አሜሪካ በየመን የሁቲ አማፂያን የሚገኙበትን በርካታ ስፍራዎች ደበደበች

የአሜሪካ ጦር በኢራን የሚደገፉ እና በየመን የሚንቀሳቀሱ የሁቲ ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸውን 15 ቦታዎች መደብደቡን አስታወቀ። ፔንታጎን የአየር ኃይሉን እና የጦር መርከቡን በመጠቀም “የውቅያኖስ ላይ እንቅስቃሴን ለመከላከል” በሚል ጥቃቱን መክፈቱን አስታውቋል። ሰንዓን ጨምሮ በተወሰኑ የየመን ከተሞች በርካታ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ከባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚቀዝፉ ከ100 በላይ መርከቦች ሲያጠቁ ሁለቱን ደግሞ ማስመጣቸው ይታወሳል። የአማፂ ቡድኑ ጥቃቱን የከፈቱት እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ በመቃወም ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚከታተለው ማዕከላዊ ዕዝ እንዳለው ከሆነ የአየር ድብደባው ዒላማ ያደረገው የጦር መሣሪያ የሚገኝባቸውን፣ የጦር ካምፖች እና የሁቲዎች ንብረት የሆኑ መሣሪያዎች ያሉባቸውን ስፍራዎች ነው።

ለሁቲ ቅርበት ያለው አንድ መገናኛ ብዙኃን በአሜሪካ የአየር ጥቃት ከተመቱት ከተሞች መካከል የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ትገኝበታለች። ሰኞ ዕለት ሁቲዎች አሜሪካ ሠራሽ የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን መትተው መጣላቸውን ተናግረው ነበር። አሜሪካም ሰው አልባ አውሮፕላኑ ተመትቶ እንደወደቀባት አረጋግጣለች።

ባለፈው ሳምንት ፔንታጎን እንዳለው ከሆነ የሁቲ አማፂያን በቀጣናው በሚገኘው የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ “የተቀናጀ ጥቃት” ቢከፍቱም የተኮሷቸው መሣሪያዎች ሁሉ ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት ከሽፈዋል። ሁቲዎች በቀይባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ከማጥቃታቸው ባሻገር በቀጥታ ወደ እሥራኤል ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ እንዲሁም የድሮን ጥቃትም ይፈጽማሉ።

በሐምሌ ወር ከየመን የተነሳ ድሮን በቴልአቪቭ አንድ ሰው ሲገድል 10 አቁስሏል። ባለፈው ወር ቡድኑ በቴልአቪቭ የሚገኝ ዋና አየር ማረፊያን ዒላማ ያደረገ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሚሳዔሎችን ወደ እሥራኤል አስወንጭፏል። እሥራኤል ከሁቲ አማፅያን ለሚደርስባት ጥቃት በሙሉ አጸፋዊ ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ፣ ዩኬ እና 12 ሌሎች ሀገራት በቀይ ባሕር ላይ ያለውን የመርከቦች ዝውውር ከሁቲ አማፂያን ጥቃት ለመጠበቅ በሚል በጋራ ጥቃት ከፍተው ነበር። ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ከምትደግፋቸው አማፂያን መካከል ሄዝቦላ በሊባኖስ፣ ሐማስ በጋዛ፣ ሁቲዎች ደግሞ በየመን ይገኛሉ ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You