የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄድ ከጀመረ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን የሚያሻግር፤ ሰላሟን የሚያፀና እና ልማትን የሚያረጋግጥ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የጎሳ መሪው ኢብራሂም አሊ ከዞን ሦስት ዱለቻ ወረዳ ተወክለው የመጡ ተሳታፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተን መፍትሔ በማስቀመጥ ሰላማችንን እንድናፀና እና ፊታችንን ወደ ልማት እንድንመልስ የሚያደርግ ነው።
ወዳጅ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጠላትም እንዳለን ልንረሳ አይገባም የሚሉት የጎሳ መሪው፤ ጠላቶቻችን እንዳያገኙን እኛ በውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ስምምነት ላይ መድረስ አለብን ሲሉም ያሳስባሉ።
አለመግባባቶችን በንግግር መፍታት የኖርንበት ባህላችን ነው። እኛ አፋሮች ምንጊዜም ወደ ፍርድ ቤት አንሄድም። በግለሰቦች መካከልም ሆነ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን የተበደለውን ክሰን፣ አስተቃቅፈን እና አሳስመን በዛፍ ጥላ ስር ነው የምንፈታው ነው የሚሉት።
ይህ ባህላዊ የግጭት አፈታታችን ሳይናቅ እውቅና ተሰጥቶት በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንድንሳተፍ በመጠራታችን ልምዳችንን ተጠቅመን በሀገር ደረጃ ያለውን ችግር ለመፍታት የራሳችንን መፍትሔ እናዋጣለን ሲሉም ያክላሉ።
ከዞን አራት ወሊና ወራዳ ተወክለው የመጡት ሌላው ተሳታፊ የ54 አመቱ አርብቶ አደር አዴን አግዲሳ አዴን፣ ምክክሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አለመግባባቶችና ግጭቶች መቋጫ እንዲያገኙ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንዲሁም ዘላቂ ልማት ለማካሄድ የሚያስችል ነው ይላሉ።
አርብቶ አደሩ፣ አርሶ አደሩን፣ ነጋዴው፣ የመንግስት ሠራተኛው፣ ተማሪው፣ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች የተካተቱበት ከዘጠኝ ዘርፎች የተውጣጣ ቡድን እርሳቸው ከመጡበት ወረዳ ተወክሎ በአጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝም ይገልጻሉ።
ምክክራችን የእስካሁን ሂደቱ አስደሳች ነው። እርስ በእርስ ተደማምጠው በሥነሥርዓት እየተወያዩ እንደሚገኙ የሚጠቁሙት አርብቶ አደሩ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሰላም እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ሰመራ ከተማን ወክላ የተገኘችው ወጣት መዲና ኢብራሂም በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፉ ለክልላችን እና ለሀገራችን የሚጠቅሙ በመሠረታዊነት ለአለመግባባታችን ምክንያት የሆኑ አጀንዳዎችን በማንሳት በሰከነ መንፈስ እየተነጋገርን እና እየተወያየን እንገኛለን ብላለች።
ምክክሩ ለሀገራችን ብርሃን፣ ዕድል እና ተስፋ ይዞ የመጣ ነው። ይህን ታሪካዊ ዕድል በአግባቡ ተጠቅመን ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታና ስደት ተወግዶ አለመግባባቶችን በንግግር የመፍታት ባህል እንዲዳብር እና በአብሮነት ሀገራችንን ለማሳደግ ሁላችንም የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ስትልም ጥሪ አስተላልፋለች።
ከአዋሽ ከተማ መስተዳድር ተወክለው የመጡት የመንግሥት ሠራተኛው ሃጂ መሃመድ አርባ በበኩላቸው፤ እያደረግን ባለነው ውይይት እንደ ክልል አንኳር ናቸው ያልናቸውን አጀንዳዎች እየለየን ነው። በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ ችግር ምንድን ነው የሚለውን አንጥረን በማውጣት በሽታው እንዲወገድ በማድረግ ሀገራችንን ለዘላቂ አላማ ለማዘጋጀት እየተነጋገርን እንገኛለን ነው ያሉት።
የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በሀገር ደረጃ ለሚደረገው ምክክር አንኳር አጀንዳዎችን እና ክልሉን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን በመምረጥ ከሁለት ቀናት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም