የአየር ኃይሉ ጀግና

የአንዳንድ ሰዎች ገድል በሰፊው ይዘመርለትና ገናና ይሆናል፡፡ የአንዳንድ ሰዎች ገድል ደግሞ በብዙዎች ዘንድ ልብ የማይባል፤ ይባስ ብሎም የማይታወቅ ይሆናል፡፡ የእኚህ ጀግና ታሪክ ደግሞ እንዴትም ቢገለጽ ጀግንነታቸውን ሊገልጸው አይችልም፡፡ በሰማይ ላይ እንደ ውሃ ዋና የተገላበጡ ናቸው፡፡ በሰማይ ላይ የጠላት የጦር አውሮፕላንን ያጋዩ ናቸው፡፡ ከ8 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ብርጋዴር ጄኔራል ለገሰ ተፈራ የዚህ ሳምንት ክስተት ናቸውና በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ገድላቸውን እናስታውሳለን፡፡

ለገሰ ተፈራ በ1934 ዓ.ም ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴና ከወይዘሮ ተናኜ ተክለ ወልድ ለቤተሰቡ የበኩር ልጅ ሆኖ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለደ፡፡ ሕፃኑ ለገሰ እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው ወደነበሩት የኔታ ቸርነት የተባሉ መምህር ዘንድ እየሄደ የቄስ ትምህርት ተምሯል። የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በደጃዝማች ወንድይራድ እና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል፡፡

ለገሰ ሐረር የጦር አካዳሚ እንዲገባ የተደረገው በንጉሠ ነገሥቱና በሌተናል ጀኔራል አቢይ ምርጫና ምክረ ሃሳብ ነበር፡፡ የተቀላቀለው አካዳሚ በልዩ ባለሙያዎች የተዋቀረና የተደራጀ የላቀ ወታደራዊ መቅሰሚያ ማዕከል ነበር።

የመከላከያ ሚኒስቴር አየር ኃይል ለበረራ የሚቀበላቸው እጩ መኮንኖች በቂ የሆነ የወታደራዊ ሥልጠና ያገኙ መሆን አለባቸው የሚል መመሪያ አወጣ፡፡ የአየር ኃይል ትምህርት ክፍል ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ እየሄደ መመልመል ጀመረ። ለገሰ ተፈራ አየር ኃይል የሚፈልገውን መስፈርት አሟልተው ከተገኙ መካከል አንዱ ሆነ፤ የአየር ኃይል የበረራ ትምህርት ቤት አባልም ለመሆን በቃ። የበረራ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅም ጀት አብራሪ እና የበረራ አስተማሪ ሆነ። በሀገር ውስጥ ካገኙት የበረራ ትምህርት በተጨማሪ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከፍ ያለ ወታደራዊና የበረራ ትምህርት ቀስመዋል። በተለይም በአሪዞና የአየር ኃይል ማሠልጠኛ ተቋም ከበረራ ጋር የተያያዘ የመሣሪያ አጠቃቀም ትምህርትን አጥንተዋል።

በ1962 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የጨበጠው የሶማሊያው መሪ ሜጀር ጀኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ቅኝ ገዢ ኃይሎችና የሶማሊያ ቀድሞ መሪዎች ያስተጋቡት የነበረውን ‹‹ታላቋ ሶማሊያ››ን የመፍጠር ሕልም ለማሳካት ጦሩን ሲያደራጅ ቆይቶ ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ በዚህ ወቅት ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ የዘጠነኛው ስኳድሮን አባል ሆነው ተሰለፉ፡፡

ሐምሌ 14 ቀን 1969 ዓ.ም የአየር ለአየር ውጊያ ተጀመረ። የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያን የሲቪል አውሮፕላን መትቶ ጣለ፡፡ ይህ እንደተሰማም ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስና ኮሎኔል መንግሥቱ ካሣዬ ወደ ቦታው በረሩ፡፡ ሁለት የሶማሊያ ሚግ-21 የጦር አውሮፕላኖች ተመሳሳይ ጥፋት ለማድረስ በኢትዮጵያ የአየር ክልል ውስጥ እየበረሩ አገኟቸው፡፡ ኮሎኔል በዛብህ እና ኮሎኔል መንግሥቱ ውጊያ ለመግጠም ፊታቸውን አዞሩ፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ቀረብ ብሎ በታያቸው የሶማሊያ ጦር አውሮፕላን ላይ ሲተኩሱበት አውሮፕላኑ ለሁለት ተገምሶ ወደቀ፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ደግሞ ወደ ሌላኛው የሶማሊያ የጦር አውሮፕላን ለመተኮስ ሲዘጋጁ የሶማሊያው ፓይለት ፊቱን አዙሮ ሸመጠጠ፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱና ሶማሊያዊው ፓይለት የያዟቸው የጦር አውሮፕላኖች በፍጥነትም ሆነ በጉልበት ስለማይመጣጠኑ ወራሪው ፈርጥጦ ነፍሱን አተረፈ፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስና ኮሎኔል መንግሥቱ ካሣዬ በድል አድራጊነት ተመለሱ፡፡

በአየር ለአየር ውጊያ የጦር አውሮፕላኗን ያጣችው ሶማሊያ ለበቀል እርምጃ ሦስት ሚግ-21 አውሮፕላኖችን አሠማራች፡፡ አውሮፕላኖቹ የሶማሊያን የአየር ክልል ሳያልፉ የኢትዮጵያ የራዳር ሠራተኞች ስላዩዋቸው ትዕዛዝ መጣ። ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ተነገራቸው፡፡ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ ኪዳኑ አብረዋቸው ተመደቡ፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ለባልደረቦቻቸው ‹‹ሦስት ሚጎች ናቸው፤ ታዲያ እንግዲህ አንድ አንድ ይድረሰና!›› አሉ በቀልድ መልክ፡፡ ሦስቱም ጀግኖች ወደ ኤፍ-5 የጦር አውሮፕላኖቻቸው ገቡ፡፡ ተንደርድረው ወደ ሰማይ ተፈተለኩ፡፡

የራዳር ሠራተኞች የጠላት አውሮፕላኖች የት እንዳሉና በምን ያህል ከፍታ እንደሚበሩ ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ አስታወቁ፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ደግሞ መረጃውን ለባልደረቦቻቸው ገለፁ፡፡ ከላይ ወደታች ለማጥቃት በማሰብ ከጠላት አውሮፕላኖች በላይ ከፍ ብለው መብረር ጀመሩ፡፡ የጠላት አውሮፕላኖች በመሣሪያቸው የዒላማ ወሰን ውስጥ ሲገቡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ሰንጥቀው (ዳይቭ አድርገው) ገቡ፡፡ የሶማሊያ ፓይለቶች አንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ አጋጥሟቸው ስለማያውቅ በጣም ደነገጡ፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መተኮስ ሲጀምሩ ጎን ለጎን የነበሩት የጠላት አውሮፕላኖች ወደ ግራና ወደ ቀኝ ታጠፉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ እርስ በእርስ ተላተሙና ብትንትናቸው ወጣ፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ፈገግ ብለው ወደ ባልደረቦቻቸው ሲመለከቱ ኮሎኔል ባጫ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ የተረፈውን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላን ሲያባርሩ ተመለከቱ፡፡ እርሱም ብዙ ሳይሄድ ከመሬት ጋር ተላተመ፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰም ‹‹የሰውን መሬትና አየር በግፍ ጥሶ የገባ እኛ ብቻ ሳንሆን ተፈጥሮም ይታገለዋል›› አሉ፡፡

በሁለት ቀናት የአየር ለአየር ውጊያ የዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ አራት የጦር አውሮፕላኖቿን አጣች፡፡ የሁለቱን ቀናት ጨዋታ ኢትዮጵያ 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈች። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰና ባልደረቦቻቸውም አስደናቂ የጀግንነት ጀብድ ፈፅመው በድል አድራጊነት ተመለሱ፡፡

የሶማሊያ ጦር ኃይሉን አጠናክሮ መጠነ ሰፊ የማጥቃት ዘመቻ ከፍቷል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር በከፍተኛ ወኔ እየተዋጋ ቢሆንም ርዳታ ካላገኘ ድሬዳዋ በጠላት እጅ መውደቋ ስለማይቀርና አየር ኃይል ድሬዳዋን የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት ስለተጣለበት የአየር ኃይል አባላት ለዘመቻው ተዘጋጁ፡፡ በወቅቱ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ የተመደቡት ለአየር በአየር ውጊያ ነበር፡፡

የሀገር ፍቅር፣ ጀግንነት፣ እልህና ቁጭት የተቀላቀለበት የአየር ላይ ጉዙ ወደ ድሬ … ለቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች የተመደቡት እነ ብርጋዴር ጀኔራል አምሃ ደስታ (በኋላ ሜጀር ጀኔራል እና የአየር ኃይል ዋና አዛዥ) በድሬዳዋና አካባቢው ሰፍሮ የነበረውን የሶማሊያን ጦርና ከባድ መሣሪያዎቹን አመድ አደረጉት፡፡ አሁን ተራው የነብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ነው፡፡ ከራዳር ሠራተኞች የመጣው መልዕክት ደረሳቸው፡፡ ሁለት የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ዕይታቸውና ኢላማቸው ውስጥ ሲገቡላቸው ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ‹‹በግፍ ስለደፈራችኋት ኢትዮጵያ››፣ መቶ አለቃ አፈወርቅ ደግሞ ‹‹ስለ ድሬ›› ብለው ሁለቱን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ወደ አመድነት ቀየሯቸው፡፡ ሁሉም የአየር ኃይል አባላት የድሬዳዋን እንባ ጠርገው በድል ተመለሱ፡፡

ከዚህ በመቀጠል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋነኛ ትኩረት በሶማሊያ ጦር ከባድ መሣሪያዎችና አየር መቃወሚያዎች ላይ ሆነ፡፡ ‹‹ … የሶማሊያ ጦር አየር መቃወሚያና ከባድ መሣሪያ ጂግጂጋ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግረኛ ጦር እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ሆኖበታል …›› የሚል መልዕክት ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መጣላቸው፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እና ብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ገብረፃድቅ ተመድበው ወደ ቦታው ሄዱ፡፡ ወዲያው ግን ሁለት ሚግ-21 የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖች ከሃርጌሳ ወደብ መነሳታቸው ለነብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተነገራቸው፡፡ ሁለቱም በፍጥነት ወደላይ በመውጣት የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖችን ዒላማቸው ውስጥ በማስገባት ፋታ ሳይሰጡ አጋዩዋቸው፡፡ ከዚች ቀን በኋላም የሶማሊያ ጦር አውሮፕላኖች ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል ሳያዞሩ ቀሩ፡፡

ጦርነቱ ሲጀመር ሶማሊያ 28 ሚግ-21፣ ኢትዮጵያ ደግሞ አራት ኤፍ-5 ተዋጊ አውሮፕላኖች ነበሯቸው፡፡ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን ሶማሊያ ከ20 በላይ የጦር አውሮፕላኖችን አጥታ አራት ብቻ ቀሯት፡፡ ከነዚህ መካከል ደግሞ አምቱን የሶማሊያ የጦር አውሮፕላኖች ያረገፏቸው ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ናቸው፡፡

ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እና ብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ገብረፃድቅ ከግዳጅ በድል ተመልሰው ምሳ ለመብላት እየተዘጋጁ ሳለ የሶማሊያ ጦር በኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ እየተመራ በባሌ በኩል ከፍተኛ ጥቃት ስለከፈተ ርዳታ እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበላቸው፡፡ አንድ ጉርሻ ሳይጎርሱ ከነድካማቸውና ከነረሃባቸው ለግዳጅ ተሰማሩ፡፡

በዕለቱ ግዙፉንና እጅግ በጣም ከባድ ለሆኑ ውጊያዎች የሚሠማራውን ካምቤራ ቢ-52 የጦር አውሮፕላን ለማጀብ የተጓዙት ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ፣ የጠላት አሰላለፍ እንዴት እንደሆነ ለካምቤራው አብራሪ ብርጋዴር ጀኔራል መስፍን ኃይሌ ለማሳወቅ ዝቅ ብለው መብረር ሲጀምሩ የሶማሊያ ጦር ሁሉንም መሣሪያዎቻቸውን ተኮሱ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳካላቸው፤ የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ አውሮፕላን ተመታች፡፡ ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ ጭስ በጭስ ሆኗል። ጭሱ እርሳቸውን ለመዋጥ እየተሳበ እየመጣ ነው። ኃይለኛ ሙቀትም ተከሰተ። ሁኔታውን ለብርጋዴር ጀኔራል አሸናፊ ለመንገር ሬድዮናቸውን ቢሞክሩ እምቢ አለ። በአደጋ ጊዜ መገናኛ በኩል ግንኙነት ለማድረግ ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀረ።

‹‹ትንሽ ትሂድና ከጠላት ዕይታ ልዳን›› ብለው በረራ ቀጠሉ። አውሮፕላኗ ግን ከዳች፡፡ መውረድ ጀመረች። ፓራሹቱ በደንብ የሚዘረጋበትና የሚሠራበት ተገቢ ከፍታ ላይ እንዳልነበሩ ቢያውቁም አብሮ ላላመቃጠል ሲሉ ዘለሉ፡፡ ጀግናው እና አውሮፕላናቸው በተለያየ አቅጣጫ ወደ መሬት ወረዱ፡፡ የስፖርት ሰው መሆናቸው ከፈጣሪ ርዳታ ጋር ተደምሮ አየር ላይ ብዙ ሳይቆዩ ወረዱ። የጠላት ወታደሮች ግን ፓራሹቱ ሲወርድ አላዩትም ነበርና ወዲያውኑ አልያዟቸውም። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ራሳቸውን አንበሳ፣ ነብርና ሌሎች ግዙፍና ጥቃቅን ፍጥረታት በሚርመሰመሱበት ጫካ ውስጥ አገኙት፡፡ ስለቀጣይ እጣ ፋንታቸው እያሰላሰሉ ባሉበት ቅፅበት ከነድካማቸውና ከነረሃባቸው እንቅልፍ ሸለብ አደረጋቸው፡፡

እንዳይነጋ የለም ነጋ፡፡ ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ የአካባቢው ልጃ ገረዶች ከወንዝ ውሃ ቀድተው ሲመለሱ ተመለከቱ፡፡ ልጃ ገረዶቹ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ሲያዩዋቸው ተደናገጡ፡፡ በእጃቸውም ‹‹ና›› የሚል ምልክት አሳዩዋቸው፡፡ ይዘውት ከነበረው ውሃም አጠጧቸው። ወደ ቤት ይዘዋቸው ሄደውም የሚበላና የሚጠጣ ሰጧቸው። ልጃገረዶቹ የኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ወታደሮች ቤተሰቦች ስለነበሩ ‹‹ባይተዋር ሰው ከሰፈራችን መጥቷል›› ብሎ የሚናገር ሰው ወደ ወታደሮቹ ልከው ነበር፡፡ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ በስድስት ታጣቂ ወታደሮች ተከበቡ፡፡ ‹‹እጅህን ስጥ›› ተባሉ። መሣሪያቸውንም እንዲያስረክቡ ተነገራቸውና አስረከቡ።

ኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ራሱ መኪናውን ይዞ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ካሉበት ቦታ ድረስ መጣ። የማሸነፍ ስሜት ይታይበታል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ሲዋጉ፣ ሲከላከሉና ሲያጠቁ የተለዩ ስለሆኑ ለሶማሊያ ወታደሮች የተነገራቸው እንደሰው ሳይሆን ልዩና አዲስ ፍጡር ተደርገው በመሆኑ እነዚያ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ‹‹እጅ ወደ ላይ›› ያሉት ለመንካት ፈርተዋቸው ነበር። የአየር ኃይል ሰው መያዛቸውንም ተጠራጠሩ። ዛሬ ሶማሊያ በለስ ቀንቷታል። የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ዋርካ ጥላለች። በእርግጥ ሁሉም የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ለሶማሊያ እኩል አስፈሪና አደገኛ ቢሆኑም የአየር ኃይሉ ፈርጥ መማረክ ግን በቀላሉ የሚታይ አልነበረም፡፡

ማስተር ቴክኒሺያኖቹ ኰሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ሞቃዲሾ ላለው የዚያድ ባሬ መንግሥት ስለሁኔታው ያስተላለፈውን መልዕክት ጠልፈው ሲያገኙት የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ መማረክ በኢትዮጵያ ጦር ዘንድ ታወቀ፡፡ ኮሎኔል አብዱላሂ የሱፍ ‹‹ሰውዬው ከነብር የበለጠ ቁጡ ነው፤ በጠላት እጅ የገባም አልመሰለው፤ ተለሳላሽ አይደለም፤ ሰው ሲማረክ እኮ ትከሻውን ይሰብራል፤ የማረከው እንዲራራለትም አንገቱን ይደፋ ነበር፡፡ ይህ ሰው ግን ለየት ያለ ነው። ግድ ያለውም አይመስልም። መረጋጋቱና ኩራቱ ያናድዳል። ወደናንተ ስልከው ይህንን ትዕቢቱን፣ ቁጣውን፣ መረጋጋቱንና ኩራቱን ከውስጡ ጨምቃችሁ ማውጣት አለባችሁ። አሁን ባለበት ከቀጠለ ለወደፊት የሚመጡትም እንዲሁ ይቀጥላሉ። ስለዚህ ሶማሊያ ማን እንደሆነች እንዲያውቅ መማር ይኖርበታል›› እያለ ለአለቆቹ ሲናገር ተደምጧል።

የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ ሁለት እጆች የኮሎኔል አብዱላሂ መኪና ላይ ታስረው ለሶስት ሰዓታት ያህል እንደተጓዙ ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰን ወደ ሞቃዲሾ እንዲወስድ የተዘጋጀው አውሮፕላን ዘንድ ደረሱ። ከመኪናው እንዲወርዱ ተደርጎ እጅና እግራቸውም በሰንሰለት አብረው ታሰሩ፤ ከአውሮፕላኑም ኋላ ወስደው ሸጐጧቸው፡፡ ምርኮኛውን ከኮሎኔል አብዱላሂ ተረክበው ለዚያድ ባሬ እንዲያስረክቡ የተላኩት ሁለት ሰዎች (የዚያድ ባሬ የሃይማኖት ዋና መሪ የነበሩት ሼህ መሃመድ አሊና የመከላከያ ሚኒስትሩ ጀኔራል መሃመድ አሊ ሰመተር) አውሮፕላኑ ውስጥ ነበሩ።

የሃይማኖት ዋና መሪው የብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እግሮችና እጆች እንዲፈቱና አጠገባቸው አምጥተው እንዲያስቀምጧቸው ትዕዛዝ ሰጡ። የመከላከያ ሚኒስትሩ ራሳቸውን ለብርጋዴር ጀኔራል ለገሰ እጅግ ክብር ባለው መንገድ አስተዋወቁ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰም በኢትዮጵያዊ ትህትናና በወታደራዊ ቅልጥፍና ራሳቸውን አስተዋወቁ።

እነዚህ ሶስት ሰዎች ሲነጋገሩ ለዘመናት ተለያይተው የተገናኙ ጓደኛሞች እንጂ ጠላቶች አይመስሉም። ስለብዙ ጉዳዮች ተጨዋወቱ፡፡ ሳያስቡት አውሮፕላኑ ሞቃዲሾ መድረሱ ተነገራቸው፡፡ ሁለቱም ሰዎች ‹‹ስንለይህ እናዝናለን። ጊዜ ፈቅዶ ብዙ ብንጫወት መልካም ነበር፡፡ አይዞህ›› ብለዋቸው ተሰነባብተው ተለያዩ። ብርጋዴር ጀኔራል ለገሰም ከገቡ በሕይወት ተመልሰው ወደማይወጡበት ‹‹ሸሌ ሞርቶ›› በተባለው እስር ቤት በልዩ ስሙ ሳታንቡር ተብሎ ወደሚታወቀው ክፍል ተላኩ። በእስር ላይ በነበሩባቸው ጊዜያትም የጦሩ አባላት በተለይ የአየር ኃይል ባልደረቦቻቸውና ሠራዊቱ መንግሥት ከእስር እንዲያስፈታቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎችንና ተማፅኖዎችን ያቀርቡ ነበር፡፡ ከ11 ዓመታት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ተለቀቁ፡፡ የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጀግና ሜዳይ ተሸላሚም ሆኑ፡፡

የ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፡፡ በዚያው ሲኖሩ ቆይተውም መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም አርፈዋል፡፡ አስከሬናቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሥርዓተ ቀብራቸው ተወልደው ባደጉባት፣ በሚወዷትና ዋጋ በከፈሉላት እናት ሀገራቸው ምድር ተፈፅሟል፡፡

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You