ሰርተፊኬቱ የዩኒቨርሲቲው ምሩቃን በኢንዱስትሪዎች የሚኖራቸውን ተፈላጊነት ይጨምራል

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ያገኘው ISO ሰርተፊኬት ምሩቃኑ በኢንዱስትሪዎች የሚኖራቸውን ተፈላጊነት የሚጨምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የጥራት ስራ አመራር ስርአት ( ISO 2009: 2015 ) ማእቀፍ ውስጥ የተቀመጡትን መመዘኛዎች አሟልቶ በመገኘቱ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ 13 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በነዚህ አመታትም ለጥራት ቅድሚያ እየሰጠ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ዶ/ር ደረጀ ዩኒቨርሲቲው በ2022 በሀገሪቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእቀል ሆኖ ለመውጣትና በአህጉር ደረጃ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን አቅዶ የመማር ማስተማር፣የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ISO በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የጥራት አያያዝ መስፈርት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዩኒቨርሲቲው ሰርተፊኬት ማግኘቱም የትምህርት ጥራት ስብራትን ለማስተካከል የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ተገማች፣ ህግና ስርአትን የተከተለ እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ አሰራሮችን ሲተገብር በመቆየቱ ሰርተፊኬቱን ሊያገኝ መቻሉ ተናግረዋል፡፡

የጥራት ስራ አመራር ስርአት የምስክር ወረቀትም የተሻለ የደንበኛ እርካታ እንዲኖር፣ የገበያ ተደራሽነትና ተፈላጊነትን ለመጨመር፣ የምሩቃኑን በኢንዱስትሪዎች ተፈላጊነት ለመጨመር፣ ተግባራዊነት ያላቸው የምርምር ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስም ለመገንባት የሚያስችለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ISO 17025 የላብራቶሪ አክሪዴሽን ስራንና የአካዳሚክ ፕሮግራሞች አክሪዴሽን ለማግኘት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጥራት ቅንጦት ሳይሆን አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ ነው ነው ያሉት ዶ/ር ደረጀ ለዚህም ከፍተኛ ፍላጎት ፣ልባዊ ጥረትና መሰጠትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁሉም የትምህርት ተቋማት ይህንን አሰራር ምሳሌ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ማእከል ሚኒስትር ዴኤታ ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል (ዶ/ር ) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ጥራት አሰራር ስርአቶችን ተግብሮ ለእውቅና ብቁ ሆኖ መገኘቱ በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፋና ወጊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሰርተፊኬት ለተጨማሪ መሻሻል፣ ለዩኒቨርሲቲው ተደራሽነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማእከል መሆኑን ለማረጋገጥ ሊጠቀመው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You