልማትን የሚናፍቁ፣ የልማት ዋነኛ ተዋናይ መሆን የሚፈልጉ ናቸውና ልማት ያለሰላም አይሆንም ብለው ስለሰላም በእጅጉ ያቀነቅናሉ።

ሰላም የሚያስፈልገው ሀብት ንብረት ላለው ብቻ አይደለም፤ ጥሩ ስራ ላለው ብቻም አይደለም። በስልጣን ላይ ተደላድሎ ለተቀመጠውም ብቻ አይደለም፤ ለሁሉም ወገን በእጅጉ ያስፈልጋል።

ምንም የሌለው፣ ያጣ የነጣውም ቢሆን ሰላምን ይፈልጋል። ሰላም ከሌለ ፣ ሰው እንደልቡ ወጥቶ ካልገባ ድጋፍ የሚያደርግለት ሊያጣ የሚችለው ይህ ዜጋም ሰላም በእጅጉ ያስፈልገዋል። የሚኖርባት ታዛ ሰላም እንዲኖራት ይመኛል። መቆሙ በሰላም መሆኑን ያውቃል።

እሱም ተመስጌን አለው። ተመስጌን ማለቱ ጤና በመሆኑ፣ በሰላም ንግቶ በመምሸቱ፣ ባሻው ውሎ በመግባቱ ወዘተ ነው። አጉራሽ አልባሾቹ በሰላም እንደልብ ወጥተው መግባታቸውንም ይፈልጋል።

እናም ሰላም የማያስፈልገው ሰብአዊ ፍጡር የለም። ሰላም ሀብት ንብረት የሚጠበቅበት፣ የሚገኝበት፣ ወዘተ. ብቻ አይደለም፤ የእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ህልውና የሚጠበቅበትም ነው።

ብዙ አጃቢ ያለውም እንዲሁ ሰላም ያለው ነው ተብሎ አይወሰድም፤ ለምን አጃቢ አስፈለገውና። ይህ ሰው የሰላም ጉዳይ አጀንዳው አይሆንም ብለው የሚያስቡ አይጠፉም፤ እነዚህ ወገኖች እሱ ምን አለበት ሊሉ ይችላሉ ተብሎ ሊታሰብም ይችላል። እውነታው ግን ሌላ ነው፤ በአጀብ መሄዱ ከሰላም እጦት እንደሚመነጭ፣ አጀቡም ሰላም ፍለጋ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።

የሰላም ትርጉሙም፣ ዋጋውም ብዙ ነው። ሰላም ከሌለ የተገነባው ሊፈርስ፣ የተከማቸው ሊዘረፍ፣ ከንቱ ሊቀር፣ የታቀደው መና ሊሆን፣ የለሰለሰው ማሳ በዘር ላይሸፈን፣ የደረሰው አዝመራ ላይሰበሰብ፣ የተከፈተው ድርጅት ላያመርት፣ ላያገለግል፣ ላይሰራ ይችላል።

ሰላም ከሌለ የሰበሰቡትን ሀብት ብቻም ሳይሆን የጎረሱትን መጣልም ይከተላል። እንደ አይን ብሌን የሚታይ የቤተሰብ አባልን፣ ወገንን ማጣትም አለ። በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ አፈናዎች ፣ ግጭቶችና ጦርነቶች ይህ ቀውስ ታይቷል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የበሉና አካል ያጎደሉ፣ ስነልቦናቸውን በእጅጉ የጎዱ፣ የሀገርን አንጡራ ሀብት ሙጥጥ አርገው የጨረሱ ግጭቶችና ጦርነቶች በሀገሪቱ ተካሂደዋል።

ኢትዮጵያውያን የሰላምን ዋጋ ታሪክ አንብበው፣ ተነግሯቸው ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ጦርነቶችና ግጭቶች ወገኖቻቸው ተገድለውባቸው አይተዋል፤ ራሳቸውም ወገኖቻቸውም ተፈናቃይ ሆነው አይተዋል፤ ቆስለው ቆስለውባቸው፣ ሞተውባቸው አካል አጥተው፣ አጥተውባቸው፣ ንብረት ወድሞባቸው አይተዋል።

የሰላም እጦት ያስከተለው ጦስ በአንድም ይሁን በሌላ በእያንዳንዱ ቤት ገብቷል፤ ለዚያውም ተመላልሶ። ቢያንስ ጦርነት ባስከተለው የምጣኔ ሀብት ድቀት የእያንዳንዱ ቤት ተፈትኗል። ኢትዮጵያውያን ይህ ችግር እንደ ውሃ ቀጂ የተመላለሰባቸውም እንደመሆናቸው የሰላምን ዋጋ በሚገባ ይገነዘባሉ። የሰላምን ጉዳይ ሁሌም አጀንዳቸው ቢያደርጉ ትክክል ናቸው።

ቀውሶቹ ኢትዮጵያውያንና መንግሥታቸው የሰላምን ዋጋ በሚገባ መገንዘብ እንዲችሉ አድርገዋቸዋል፤ ስለሰላም አጥብቀው እንዲያቀነቅኑ አድርገዋቸዋል። የሰላም ጉዳይ ከአጀንዳዎቻቸው ሁሉ ጋር እንዲነሳ እንዲያደርጉ አስገድደዋቸዋል።

ይህን ሁሉ የተመለከተ፣ የዚህ ሁሉ ጉዳት ሰለባ የሆነ ህዝብ ሰላምን በእጅጉ መሻቱ ፣ በጸሎቱም፣ በመልካም ምኞት መግለጫውም በሀዘኑም በደስታውም ሰላም ያምጣልን፤ ሰላሙን ይስጠን ማለቱ፤ ሌላው ትርፍ ነው ሲል መግለጹ ተገቢ ነው። በሰላም እጦት የተጎዳ፣ ወገኖቹና ሀገሩ የተጎዱበት በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ሰላምን ቢጠቅስ ያተርፋል እንጂ ጉንጭ አልፋ አይሆንበትም።

ሰላም እንዲመጣ፣ ያለውም እንዲጠናከር ሁሌም መመኘት አንድ ጥሩ ነገር ነው።ይህ ለሰላም ያለ ጽኑ ፍላጎት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ብቻውን ግን በቂ አይደለም፤ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ መልካም ምኞትን ከመግለጽ ባሻገር ለሰላም መስፈን መሥራትም ይገባል። ሰላምን ለማምጣቱ፣ ለማስፈኑ ፣ ያለውንም ለማጠናከሩና ለማስፋቱ ስራ እያንዳንዱ ዜጋ በኃላፊነትና በባለቤትነት ስሜት ከእኔ ምን ይጠበቃል ብሎ መስራት ይኖርበታል።

መንግሥት ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት ስለመሆኑ ሁሌም አስረግጦ ይገልጻል። ይህን የሚለው ደግሞ ህዝቡ ሰላምን በማስፈን የተጫወተውንና የሚጫወተውን ሁነኛ ሚና ታሳቢ በማድረግ ነው። ህዝቡም በእዚህ ልክ ሰላምን በማምጣት፣ በመጠበቅ፣ በማስፋትና ዘላቂ በማድረግ በኩልም በኃላፊነት ስሜት መስራት ይኖርበታል። ይህ ሲሆን የጠፋው ሰላም ይመለሳል፤ ያለውም ዘላቂ መሆን ይችላል።

እስመለአለም

አዲስ ዘመን መስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You