በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ መቸገራቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፡በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የካምባ ከተማ አስተዳደርና ካምባ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ተቸግረናል ሲሉ ገለጹ፡፡

የካምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑትና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወርሐዊ ደመወዝ እስከ 15 ቀን ድረስ እየዘገየ ይገባል። በዚህ መሐል መምህራን ሥራ ስለሚያቆሙ ተማሪዎች እየተጉላሉና እየተበተኑ ይገኛሉ።

አሁን ላይ ጉዳዩን ይበልጥ ከባድ ያደረገው የአንድ ወር ደመወዝ መታጠፉ መሆኑን በመጥቀስ፤ የሐምሌ ወር ደመወዝ ተዘሎ የነሐሴ ወር ነው የተከፈለው። ጥሬ ገንዘብ የለም በሚል እስካሁንም ድረስ የሐምሌ ደመወዝ አልገባልንም ብለዋል።

መምህር ሌላ ተጨማሪ ሥራ የለውም የወር ደመወዙን ጠብቆ ነው የሚተዳደረው እንዲህ አይነት ችግር ሲገጥም ደግሞ የመምህራንን ኑሮ ያከብደዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ወረዳውን ስንጠየቅ ምንም ማድረግ አንችልም፤ ዞን ሲጠየቅ ደግሞ ከኔ አቅም በላይ ነው ይላሉ በማለት እስካሁን በቂ ምክንያት ማግኘት አለመቻላቸውን ቅሬታ አቅራቢው ገልጸዋል።

እንዲህ አይነት ችግሮች በመማር ማስተማሩ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው ገልጸው፤ ይህም የመምህራንን ሥነ ልቦና ከመጉዳት አልፎ የተማሪዎች ውጤት ላይም ጫና ሊያሳድር እንደሚችልና ችግሩ ሳይባባስ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የፍትሕ ጽሕፈት ቤት ዓቃቤ ሕግ ባለሙያ የሆኑ እና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የወረዳው የመንግሥት ሠራተኛ፤ ችግሩ ከባለፈው 2016 በጀት ዓመት ጀምሮ የቀጠለ ነው።እስካሁን ድረስ ችግሩ አልተቀረፈም።በዚህ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በአግባቡ ትምህርት እየሰጡ አይደለም።

በእነዚህ አካባቢዎች ለመምህራን ደመወዝ እየዘገየ በመከፈሉ ምክንያት ትምህርት በአግባቡ አልተጀመረም ያሉት ባለሙያው፤ በሠራተኞች ደመወዝ መዘግየት ምክንያት የጤና ተቋማትን ጨምሮ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በ2016 ሙሉ ዓመቱን የወር ደመወዝ ወሩ ካለፈ በኋላ ይከፈል እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም የአካባቢው የመንግሥት ሠራተኞች ብዙ ፈተናዎችን እንዳሳለፉ አስታውቀዋል። በተለይ ሐምሌና ነሐሴ ወራት ላይ ይህ ክስተት ከበድ ያለ ነበር በማለት ከክረምቱ ወራት የአንዱ ወር ደመወዝ እስካሁን እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

መምህራን ደመወዛቸው ሲዘገይ ሥራቸውን እያቆሙ እንደሆነ፤ ተማሪውም ትምህርቱን አቋርጦ እየጠፋ እንዳለና ይህም የመማር ማስተማሩን ሂደት እያስተጓጎለው መሆኑን ጠቅሰዋል።ይህ የብልሹ አሠራር ማሳያ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።

“በዚህ ጉዳይ ከወረዳው ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ላሉ አስፈጻሚ አካላት ጥያቄ ብናቀርብም መፍትሔ ማግኘት አልቻልንም” ያሉት የመረጃ ምንጩ፤ ጥያቄ ስናቀርብም ወረዳው ወደ ዞን፤ ዞኑ ወደ ወረዳው በመጠቆምና ችግሩን ራሳችሁ ፍቱት ከማለት ውጭ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያትም የካምባ ከተማ አስተዳደርና ካምባ ዙሪያ ወረዳዎች የመንግሥት ሠራተኞች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እያለፉ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ከደመወዝ መዘግየት ባሻገር አንዳንድ ጊዜ ባልታወቀ ምክንያት ብር ተቀንሶ የሚገባበት አጋጣሚ ስለመኖሩም ተናግረዋል።ምክንያቱ ሲጠየቅም ምላሽ እንደማይሰጣቸው ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቅሬታ አቅራቢዎችን ጥያቄ በመያዝ ለወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ጎንችሬ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል ቢጠይቅም አንድ ጊዜ መስክ ላይ ነኝ፤ ሌላ ጊዜ ማንነታችሁን የሚገልጽ ማረጋገጫ ላኩልኝ በማለት ማረጋገጫው ተልኮላቸውም በተደጋጋሚ ስልክ ሲደወልላቸው ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።

ከዚህም በተጨማሪ ኢፕድ ክልሉንና ዞኑን ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርግም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ወረዳዎችን ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቶታል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You