ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው፤ የሰላም፣ የአንድነትና የብራ ንጋት መልካም ምኞት ምልክት የሆነው ኢሬቻ፤ የኦሮሞ ሕዝብ በጋራ ወጥቶ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ትልቅ በዓል ነው ብለዋል።

አቶ ተመስገን እንደገለጹት፤ ዝናብ ሰጥቶ ያበቀለውን ፈጣሪ፣ የክረምቱን ጎርፍና በረዶ በሰላም አሳልፎት ብሩህ በሆነና በተስፋ ወደ ተሞላው ብራ ያሻገረውን ፈጣሪ፤ ለማመስገን ወደ መልካ (ወንዝ) ወጥቶ የኢሬቻን ሥርዓት ይፈጽማል፡፡

“ብራ ለፍጥረት ሁሉ ልዩ ነው። ለሁሉም የሚተርፍ ነገር አለው። ብራ ምድሩ በልምላሜ ተሞልቶ፣ በአበቦች ውበት አጊጦ፣ ጋራው ሸንተረሩ ዓይንን የሚማርክበት ወቅት ነው። የአበቦች መዓዛ አካባቢን የሚያውድበት ጊዜ ነው”ብለዋል አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው።

እንስሳት እንደልብ ግጦሽ የሚያገኙበት ነው፤ ክረምቱን በቀፎ ውስጥ በረሃብ ያሳለፉት ንቦች ወጥተው አበቦችን እያማረጡ በመቅሰም ማር ለመስራት የሚታትሩበትም ነው ብለዋል።

ብራ ክረምቱን ተሸሽገው የቆዩ አዕዋፍ ዜማ እያሰሙ የሚጠራሩበትና የሚፈላለጉበት ወቅት ነው። ስለ ዜማ ከተነሳ አዕዋፋት ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም እያዜሙ የሚፈላለጉበትና የሚገናኙበት ወቅት ነው፤ ኦሮሞም በዚህ ውብና በተስፋ በተሞላ ወቅት የክረምቱን አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፎት በሁሉም ነገር ወደተትረፈረፈ ብራ ላሻገረው ፈጣሪው በጋራ እውቅና ይሰጣል፤ በህብረትም ምስጋና ያቀርብለታል ብለዋል።

በኢሬቻ እርጥብ ሣር ይዞ ወደ መልካ (ወንዝ) በመውጣት አንዱ ለሌላኛው ያለውን ክብር የሚያሳይበት፣ የተጣላ ይቅር የሚባባልበት፣ ለፈጣሪው ያለውን ምስጋና የሚገልፅበት እንደሆነም በመልዕክታቸው ገልጸው፤ ለመላው የኦሮሞ ሕዝብም ለ2017 የኢሬቻ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You