ኢሬቻ- የምስጋናና የሰላም ምልክት

የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በረዥም ጊዜ የሕይወት ውጣ-ውረዱ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ሥርዓት ሲሆን፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነው የምስጋና፣ የሰላምና የወንድማማችነትም ምልክት እንደሆነም ይነገርለታል::

የኦሮሞ ሕዝብ የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመና፣ የጭጋግና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት ነው። ይህ በዓል በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አርሰዲ ከመከበሩ በፊት በዓሉን የሚገልጹ የተለያዩ ሁነቶች ይካሄዳሉ።

በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ በክፍለ ከተማ ደረጃ ሰሞኑን ፌስቲቫል ተካሂዷል። በዚሁ ወቅት የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካባ መብራቱ እንደሚገልጹት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች እህትና ወንድሞቹ ጋር በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነው የምስጋና፣ የሰላምና የወንድማማችነትም ምልክት ነው::

የኢሬቻ በዓል የእርቅ፣ የሰላምና የአንድነት ነው:: ለኦሮሞ ሕዝብ ኢሬቻ የአንድነት መገለጫና ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት መሆኑንም የሚገልጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ የዓለም ቅርስና የኢትዮጵያዊያን ሀብት የሆነው የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በአብሮነትና የሀገርን ገጽታ በሚገነባ መልኩ በማክበር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ያነሳሉ።

እንደ ሥራ አስፈፃሚዋ ገለጻ፤ በዓሉ ከወረዳ ጀምሮ የተለያዩ ባህላዊ ሁነቶችን በማካሄድ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል:: በፌስቲቫሉ ላይ ከኦሮሞ ተወላጆች በተጨማሪ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተገኝተዋል:: ኢሬቻ የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የመተሳሰብና የአንድነት በዓል ስለሆነ ይህንንም በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በተደረገው ዝግጅት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መታደም ችለዋል::

በአዲስ አበባ ደረጃ ለሚከበረው የሆራ ፊንፊኔም ወደከተማው የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት መደረጋቸውን የሚያነሱት ሥራ አስፈፃሚዋ፤ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የኦሮሚያ ክልል አጎራባች በመሆኑ የሚመጡ በርካታ እንግዶችን ለማስተናገድና በተለይም በዓሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል::

በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ወጣቶች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች፣ ፎሌዎችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ዝግጅት አድርገዋል:: ከወጣቶች የሚጠበቀው አካባቢዎቻቸውን በንቃት መጠበቅና በተጨማሪም በአራቱም አቅጣጫ የሚመጡ እንግዶችን ማስተናገድ በመሆኑ ዝግጅት ማድረጋቸውን ወይዘሮ ካባ ያነሳሉ::

ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ከዚህ በተጨማሪም በዓሉ የወንድማማችነትና የአንድነት ሆኖ እንዲከበርና የሚመጡ እንግዶችም ሰላማቸው ተጠብቆ ወደየመጡበት አቅጣጫ እንዲመለሱ የሰላምና የጸጥታ መዋቅሩ እስከ ብሎክ ድረስ በመደራጀት አካባቢውን በሶስት ፈረቃዎች በተጠንቀቅ እየጠበቀ እንደሚገኝ ይገልጻሉ::

የኢሬቻ በዓል እምነት ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነትና በወንድማማችነት ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው:: በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም(ዩኔስኮ) በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን የሚገልጹት ደግሞ የፌስቲቫሉ ታዳሚ የሆኑት አባገዳ ተክሉ መልካ ናቸው::

እንደ አባገዳ ተክሉ ገለጻ፤ በዓሉ ከዚህ ቀደም ተደብቆ የነበረ ቢሆንም በተደረጉ ጥረቶች የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ማክበር ከተጀመረ አምስት አመት ሆኖታል:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያከብረው የራሱ ባህል እንዳለው ሁሉ የኦሮሞ ሕዝብም የኢሬቻ በዓል የሰላምና የወንድማማችነት መሆኑን በመገንዘብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በነቂስ ያከብረዋል::

በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የሕዝቦችን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ያስፈልጋል:: በዚህም የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አከባበር አንድነትን፣ አብሮነትን የበለጠ በማጉላትና ሕብርን በሚያሳይ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አባገዳ ተክሉ ይናገራሉ።

የፌስቲቫሉ ተሳታፊ ወጣት ግርማ አሰፋ በበኩሉ እንደሚገልጸው፤ ኢሬቻ ኢትዮጵያ ያላትን ባህልና እሴት አጎልቶ ለማሳየትና ለማስተዋወቅ የሚያስችል ትልቅ በዓል በመሆኑ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ልዩ በሆነ መልኩ እየተከበረ ይገኛል::

የኢሬቻ በዓል ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተሰባስበው የሚያከብሩት የጋራ በዓል በመሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ በዓሉን ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በአንድ ላይ በመሆን እንደሚያከብረው የሚገልጸው ወጣት ግርማ፤ በመሆኑም ወጣቶች በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባም ይናገራል።

እንደ ወጣት ግርማ ገለጻ፤ ይህ ትውልድ ሰላሙን አጥብቆ በመጠበቅና መገፋፋትን በማስወገድ የበዓሉን ባህላዊ እሴቶች በማስጠበቅ ወደሚቀጥለው ትውልድ ማሻገር ይኖርበታል:: የሰላም መነሻው ከምንኖርበት ቤታችን ነው፤ ይህም እያደገ ወደዓለም ይደርሳል:: ሰላም በምንም የማይለካና በዋጋ ሊተመን የማይችል ነው:: ሰላምን ማስጠበቅ የሚቻለውም ሁሉም በጋራ ሲቆም ነው::

በፌስቲቫሉ ላይ የተለያዩ ባህላዊ ውዝዋዜዎች በክፍለ ከተማው ባንድ ለታዳሚዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ካባ መብራቱን ጨምሮ ሌሎች የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ አባገዳዎች፣ሀደ ስንቄዎች፣ፎሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You