አዲስ አበባ፡- በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ለማሳደግ የንግድ ማህበራት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ተገለጸ።
የዓለም አቀፍ ንግድ ፖሊሲ ባለሙያ አቶ ጃሌቶ ገመዲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በቅርቡ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ዙሪያ ሊኖሩ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ውጤታማ ትግበራ እንዲኖር ለማስቻል እንዲሁም የግሉ ሴክተር እና ላኪዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ ያለመ ጥናት መካሄዱን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ዙሪያ የንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ አናሳ መሆኑን አንስተዋል። በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ለማሳደግም የንግድ ማህበራት በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የተቀመጡ አሠራሮችና ሕጎች፣ ውስብስብ የፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓቶችና የቁጥጥር ማነቆዎች ተግዳሮት እየፈጠሩ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፤ ወጥነት የጎደለው የአፈፃፀም እና የአሰራር ቅልጥፍናም እንዲሁ ተጽዕኖ እየፈጠረ ይገኛል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ላይ ያላትን ግንዛቤ የተመለከተውን ጥናት መነሻ አድርገው እንደገለጹት፤ በተለይም ከአፈፃፀሙ ጋር በተያያዙ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ተሳትፎዋን ስትቀጥል በርካታ መሰናክሎች መታየታቸውንና ይህም በሀገሪቱ ባሉ የንግድ ተዋናዮች ላይ ያለውን የእውቀት እና የግንዛቤ ክፍተት አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴዎችና የቢዝነስ ማህበረሰቦች በተለይም ወደ ውጭ በመላክ ላይ የተሰማሩት የነፃ ንግድ ቀጣና አሰራርን ለመረዳት እየቸገሩ መሆናቸውን አንስተዋል። ትክክለኛ የክትትል ስልቶች አለመኖራቸውም የታሪፍ አተገባበርን ውጤታማነት በማደናቀፍ ብዙ ኩባንያዎች አዲሱን የንግድ አካባቢ ለመምራት ዝግጁ እንዳይሆኑ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በጥናቱ ውጤት ስለ አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ብዙዎች ጋር መረጃው አልደረሰም። አብዛኞቹ ከአዲስነቱ የተነሳ አያውቁትም። ሀገር ውስጥ ሆነው የሚገበያዩ ከ70 እስከ 80 በመቶ ያህል የሚሆኑት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ግንዛቤው የላቸውም።
“ከሚያጋጥሙ ችግሮች አንዱ ከቢዝነስ አመዘጋገብ ጋር የተያያዘ ነው። ነጋዴዎች በቢዝነሱ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ላይሰንሱን ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህንን በሚመለከት እስካሁን አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ። በቀላሉ ወደ ቢዝነሱ መግባት አስቸጋሪ ነው። የሚጠበቀውን መስፈርት ከማሟላት አኳያ ችግሮች አሉ። ኢንቨስተሮችን ከማበረታት አኳያም ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።
አቶ ጃለቶ እንደገለጹት፤ ባለው ሂደት ኢንቨስተሮችን በበቂ ሁኔታ አላበረታታም። ይህ የሀገሪቷንም ፍላጎት የጠበቀ መሆን አለበት። ኢንቨስትሮች ከመጡ በኋላ ትኩረት የሚያደርጉት ትርፋቸው ላይ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ያላትን ሀብት መጠበቅ መቻል አለባት። ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ማበረታታት ያስፈልጋል።
በየክልሉ ያሉት፣ የንግድ ማህበራት ዘርፎችም አንድ ላይ ተሰባስበው ከፖሊሲ ጋር የተያያዙ ነገሮችን አንድ ላይ መስራት መቻል እንዳለባቸው፤ በገበያ ውድድር የተሻለ ነገር ከመፍጠር አንጻር ከመንግሥት አካል ጋር በመሆን ምክረ ሃሳብ አቅርበው በተሻለ መንገድ ንግዳቸውን ሊያሳልጥ የሚችል አሰራር መዘርጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገበያ ያላትን አቋም ለማሳደግ ስትፈልግ እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት እና የንግድ ምህዳሩን ማሻሻል የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ያለውን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ መሠራት አለበት ሲሉም መክረዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን መስከረም 28/2017 ዓ.ም