ከ457 ሺህ በላይ ዜጎች በወባ ተይዘዋል
አዲስ አበባ፡– በአማራ ክልል የወባ ወረርሽኝ ተጨማሪ ቀውስ እንዳያስከትል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቢሮ አስታወቀ።457 ሺህ 718 ዜጎች በወባ በሽታ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
በአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና የወባ መከላከልና ቁጥጥር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል የወባ ወረርሽኝ ስርጭት ተጨማሪ ቀውስ እንዳያስከትል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በክልሉ የታመሙ ሰዎች ተገቢውን የሕክምና መድኃኒት እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ የወባ ትንኝ የሚራባባቸው ቦታዎችን በማፋሰስ፣ አጎበር በማሰራጨት እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ወረርሽኑ ተጨማሪ ቀውስ እንዳያስከትል የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የወባ በሽታ ወረርሽኝ ተጨማሪ ጉዳት እንዳያስከትል፤ በክልሉ ድገተኛ አደጋዎች ማሳለጫ ማዕከል በኩል መረጃዎችን የመቀበል፤ የተቀበለውን መረጃ የመተንተን፤ ለሚመለከተው አካል የማድረስና አስፈላጊውን ሥራ እንዲሠራ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የወባ ወረርሽኙ አሁን እያስከተለ ካለው ጉዳት አልፎ ሌላ ቀወስ እንዳያመጣ በየዕለቱ ከዞን ባለሙያዎች ጋር በበይነ መረብ የመወያየት እንዲሁም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በየሳምንት አንድ ቀን በኦንላይን ስብሰባ የማድረግና መሠራት የአለበትን ነገር የመሥራት፤ ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዜጎች የሕመም ስሜት ሲሰማቸው በአካባቢያቸው ባለው የጤና ተቋም እንዲታከሙ፤ ለሕክምና ሲሄዱም መድኃኒት የለም ተብለው አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይመለሱ ከመድኃኒት አቅራቢዎች በቅንጅት በመሥራት የሕክምና ግብዓት እንዲሟላ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የወባ በሽታ ሕሙማን ቁጥር እንዳያሻቅብ ሁሉም ማኅበረሰብ የአካባቢውን ንፅሕና የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ ሁሉም ኃላፊነቱን የማይወጣ ከሆነ የወባ በሽታ ወረርሽኙ ዜጎችን የማጥቃት መጠኑ ከፍ ሊል ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ክልል 457 ሺህ 718 ዜጎች በወባ በሽታ ተይዘዋል፤ 31 ሰዎች በበሽታው ሞተዋል ያሉት አቶ ዳምጤ፤ በወረርሽኝ ከተጠቁት ዞኖች ውስጥ በአዊ ዞን 84 ሺህ ሰዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ከአዊ ዞን በተጨማሪ ደቡብ፣ ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞን፤ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም ዞን በቅደም ተከተል እንደሚገኙበትም ተናግረዋል፡፡
በወባ በሽታ ከተያዙት 457 ሺህ 718 ዜጎች ውስጥ 64 በመቶ የሚሆነውን ከ15 ዓመት በላይ የዕድሜ ክልል ውስጥ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ 24 በመቶ የሚሆነውን ከአምስት እስከ 14 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሸፍኑ፤ 12 በመቶ የሚሆነው ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙት ይይዛሉ ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ፤ የዝናብ መጨመርና መቀነስ፤ ማኅበረሰቡ ተገቢውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ባለመሥራቱ፤ የአጎበር አጠቃቅም ባሕሉ አናሳ መሆን፤ የተፈናቃይ መኖር የወባ በሽታ ወረርሽኝ እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡
ታደሠ ብናልፈው
አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም