በጅማ አቅራቢያ የሚኖሩት ቀመር አባቢያ እና አባጎጃም አባ ጅርጋ ተጋብተው ብዙም ሳይቆዩ ጃፋር አባጎጃምን ወለዱ። በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ አቅራቢያ ዶዶ ወረዳ ግንጆ ሰረር አካባቢ የተወለደው ጃፋር፤ የቤቱ ልዩ ልጅ ሆኖ በተቀማጠለ መልኩ ማደግ ጀመረ። ምንም እንኳ ጃፋር በ1995 ዓ.ም ሲወለድ በቤታቸው ደስታ ሞልቶ ቢሰነብትም ብዙ ዓመታት አልተቆጠሩም። በእንክብካቤ እየቦረቀ ከአካባቢው ልጆች ጋር እየተጫወተ ያደገው ጃፋር፤ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ጅማ ከተማ ላሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ፤ መማር ቢጀምርም ብዙ አልቀጠለም።
ገና ሶስተኛ ክፍል ሲደርስ የመማሩ ጉዳይ አደጋ ላይ ወደቀ። ወላጆቹ ልጃቸውን ማስተማር የማይችሉበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ጃፋር ጓደኞቹ ትምህርት ቤት ሲሔዱ እርሱ ግን ቤት መቀመጥ ግዴታ ሆነበት። ለእናቱ እያገለገሉ ዓመታት ተቆጠሩ። እኩዮቹ እየተማሩ እርሱ ግን ቤት መቅረቱ አስከፋው። ጃፋር አንድ ሃሳብ መጣለት ‹‹ የፈለጉትን ሥራ ሠርተው ያድጉባታል›› እየተባለች ወደሚነገርላት አዲስ አበባ ለመሄድ አሰበ። ነገር ግን በቀላሉ ሊሆንለት አልቻለም። በብዙ ውጣ ውረድ እና ፈተና በ18 ዓመቱ በ2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ።
አዲስ አበባ እንደፈለጋት እና እንዳሰባት በቀላሉ የሠራ ሁሉ የሚያድግባት አልሆነችለትም። እየተሸከመ እና እየተሯሯጠ ለመሥራት ቢታትርም፤ ለብቻውን ቤት ተከራይቶ መኖር እና በሚፈልገው መጠን ራሱን እየጠበቀ ማደግ አልቻለም። ጃፋር አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ሞከረ።
ነገር ግን የሚያገኘው ገቢ የቤት ኪራይ ለመክፈል እና ቀለብ ለመቻል የሚበቃ አይደለም። ስለዚህ ሌላ ሥራ መፈለግ ጀመረ። አዲስ ከገጠር ለሚመጣ ሰው ዳቦ ቤት መቀጠሩ ጥሩ መሆኑን እና ለማደግም እንደሚመች ሰማ። ዳቦ ቤት ተቀጥረው ሲሰሩ ማደሪያም ስለሚመች የቤት ኪራይ ወይም የማደሪያ ወጪ እንደማያሳስብ ሲያረጋግጥ ዳቦ ቤት ለመቀጠር ወሰነ።
ለዘመዶቹ እና ጅማ ከተማ አቅራቢያ እያለ ከቤተሰቡ ጋር ለሚቀራረቡ ለነበሩ አዲስ አበባ ላሉ የአካባቢው ሰዎች በዘመድ ዳቦ ቤት እንዲያስቀጥሩት ጠየቀ። ብዙም ሳይቆይ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዳቦ ቤት ተገኘለትና መቀጠር ቻለ። እንዳሰበው ምግብም ሆነ መኝታን የሚያመቻቸው የዳቦ ቤቱ ባለቤት ነው። ነገር ግን የሚበላውም ሆነ የሚታደረው በጋራ ነው። በግል መተኛ አለመኖሩን ቢያውቅም አልተከፋም።
ፅዳት የሚወደው ጃፋር
ሙስጠፋ ዳቦ ቤት የተቀጠረው ጃፋር፤ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ሥራውን ለመደ። ሊጥ ሲቦካ አብሮ ያቦካል። ሊጥ እየተመጠነ ባትራ ላይ ሲደረደር አብሮ ይደረደረል። ባትራ ዳቦ ማብሰያ ማሽን ውስጥ ይጨምራል። ዳቦ ሲበስል ተከታትሎ ያወጣል። ዳቦ ተጋግሮ እንዳለቀ እጁን፣ አንገቱን እና ፀጉሩን ይታጠባል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም ዳቦ ጋጋሪዎች በጋራ የሚተኙበትን ቤት ያፀዳል።
ጃፋር አብረውት የሚሠሩት እና አብረውት የሚተኙት ሠራተኞች እራሳቸውን ለመጠበቅ ዝግጁ አይደሉም። ፍራሽ ማንጠፍ እና ቤት ማፅዳት አያውቁም። ጃፋር በበኩሉ ፍራሹ በትክክል እንዲነጠፍ እና ቤቱ እንዲፀዳ ይፈልጋል።
አብረውት የሚያድሩት የሥራ አጋሮቹ ቤት አለማፅዳታቸው ብቻ ሳይሆን አለመታጠባቸው እና ራሳቸውን አለመንከባከባቸው በእጅጉ ያበሳጨዋል። ሰፈሩ የሰለጠነ ቦሌ አካባቢ 66 አፓርታማ አጠገብ በመሆኑ፤ በመንገድ ላይ የሚታዩት እና ሙስጠፋ ዳቦ ቤት ዳቦ ሊገዙ የሚመጡት ሰዎች ዘናጮች ናቸው።
ጃፋር ሞልቶለት እንደሚያያቸው ሰዎች ሽቶ ተነስንሶ በመልካም ጠረን አካባቢውን ማወድ ባይችልም፤ በላብ እና በመጥፎ ጠረን ሰዎችን እንዳይረብሽ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋል። ሥራው አድካሚ በመሆኑ ከሰውነቱ የሚወጣው ላብ የተለየ ነው። እርሱም ላቡን በየቀኑ ይታጠባል። ሌሎች የሥራ ጓደኞቹ ግን እንደ እርሱ አይታጠቡም። ፀጉራቸው እና ልብሳቸው ዱቄት እንደተነሰነሰበት አድረው፤ ዱቄት እንደተነሰነሰባቸው ይውላሉ። ሲተኙም ሲነሱም ፅዳት ብሎ ነገር አይገባቸውም።
መጥፎ አጋጣሚ
ጥቅምት 18 እነጃፋር በጊዜ የዳቦ ጋገራቸውን ጨርሰዋል። ጃፋር እንደለመደው ተጣጥቦ መተኛቸውን ለማፅዳት መጥረጊያ አነሳ። አብሮት የሚሰራው አህመዲን ሲራጅ በበኩሉ እንደ ጃፋር ተጣጥቦ ቤቱን ከማፅዳት ይልቅ፤ ሥራውን ከጨረሰበት ሰዓት ጀምሮ በስልኩ እየተጫወተ ይዝናናል። ጃፋር በአህመዲን ሁኔታ ተናዷል። ጃፋር የያዘውን መጥረጊያ በኃይል እያዘዘ የቤቱ ወለል ሲጠርግ፤ በዱቄት ልብሱ እና ፀጉሩ የተሸፈነው አህመዲን ላይ አቧራው ቦነነ።
አህመዲን ተቀምጦ በሞባይሉ መጫወቱን ትቶ ተነሳ። ‹‹ምን ማለትህ ነው? አቧራ ለምን ታቦንብኛለህ?›› ብሎ አፈጠጠበት። ጃፋር በበኩሉ፤ ‹‹እና ምን ላድርግህ ቤቱ አይጠረግ?›› ሲል ጥያቄ አቀረበ። አህመዲን ‹‹ አዎ አይጠረግ ›› ሲል ምላሽ ሰጠው። ጃፋር ‹‹ታዲያ አይጠረግ? ቦርኮ›› ብሎ ተሳድቦ ቤት መጥረጉን ቀጠለ። አህመዲን ስልኩን ወርውሮ የጃፋርን አንገት አነቀው። ጃፋር ያነቀውን አህመዲንን አርቆ ወረወረው። አህመዲን በድጋሚ ከወደቀበት በመነሳት ጃፋርን በጥፊ መታው። ጃፋር እጁን ጨብጦ ወደ አህመዲን ሆድ ቦክስ ሰነዘረ፡፡
አህመዲን የጃፋርን ቡጢ መቋቋም አቃተው፤ ሆዱን በእጁ ይዞ አጎነበሰ። ጃፋር ባለ በሌለ ኃይሉ ያጎነበሰውን አህመዲንን በክርኑ ጀርባውን መታው፤ አህመዲን በግንባሩ ወደቀ። ጃፋር አህመዲን ላይ ጨከነ። በደረቱ የተደፋው አህመዲንን ደጋግሞ በቀኝ በኩል ጭንቅላቱን ረገጠው። አህመዲን ከአፍ እና ከአፍንጫው ደም መፍሰስ ጀመረ። ጃፋርን ያስቆመው አልነበረም። አህመዲን ከወደቀበት ሳይነሳ በጃፋር እየተደበደበ ሕይወቱ አለፈ። ጃፋር የአህመዲን ሕይወት ሲያልፍ፤ እርሱም መምታቱን አቁሞ ተቀመጠ። ሰዎች ተሰባስበው ሲጯጯሁ አህመዲን ከተቀመጠበት አልተነሳም። ፖሊስ ጠርተው አስያዙት።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ወዲያው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አዋለ። የምርመራ ቡድኑ የሟች አስክሬን ፎቶ ካነሳ በኋላ፤ የአህመዲንን አስክሬን ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ላከ። ፖሊስ በጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው 66 አፓርታማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወንጀል መፈፀሙን አረጋግጦ ማስረጃ ማደራጀት ጀመረ። ጃፋር በጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ቢሮ ተገኝቶ፤ ቃሉ ፍርድ ቤት ማስረጃ ሆኖ እንደሚቀርብበት ተነግሮት በውዴታ ቃሉን ሰጠ።
ጃፋር በሰጠው የዕምነት ክህደት ቃል ላይ ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል። በጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከሟች አህመዲን ጋር መጋጨታቸውን እና የግጭታቸው መንስኤም ቤት ሲጠርግ አቧራ አቦነንክብኝ በሚል ምክንያት ነው ብሏል። እርሱም አህመዲንን ‹‹ቦርኮ›› ብሎ መሰደቡን እና አህመዲን እንዳነቀው፤ እርሱም የአህመዲንን እጅ ከአንገቱ ላይ በማላቀቅ ወርውሮ እንደጣለው ገልጿል።
በድጋሚ ሟች አህመዲን ከወደቀበት ተነስቶ በጥፊ እንደመታው እና የአህመዲንን ምት ተከትሎ እርሱ ደግሞ በብስጭት ደጋግሞ በቦክስ የአህመዲንን ሆድ መምታቱን፣ አህመዲን ሲያጎነብስ በክርኑ ጀርባውን እንደመታው በመጨረሻም አህመዲን ሲወድቅ ደጋግሞ ጭንቅላቱን እንደረገጠው አምኖ አህመዲን በመሞቱ ግን መፀፀቱን ገለፀ።
የፖሊስ የምርመራ ቡድን ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ጳሆ 8/1713 የተፃፈ የአስክሬን የምርመራ ውጤት ማስረጃ፤ የሟችን ማንነት እና ሟች በሰውነት ክፍሎቹ ላይ የደረሰበትን ጉዳት የሚያሳይ ፎቶ፤ የተጠርጣሪውን የእምነት ክህደት ቃል ጨምሮ ስምንት ምስክሮችን አካቶ ለዓቃቤ ሕግ አቀረበ።
የዓቃቤ ሕግ ክስ
ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 540ን ተላልፎ ተገኝቷል ሲል ክስ ለመመስረት የወንጀል ዝርዝሩን አቀረበ። ከፖሊስ የምርመራ ቡድን የቀረበለትን የወንጀሉን መነሻ፣ ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሁኔታ የሚያመላክቱ መረጃ እና ማስረጃውን አደራጅቶ እና አዳብሮ ለፍርድ ቤት አቀረበ።
ዓቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ላይ እንዳብራራው፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው ቦሌ ሚካኤል አቅራቢያ በጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ የግድያ ወንጀል ተፈፅሟል። ሟች እና ተጠርጣሪ የፀባቸው መነሻ ቤት ሲጠረግ አቧራ ቦነነ በሚል ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በመደባደባቸው የአህመዲን ሕይወት አልፏል። ይህንን ለማስረዳት ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአስክሬን የምርመራ ውጤት ማስረጃን ከማቅረብ በተጨማሪ፤ የሟችን ማንነት እና የደረሰበትን ጉዳት የሚያመለክት ፎቶ ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል። በተጨማሪ ስምንት የሰው ምስክሮች በየተራ እንዲመሰክሩ በማድረግ ተጠርጣሪው ጃፋር አባጎጃም አህመዲንን ገድሏል ብሎ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጥያቄ አቅርቧል።
ውሳኔ
ተከሳሽ ጃፋር አባጎጃም አባ ጅርጋ በተከሰሰበት ሰው የመግደል ወንጀል ጉዳዩ በፍርድ ቤት ክርክር ሲታይ ቆይቶ ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን ተሰጥቷል። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት፤ ፍርድ ቤቱ ክስ እና ማስረጃውን ከሕግ ጋር አገናዝቦ ተከሳሹን ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል ብሎ ባመነበት በአምስት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም